በድሬዳዋ 147 ሺ 731 መራጮች ተመዘገቡ

  • PDF

ድሬዳዋ፤ የካቲት 12/2005/ዋኢማ/ - በመጪው ሚያዝያ ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ 147 ሺ 731 መራጮች መመዝገባቸውን የድሬዳዋ የምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ ወይዘሮ ጊኒ ረሺድ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ከተመዘገቡት ውስጥ 74 ሺ 174 ወንዶች ሲሆኑ 73 ሺ 557 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ምርጫው በሁለት የምርጫ ክልሎች የሚካሄድ ሲሆን፤ በከተማ 151 በገጠር ደግሞ 79 የምርጫ ጣቢያዎች ነው ብለዋል።

በከተማዋ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ሴቶች በመራጭነት፣ ተመራጭነት፣ ታዛቢነትና በምርጫ አስፈጻሚነት ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ወይዘሮ ጊኒ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።