ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የተሰማረ የሰው ኃይል ለማፍራት አማራጭ እንደምትሆን ተገለፀ

  • PDF

ጅጅጋ፤ የካቲት 12/2005/ዋኢማ/ - በኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመገንባት ላይ ለምትገኘው ሶማሊያ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት አማራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሶማሊያ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስታወቁ።

የሶማሊያ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፕሮፌሰር መሀመድ ኡስማን ጀዋሪ የሚመራው የሶማሊያ ፓርላማ ልዑካን ቡድን በሶማሌ ክልል የሚገኙትን የጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የዶክተር አብዱል መጅድ ሁሴን መምህራን ኮሌጅ፣ የጅጅጋ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እና  ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የጅጅጋ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ሪፈራል ሆስፒታል አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

የልዑካን ቡድኑን የመሩት የሶማሊያ ፓርላማ ፕሮፌሰር አፈ-ጉባኤ መሀመድ ኡስማን ጀዋሪ ጉብኝቱን ካጠናቀቁ በኋላ በተለይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ መንግስት እየተከተለ ባለው የከፍተኛ ትምህርት ልማት የአገሪቱ ዜጎችንና የጎረቤት አገር ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል።

ይህም የሀገራቱን ህዝቦች ወንድምማማችነት ከማጠናከሩም በላይ ሶማሊያን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።
ሶማሊያን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት በኢትዮጵያ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማራጮቻችን ይሆናሉ ያሉት የልዑካን ቡድን መሪው፤ የከፍተኛ ትምህርትን ካስፋፋችው ኢትዮጵያ በርካታ ተሞክሮዎችን እንደምትቀስምና ለተግባራዊነቱም በጋራ መስራት ሶማሊያ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምትከተለው የፈዴራሊዝም ስርዓት የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጧን ተመልክቻለሁ ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ በተለይ በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ በሚገኘው የሶማሌ ክልል አካባቢ የጎበኙት የልማት እንቅስቃሴ እጅጉን ያስደሰታቸው መሆኑንና ልምድ የሚወስዱበት መሆኑን መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።