ሐረካቱል ሸባብል ሙጅሃዲን ፊ ቢላድ ሂጅራይተን (ክፍል1)

  • PDF

ዮናስ (የካቲት 11/2005)

ስልጣን በምርጫ አንጂ “ጂሃዳዊ ሃረካትን” በማብጠልጠል የማይገኝባት ሃገር፤ጉዳዬ “ጂሃዳዊ ሃረካት” የሚል ርዕስ የተሰጠውና በብሄራዊ መረጃና የደህንነት አገልግሎት ተዘጋጅቶ በኢቴቪ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ ይህን ዘጋቢ ፊልም ጉዳዬ ያደረኩት ደግሞ ከኪነጥበባዊ እይታና ማሄስ አንፃር ሳይሆን ከሃገር ደህንነት እና ከተቃውሞ ፖለቲካ አቅጣጫ ነው፡፡
ለማለት የፈለግሁት ወይም ጉዳዬ ግልፅ ይሆን ዘንድ የጽሑፌን የትኩረት አቅጣጫ ዘርዘር አድርጌ ልጠቁም፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቅራቢነትና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አዘጋጅነት የተመለከትነው “ጂሃዳዊ ሃረካት” ሰሞንኛ መነጋገሪያ ነው፡፡ መነጋገሪያነቱ ደግሞ ከበዙ አቅጣጫ የሚታይና በርካታ የተወሳሰቡ የሚመስሉ ነገር ግን ግልጽ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

መነጋገሪያው የሚጀምረው ዘጋቢ ፊልሙ በመንግስትና በኢቴቪ የተፈበረከ ድራማ ነው ከሚለው ሃሳብ ሲሆን፤ ሲቀጥል በተጠርጣሪነት የተያዙ ግለሰቦች ውሳኔ ሳያገኙ ወይም ፍርድ ቤቱ ስራውን ሳይጨርስ ግልጽ ሊወጡ አይገባም ወይም በራሳቸው ላይ ሊመሰክሩ አይገባቸውም፤ ይህም ፀረ ህገ መንግስታዊ ነው የሚለው ይገኛል፡፡ ሌላው ደግሞ የተጠርጣሪዎቹ ተደብድበዋል፣ ተገደዋል የሚለው ጉዳይና የችሎቱ ዝግ የመሆኑም ነገር በስፋት እየተነሳ ነው፡፡

እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ በርካታ ሙግቶች በማህበራዊ ድረገጾችና በየመጽሔት ጋዜጣው ላይ ከመመልከታችን ባሻገር “ለሙስሊሙ ማህበረሰብ” ጥብቅና የቆሙ የሚመስሉ የተቃዋሚ ፖርቲዎች የመግለጫ ጋጋታና አስተያየቶችንም አንብበናል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን “የመንገስት  ፍብረካና ድራማ ነው፡፡” እና “ፀረ ህገመንግስታዊ ዶክሜንተሪ” ሲሉ በማህበራዊ ድረገጾች   ሲዘባበቱበት ያየናቸው ግለሰቦች ፍፁም ፀያፍና ሃራም የሆኑ ቃላትንም በማዥጎድጎዳቸው ማነው ፀረ ህገመንግስት? ማነው ሃራም? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት አስገድደውናል፡፡
ስለሆነም “ጂሃዳዊ ሃረካት” እውነት ነው? ወይስ ውሸት? ለማለት መመዘኛው ምንድነው? ህገ መንግስት፣ ህግ፣ እውቀት ወይስ ተቃውሞ ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ በኢቴቪ የቀረቡ ዘገባዎች ሁሉ ለምን ውሸት በአልጀዚራና በቪኦኤ የቀረቡት ሁሉ ለምን እውነት በሌላ መልኩ በመንግስት ሚዲያዎች የቀረቡት እና የሚቀርቡት ዘገባዎች ሁሉ ውሸት፤ በግል ፕሬስና በውጭ ሚዲያ የሚቀርቡት ሁሉ ለምን እውነት ይሆናሉ የሚሉትን ነጥቦች ከመፈተሽ በላይ ተጠርጣሪ የሚባለው የትኛው ነው በህግ ቁጥጥር ስር ያለ አካልና የዳኝነት ተፅዕኖ እንዴት ይገለፃል፡፡ ክስ ያልተመሰረተበት ግን ደግሞ በህግ ቁጥጥር ስር ያለ አካል ከፍርድ ውሳኔ ጋር እና ከዳኝነት አሰጣጥ ጋር የሚገናኘው ነገር አለን በ"ጂሃዳዊ ሃርካት” ላይ ያየናቸው ግለሰቦች ሁሉ   ከአወልያው ኮሚቴ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው 29 ግለሰቦች ጓድ ናቸው የሚሉትን መሰረታዊ ነጥቦች በመመልከት በየማህበራዊ ድህረገጾች እና በየግል ፕሬሱ የሚናፈሰውን ወሬ ተጨባጭ መሆንና ያለመሆን ጉዳይ እንመዝናለን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከህግ በላይ እየሆነ ያለው  ማን ነው የሚለውን ጥያቄም በማንሳት ብሄራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎትንና የፀረ ሽብር ግብረ ሃይሉን እና የተከሳሾች ጠበቃ ነኝ የሚሉትን የህግ ባለሙያ ጥብቅናቸው ለማን ነው?  ስል ከሰጧቸው ቃለ ምልልሶች       አንፃር በመሞገት ምላሹን ለአንባቢያን እተዋለሁ፡፡
ጉዳዮቼ ናቸው ስል ያነሳኋቸውን ነጥቦች እና ዝርዝር ጥያቄዎች እንደወረዱ መፈተሹ በሁለት ምክንያት ተገቢ አይመሰለኝም፡፡  የመጀመሪያው የሚዛናዊነት ጥያቄ ያስነሳል የሚለው ሲሆን ተከታዩና ከመጀመሪያው ጋር ተያያዥነት ያለው ምክንያቴ ደግሞ አንባቢያኖቼ ድረ ገጾችንም ሆነ ዘገባዎችን አንዲሁም ዶክመንተሪውን ላይመለከቱት እና ላይጎበኙት ይችሉ ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ሰለሆነም የዘጋቢ ፊልሙን ወይም የዶክሜንተሪውን ዝርዝር ይዘትና ጭብጥ በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡

