ለተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12 (ዋኢማ) - በየደረጃው ያሉ አካላት ለተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከሀገር አቀፍ የጎልማሶች ትምህርት ቦርድ እና ከተቀናጀ የሴቶችን አቅም ማጎልበት መርሀ ግብር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የጎልማሶች ትምህርት የህዝብ ንቅናቄ ጉባዔ ተጀምሯል፡፡

በጉባዔው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት ቁልፍ የልማት አቅም የሆነውን የሰው ሀይል ለማልማት በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም የትምህርት ፍትሀዊ አቅርቦትን በማረጋገጥ ዙሪያ ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ በዚህም አለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር እውቅና የሰጧቸውና ያደነቋቸው ውጤቶችን አስመዝገበናል ነው ያሉት አቶ ደመቀ፡፡

የጎልማሶችን አቅም መገንባት አጠቃላይ የህብረተሰባችንን አኗኗር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርና ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ ያስችላል ያሉት አቶ ደመቀ በየደረጃው ያሉ አካላት ለተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፋአድ ኢብራሂም በበኩላቸው በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በምርት ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውን የ20 ሚሊዮን ጎልማሶች አቅም የመገንባት ግብ መጣሉን ገልፀዋል፡፡

ግቡን ተፈፃሚ ለማድረግም አምስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ሀገር አቀፍ የጎልማሶች ትምህርት ቦርድ እንዲሁም ከየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያቀፈ ሀገር አቀፍ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

በጉባዔው ላይ የዘጠኙ ክልሎች ተወካዮች የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት የ2005 በጀት አመት ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እና የየራሳቸውን ምርጥ ተሞክሮ አቅርበዋል፡፡
የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣በየደረጃው ያሉ የጎልማሶች የትምህርት ቦርድ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በጉባዔው ተሳትፈዋል፡፡ (ኢዜአ)