38ኛው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ የምስረታ በዓል ተከበረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12 (ዋኢማ) - 38ኛው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ የምስረታ በዓል በመቀሌ ከተማ በድምቀት ተከበረ፡፡

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዓሉን ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊን በማጣታችን በሀዘን ስሜት ብናከብረውም እሳቸው ባሰመሩልን የጠራ ፖሊሲና ስትራተጂ በመታገዝ በበለጠ ቁርጠኝነትና ቁጭት በመነሳሳት የተሻለ ስራ ለመስራት ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል፡፡

የህወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው በዓሉ በታላቁ መሪያችን ቀያሽነት የተጀመሩ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስራዎችን ከግብ በማድረስ ራዕያቸውን ለማሳካት ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ“ዘመቻ መለስ ለእድገትና እምርታ” በሚል መሪ ቃል ነው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና በሺዎች የሚቆጠሩ የመቀሌ ከተማና አካባቢው ህዝብ በተገኙበት በመቀሌ ሰማዕታት ሀውልት የተከበረው፡፡

በበዓሉ ላይ ለሰማዕታት የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ለመታሰቢያነት በተሰራው የመቀሌ ሰማዕታት ሀውልት ስርም የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡ (ኢሬቴድ)