የሀገር ውስጥ ዜና

ዜና ከኢትዮጵያ ውስጥ

ክልሉ ከቱሪዝም ዘረፍ ከ484 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ

  • PDF

አዲስ  አበባ ፤ ሚያዚያ 16/ 2006 (ዋኢማ) -ባለፉት  ዘጠኝ ወራት  ከቱሪዝም  ዘርፍ  ከ484 ነጥብ 5 ሚሊዮን  ብር  በላይ  ማግኘቱን የኦሮሚያ ክልል  አስታወቀ ።
የቢሮው የሕዝብ  ግንኙነት ሃላፊ  አቶ ከፍያለው ሞቲ ለዋልታ እንደገለጹት ገቢው የተገኘው ክልሉን ከጎበኙት  1 ሚሊዮን 223ሺ የውጭ ቱሪስቶችን ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተገኘው ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 17 በመቶ የቱሪስት ፍሰቱ ደግሞ 15 በመቶ ማደጉን አቶ ከፍያለው ተናግረዋል ።
የክልሉን  የተፈጥሮና ታሪካዊ  መዳረሻ  ሥፍራዎች  ለማልማት የክልሉ  መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን  እያደረገ  ነው ያሉት አቶ ከፍያለው  የመንገድና የውሃ  አገልግሎት በሥፍራዎቹ እንዲስፋፉ የአካባቢው ሕዝብ ከጉልበት  እስከ ገንዘብ  መዋጮ  ድርስ  አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል ።
በክልሉ 120 የሚሆኑ የጥብቅ ደኖችን የክልሉ መንግሥት ከአካባቢው ሕዝብን በማሳተፍ እየለሙ ይገኛሉ ያሉት አቶ ከፍያለው ጥብቅ ደኖችን ከሰዎችና ከእንስሳት ንኪኪ ነጻ እንዲሆኑና ካርታ እንዲወጣላቸው መደረጉን ገልጸዋል ።
በክልሉ የሆቴሎችን የቱሪስት አቀባበል ለማሻሻል ለ 1607 ሆቴሎች ሙያዊ ድጋፍ ፤ ክትትልና ሥልጠና ለመሥጠት ታቅዶ  በክልሉ ለሚገኙ  ለ3ሺ143  ሆቴሎች  ሙያዊ ድጋፍ ፤ ክትትልና ሥልጠና  ተሠጥቷል  ብለዋል ።
በክልሉ የሚገኙ እንደ አባጅፋር ቤተመንግሥት፤ ሼክ ሁሴን፤ኩምሳ ሞረዳና  የአምቦ ቤተ መንግሥትን  የመሳሰሉ ቅርሶችን  ለመጠገን የክልሉ ባህልና  ቱሪዝም  ቢሮ በመንቀሳቀስ ላይ  እንደሚገኝ ዋልታ  ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።   


የንግድ ሚኒስትር ሠራተኞች ለ2ኛ ጊዜ ቦንድ ለመግዛት ቃል ገቡ

  • PDF

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 16/ 2006 (ዋኢማ)- የንግድ ሚኒስቴር ሠራተኞች ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ለሁለተኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል ገቡ ።
ዛሬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተካሄደ የቃል መግባት ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሊ ሲራጅ እንዳሉት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን በዓመት በቦንድ መልክ ለመክፈል መወሰናቸው እንዳስደሰታቸው በመግለጽ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከአሁኑ ትውልድ አልፎ ለወደፊቱ ትውልድ ጥቅም የሚሠጥ በመሆኑ ሁሉም በአንድነት አሻራውን ሊያሳርፍ ይገባል ብለዋል ።
የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ የሃገሪቱን የቁጠባ ባህል በማሳደግ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ አሊ በብዙ ሃገራት የቁጠባ ባህል ሲያድግ በቀጣይነት ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ በመሆኑ ለሃገሪቱ ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል ።
የሚኒስቴሩ ሠራተኞች በበኩላቸው የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ የሚገነባ በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደአቅሙ የቦንድ ግዥ በፈጽም መልካም መሆኑን አስረድተዋል።
ከማዕድናት ወጪ ንግድ ከ343 ሚልዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