በ“ጂሃዳዊ ሃረካት” ዘጋቢ ፊልም ላይ ቡድን መሪ ወይም የሴራው አቀጣጣይ ሆኖ ያስተዋልነው፤ (ግልጽ ለማድረግ ያመች ዘንድ በኪነጥበባዊ ቋንቋ ብገልፀው የተሻለ ስለሚሆን) የዘጋቢ ፊልሙ ዋና ገጸ ባህሪ አማን አሰፋ በሽብር ስሙ (አሁንም በኪነጥበባዊ ቋንቋ) የቃለ ተውኔቱ ገፀባህሪያዊ ስያሜ አማን እስማኤል የሽብር ቡድኑ አላማና የመጨረሻ ግብ በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት መመስረት መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከዘጋቢ ፊልሙ እንዳየነው እና እንዳደመጥነው  ዋና ተዋናይ አማን የሸብር መረቡ ኬንያ ከሚገኘውና የአልቃይዳ  የምስራቅ አፍሪካ ክንፍ በሆነው ዳሩ ቢላል በሞቃድሾ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የተዘረጋ መሆኑን በአንደበቱ አረጋግጧል፡፡ በዘጋቢ ፊልሙ እንዳየነው ይህ የሽብር ቡድን ስራውን እያከናወነ ያለው በሁለት መንገድ ነው። በአይዲዮሎጂ መስመርና በጂሃድ፡፡

የጂሃዱን መስመር የሚመራው አማን የተባለው ግለሰብ ሲሆን የአይዲዎሎጂውን ጎራ የሚመሩትና የሚያዙት የሸብር አባላቱ የቡድን አባቶች ደግሞ ካሚል ሸምሱና አህመድ ሙስጠፋ የተባሉት ግለሰቦች  ናቸው፡፡ አቶ አማን አሰፋ(አማን እስማኤል) እንደተናገረው በአጠቃላይ ለሽብር አፈፃፀሙ የሚያመች ቦታ መምረጥ፣የጦር መሳሪያ ማከማቸትና የምሽግ አቆፋፈር ጥበብ ጭምር በአልሸባብ አባላትና በሌሎች አሸባሪዎች ሥልጠና ለእርሱና በእርሱ ስር ለተጠረነፉት አባላቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡

