ህወሓት የተመሰረተበት 38ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ከተሞች በድምቀት ተከበረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12 (ዋኢማ) - በታጋይ መለስ ዜናዊ በሳል አመራር በብሩህ የእድገት ጎዳና ላይ የሚገኘውን የሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መስመር አጠናክረን በማስቀጠል ለዕድገትና ብልፅግና እንረባረባለን ሲሉ በአዳማና አካባቢው የሚገኙ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ገለፁ።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ / ህ.ወ.ሓ.ት/ የተመሰረተበት 38ኛው ዓመት በዓል በአዳማ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

በአዳማ ከተማ የመለስ ሌጋሲ በሚል ርዕስ በተካሔደ የፓናል ውይይት ላይ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች በሰጡት አስተያየት ድንገተኛው የታጋይ መለስ ዜናዊ ህልፈት ክፉኛ ቢያሳዝናቸውም በበሳል አመራራቸው ያስጀመሯቸውን ጠንካራ የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ መስመ በፅናት በመተግበር ህያው ሆኖ እንዲዘልቅ እንረባረባለን ብለዋል።

የፓናል ውይይቱን የመሩት የትግራይ ልማት ማህበር የአዲስ አበባና አካባቢው ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ህሉፍ እንደገለጡት በተራማጅ ህዝባዊ ዓላማ፣ በብቁ አመራር፣ በፅናትና ህዝባዊ የትግል መንፈስ ለድል የበቃው የህወሓት ኢህአዴግ መስመር በድህነት ላይ አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ እንዲችል እጅ ለእጅ የምንረባረብበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የአዲግራት ከተማ ህዝብ በዓሉን በደማቅ ስነ ስርአት አክብሯል ።

የአዲግራት ከንቲባ አቶ ከሃሰ ገብረመድህን መላው ህዝብ በተለይ ወጣቱ የአሁኑ ሰላምና ዴሞክራሲ ፣ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ ያደረገውን መራራ ትግልና የተከፈለውን መስዋዕት አስታውሰዋል።
የህዝቡና የማህበራት ተወካዮች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፣ሙስናና ኪራይ ሰብሳብነትን በመታገል የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመሩትን የልማት ተግባራት ለማስቀጠል እንደሚረባረቡ ቃል ገብተዋል፡፡ (ኢዜአ)