  • PDF

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 15፣ 2006 (ዋኢማ) - ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዘመናዊና በባህላዊ መንገድ ተመርተው ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ማእድናት 343 ነጥብ 3 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።
የተገኘው የውጭ ምንዛሪ መስሪያ ቤቱ ካስቀመጠው ግብ አንፃር ሲታይ በግማሽ የሚገኝ ሲሆን አፈፃፀሙ ዝቅ ሊል የቻለው የዓለም የወርቅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ እና ኩባንያዎች ያመረቱትን ወርቅና ታንታለም ሙሉ በሙሉ ባለመሸጣቸው መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ለውጭ ገበያ ከቀረበው 8682 ኪ.ግ በላይ ወርቅ ውስጥ 5,752 ኪ.ግ በላይ የሚሆነው በባህላዊ መልኩ የተመረተ ነው፡፡
የዓለም አቀፉ የወርቅ ዋጋ ውድቀት የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በባህላዊ ማዕድን አምራቾች የሚመረቱ የማዕድናት ምርት መጠንን በማሳደግ እና በጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ በመሸጥ ለበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተያዘውን የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከማዕድን የወጪ ንግድ አንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡


ግብጽ ወደ ውይይቱ እንድትመለስ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/ 2006 (ዋኢማ) - በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በሚደረገው የሦስትዮሽ ውይይት ግብጽ እንድትመለስ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የመንግስታቸውን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ሲያቀርቡ እንዳሉት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ድርድሩ እንድትመለሰ ግፊት ያደርግ ዘንድ እየተሰራ ነው።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርትም ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም ጋር መልካም የሆነ ትስስር እንዳለ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል በታላቁ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ስምምነቶች መደረሱ የሀገራቱን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማጠናከሩንም ነው የገለጹት።

ከአፍሪካ ውጪ እንደ ቻይና እና የአውሮፓ ህብረት ካሉ አጋር አካላት ያለው ግንኙነት  ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደው የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር የሀገራችን ጉብኝትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

የፊንላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቀድሞው የጀርመን ፕሬዝዳንት በሀገራችን ያካሄዷቸው ጉብኝቶችም የግንኙነቶቹ ማሳያ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የካይዘን ኢስቱትዩት ወደ አፍሪካ የሰው ሃይል የልማት ኢንስቲትዩትነት እንዲቀየር መወሰኑንም ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

ተቋሙ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ቀደም ብሎ አሳካ

  • PDF

ጋምቤላ ፤ሚያዚያ 15/ 2006 (ዋኢማ) - የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በቁጠባ በኩል ያስቀመጠውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀደም ብሎ ማሳካት መቻሉን አስታወቀ።
የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መኮንን የለውምወሰን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የመጨረሻ ዘመን 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለማስቆጠብ ታቅዶ ነበር።
እስከ አሁን ባለፈው አፈጻጸም ግን በተቋሙ የተቆጠበው አጠቃላይ ገንዘብ አራት ቢሊየን ብር መሆኑን አቶ መኮንን ተናግረዋል።
በዚህም በቁጠባ በኩል  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ቀደም ብሎ በመሳካቱ አዲስ ዕቅድ የማዘጋጀት ስራ ይሰራል ብለዋል።  በዘንድሮው በበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ደግሞ ተቋሙ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንዲቆጠብ አድርጓል ነው ያሉት።
ተቋሙ ለህብረተሰቡ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት አሁን ካሉት 350 ፅህፈት ቤቶች በተጨማሪ በየአካባቢው የቁጠባ ማዕከላትን እያቋቋመ እንደሚገኝ መግለጻቸውንም ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።