ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዘ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2005 (ዋኢማ) - ባለፉት ስድስት ወራት ግምታቸው ከ35 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሞያሌ መቆጣጠሪያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በተያዘው ዓመትም ከገቢ እቃዎች ከ249 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጫንያለው ፉጂ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ጽሕፈት ቤቱ ባሉት አምስት የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሊይዝ ችሏል።

ከተያዙት ቁሳቁሶች መካከል አዳዲስ ልብሶች፣ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ፣ሞባይሎች ፣ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል ተሽከርካሪዎች፣ ልባሽ ጨርቆች፣ኮስሞቲክስ እቃዎችና የታሸጉ ምግቦች እንደሚገኙባቸው አብራርተዋል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ከሻሸመኔ አካባቢ ወደ ኪኒያ ይጓዝ የነበረ ካናቢስ የተባለ ከሶስት ኪሎ ግራም በላይ ሀሺሽ መያዙን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ጽህፈት ቤቱ ከሁለቱ ክልል መስተዳደሮች ጋር የተቀናጀ አሰራር በመተግበር የኮንትሮባንድን አስከፊነትንና በሃገር ላይ ሊያመጣ ሰለሚችለው ጉዳት ለህብረተሰቡ ሰፋ ያለ ትምህርት በመስጠቱ ህብረተሰቡ ስለጉምሩክ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማሰተካከል ተባባሪ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሞያሌ ገቢዎችና ጉምሩክና ጽሕፈት ቤት ኮንትሮባንድን ከመከላከል በተጨማሪ የውጭ እቃ ገቢን የመሰብሰበ ሰራ አንደሚያከናውን የጠቆሙት አቶ ጫንያለው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከሰማንያ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

የገቢ አሰባሰቡ ወቅታዊ ሂደቶችን የተከተለ ነው ያሉት ስራ አሰኪያጁ በየወሩ የገቢ እቃዎች በመጨመር በዓመቱ መጨረሻ እስከ 249 ሚሊዮን ብር ለመሰበሰብ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የውጭ ገቢ እቃዎች ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸሩ እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ጫንያለው ይህም ሊሆን የቻለው ከዚህ በፊት ከውጭ ብቻ ይገቡ የነበሩ እቃዎች በሃገር ውስጥ በስፋት መመረት በመጀመራቸው እንደሆነ አስረድተዋል። ቅርንጫፈ ጽህፈት ቤቱ በዶሎ በነገሌ ቦረና በሀገረማሪያም በያቤሎ እና ሞያሌ ላይ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች አሉት።