በድሬዳዋ 43 ሚሊየን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዘ

  • PDF

ድሬዳዋ የካቲት 11/2005/ዋኢማ/ - የድሬዳዋ የገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለፉት ስድስት ወራት 43 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፈርሃን አሊ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ሲል የተያዙት የሲጋራ ምርት፣ የተለያየ መድሃኒት፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የምግብ ሸቀጣሸቀጦችና የተለያዩ ቁሳቁሶች ናቸው።


ግምታቸው 43 ሚሊየን ብር የሚያወጡት ቁሳቁሶች የተያዙት በጀቡቲ መስመር፣ በጅጅጋ ቶጎጫሌ ድንበር አካባቢ፣ በምዕራብ ሐረርጌ በባሌ ዞንና በሀረር በኩል ነው ብለዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ እቃዎችን ለመቆጣጠር የድሬዳዋ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ጠንከር ያለ ቁጥጥር እያደረገ በመሆኑ ውጤታማ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ስራ አስኪያጁ ገለፃ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን በመቆጣጠሩ በኩል ከህብረተሰቡ የሚገኘው መረጃ የጎላ እንደነበር ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጠልም ጥሪ አቅርበዋል።

ከህብረተሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ ለማሳደግ ጽህፈት ቤቱ ማቀዱን የገለፁት ምክትል ስራ አስኪያጁ አቶ ፈርሃን መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያስረዳል።