15 የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ለመሳተፍ እጩዎቻቸውን አስመዘገቡ

  • PDF

አዲስ አበባ የካቲት 11/2005(ዋኢማ) - በሚቀጥለው ሚያዝያ ለሚካሄደው የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስማ ጅሩ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢህአዴግ፣ ኢራፓ፣ መኦህዴፓ፣ኢዴአን፣ ኢሰዴፓ፣ ኢፍዴኅግ፣ ወህዴግ፣ ኢዴህ፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ ኢዴፓ፣  ቅንጅት፣ ሲአን፣ ኢሶህዴፓ፣ ቤጉህዴፓና ምሶህዴፓ ናቸው።

በዚሁ መሰረትም ኢህአዴግ በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋና በአዲስ አበባ ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ 7ሺ 276 እጩዎቹን አስመዝግቧል።

ኢራፓ በትግራይ፣ ደቡብና አዲስ አበባ 48፣ መኦህዴፓ በኦሮሚያና አዲስ አበባ 19፣ ኢፍዴኅግ በደቡብና አዲስ አበባ 23፣ ኢዴአን አዲስ አበባ ላይ ለከተማ ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ 3 እጩዎችን አቅርበዋል።

እንደ አቶ ይስማ ገለፃ ኢሰዴፓ አዲስ አበባ 6፣ የወላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) በደቡብ 1 ፣ ኢዴህ አዲስ አበባ  ላይ 6 ፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ኦሮሚያና አዲስ አበባ 3፣ ኢዴፓ አዲስ አበባ  ላይ 1፣ ቅንጅት አማራና አዲስ አበባ ላይ የሚወዳደሩ 90 እጩዎችን አስመዝግብዋል።

ሲአን ደቡብ ላይ 103 እጩዎችን፣ ኢሶህዴፓ ሶማሌ ክልል ላይ 270፣ ቤጉህዴፓ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 2ሺ 240፣ ምሶህዴፓ ሶማሌ ክልል የሚወዳደሩ 13 እጩዎችን እንዳቀረቡ የተናገሩት የቦርዱ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምስት የግል ተወዳዳሪዎችም ኦሮሚያ ክልል ላይ በእጩነት መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተዋውቁበት የአየር ሰዓት በሚያገኙበት ሁኔታ ቦርዱ ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝም አቶ ይስማ ገልጸዋል።