ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ልማትና በዘመናዊ እርሻ መስፋፋት ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12 (ዋኢማ) - ኢትዮጵያን መካከኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ በኢንቨስትመንት መስክ የሚሰማሩ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ልማትና በዘመናዊ እርሻ መስፋፋት ላይ ትኩረት እንዲሰጡ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አርከበ ዕቁባይ አሳሰቡ፡፡

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ 38ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የካቲት 10/2005 ከባለሃብቶች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል፡፡
አቶ አርከበ ዕቁባይ በዚሁ እንደገለጹት መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች ትኩረታቸውን በኢንዱስትሪና በዘመናዊ እርሻ ላይ ካደረጉ መንግስት ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ ያደርግላቸዋል፡፡

የመንግስት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አቅጣጫ በኢንዱስትሪና በዘመናዊ እርሻ መስፋፋት ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አርከበ ዘርፎቹ አገሪቱ በወጪ ንግድ መስክ ተጨማሪ እሴት ያላቸውን እና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን በማሟላት ዘርፈ በዙ ልማቷን ማፋጠን ያስችላታል ብለዋል፡፡

በዚህም ባለሃብቶቹ ለዜጎች ሰፋፊ የስራ ዕድሎችን ከመፍጠርና ድህነትን ከመቀነስ ባሻገር በዕቅዱ ስኬታማነት የድርሻቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ባለሃብቶቹ በዚህ ረገድ ጥረት ካደረጉ በመንግስት በኩል ያሉ ጉድለቶችና ችግሮች በየጊዜው በሚደረግ ምክክር መፍትሔ እንደሚሰጣቸውም ቃል ገብተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ በውይይቱ ላይ አንዳንድ የአሰራር ጉድለቶችና የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ የሚሰተዋሉ ችግሮችን የጠቆሟቸው መሆኑንና ይህንን መንግስት እንደለ እንደሚቀበለው አቶ አርከበ ገልጸው በተወሰኑ ተቋማት ላይ የእርምትና የማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ገልጸዋል፡፡ በባለሃብቶች አካባቢ ብድር ከባንክ ወስደው በወቅቱ ክፍያ የማይፈጽሙ አዋጪ ያልሆነ ፕሮጀክት ይዘው የሚቀርቡ እንዳሉ እና መንግስት በዚህ ረገድ የቅድሚያ ትኩረት ለሰጣቸው ዘርፎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ክፍሎም ገብረህይወት አገርን ከድህንት ለማውጣት በሚደረገው ርብርብ የድርሻችንን ለመወጣት ቃል ገብተናል ብለዋል፡፡ አገሪቱ በፋጣን ዕድገት ላይ የምትገኝ ቢሆንም ሲወርዱና ሲወራረዱ የመጡ የቢሮክራሲና የቀልጣፋ አገልግሎት አስጣጥ ችግሮችን ከስር መሰረቱ ለማስቀረት ባለሃብቶች ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ ህወሓት በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወጣቶች የባለራዕዩ መለስ ዜናዊን ፈለግ ተከትለው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ እንዲረባረቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ወጣቶቹም በሰጡት አስተያየት የተረጋገጠውን ሰላም በመጠቀም ስራ በመፍጠርና ራሳቸውን በመቀየር ሀገሪቱ በያዘቻቸው እቅዶች ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

38ኛውን የህወሓት በዓል ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ምሁራን ጋርም ውይይት ተካሂዷል፡፡ በአዲስ አበባ በተካሄደው በዚሁ ውይይት የተሳተፉ ምሁራን ባላቸው እውቀት የተያዘውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አባይ ፀሀዬ በውይይቱ ወቅት ህወሓት ለዚህ ውጤት የደረሰው ህዝባዊ አላማን አንግቦ በመነሳቱ፣ የነጠረ አመራር በመስጠቱ፣ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያትን በመላበሱ፣ ፅኑና ለመስዋዕትነት ዝግጁ የሆነ ታጋይ ህዝብ ከጎኑ በማሰለፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ አባይ አያይዘውም ወጣቱ ትውልድ ለትምህርት ትኩረት በመስጠት የተጀመረውን የፀረ ድህነት ትግል ውጤታማ ለማድረግ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ (ኢሬቴድ)