የአይዲዎሎጂውን መስመር የሚመሩት የቡድን አባቶች ካሚል ሸምሱና አህመድ ሙስጠፋ ደግሞ በግብጽ የሥልጣን ማማ ላይ ዥዋዥዌ እየተጫወተ ባለው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲን አስምህሮ በተማሩት ዶክተር ጃሲን ኩዬት ውስጥ ስልጠና ወስደዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ካሚልና አህመድም የጦር ክንፉን ወይም ጂሃዱን እንደሚመራው አማንና የቡድን አባሎቹ አላማቸው የመንግስትን ስልጣንና የቁጥጥር ስርዓት በማዳከምና በማሳካት ከ30 አመትም በኋላ አንኳ ቢሆን የመጨረሻ ግባቸው እስላማዊ መንግስት ማየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የጦር ክንፉ መሪ አማን እስማኤል ወደሸብር ተግባር የገባው በነዳሩ ቢላል ስልጠና ስለተሰጠውና ስለተመረጠ ብቻ ሳይሆን "ጂሃድ የእድሜ ዘመን ተግባሬ ነው ብዬ ከማመኔ የሚጀምር ነው" ሲል በማያወላዳ መንድ ተናግሯል፡፡

በዚሁና የእድሜ ዘመን ተግባሬ ነው ብዬ ከማመኔ የሚጀምር ነው  ባለው መነሻነት አማን አሰፋ ሰለፊያ የተሰኘ ጭማቂ ቤት በአዲስ አበባ ይከፍታል፡፡ በዚህች ጭማቂ ቤት ታዲያ የሚገቡትና የሚወጡት ሁሉ ተግባራቸው ከጠረጴዛ ላይ ያሥቀመጧቸውን ጭማቂዎች የመጠጣትና አንጀታችውን ማራሥ  እንዳልነበር ልታውቁት ይገባል የሚለን የጭማቂ ቤቱ ባለቤት(አማን አሰፋ) በአጠቃላይ ሰለፊያ ጭማቂ ቤት ስለጅሂድና ጅሃዳዊ ጦረኝነት ውይየት የሚደረግባት ክበብ ነች ሲል ገልጾልናል፡፡ አያይዞም ይህቺ ክበብ አባላቱን  ከአልቃይዳ እና ከአልሸባብ ጋር የማገናኘት ስራዋን በብቃት ተወጥታለች ሲልም የሰለፊያን ጭማቂ ቤት የማዘዣ ጣቢያ እና የጦር መረጃ ማእከልነት አስምሮ ይነግረናል፡፡

ይህን ለማሳካትና በንድፉ መሰረት ጂሃዲን ለማሳካት ደግሞ ቀዳሚውና በስኬት መጠናቀቅ ያለበት (ፈንጂ አምካኝ ብለን ወይም ደግሞ መንገድ ጠራጊም ብለን ልንወስደው እንችላለን) የአይዲዎሎጂው ውጊያ ነው።  ስለሆነም ካሚልና አህመድ ከኩዬት ቀስመው የመጡትን መርዛማ ትምህርቶች ለአባሎቻቸው እንዴት ማድረስ አንደሚችሉና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉ በህቡእ  ሲመክሩ ሲዘክሩ እንደነበርና በሲዲ ፣በብሩሸርና መፃህፍት አማካኝነትም ያመጧቸውን  አስተምህሮዎች  ሲያሰራጩ እንደነበር ራሳቸው በ”ጂሃዳዊ ሃረካት” ዘጋቢ ፊልም ላይ አውግተውናል፡፡
እነዚህ እንግዲህን በአወልያው ትምህርት ቤት ውስጥ የተቋቋመውና የሙስሊሞች ጥያቄ አስመላሽ ኮሚቴ ተብሎ በሚታወቀው በአሁን ሰአት ደግሞ በተጠርጣሪነት ተይዘው ጉዳያቸው በነአቡበከር መዝገብ በፍርድ ቤት እየታየ ከሚገኘው 29 ግለሰቦች ጋር ያልተያያዙና ክስ ያልተመሰረተባቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን   ከዘጋቢ ፊልሙ እንደተረዳነው  ክስ ያልተመሰረተባቸውና ከአወልያው ኮሚቴ ውስጥ የሌሉበት የአይዲዎሎጂው ቡድን ጠርናፊዎች እጅ   ከአወልያው ውስጥ መዘርጋቱን እና አወልያ ት/ቤት የነካሚልና አህመድ የሽብር ክንፍ ማእከል የነበረ መሆኑን ነው፡፡
ይህንንም እነ አቡበከርና ኑር ተርኬሎ የተባሉት ግለሰቦች ትምህርት ቤቱን በመጅሊሱ ይውረድልን ሸፋን መረጃ ለማቀባበልና በሰደቃ አስባብ ውይይቶች ለማድረግ መጠቀማቸውን በጂሃዳዊ ሃረካት ላይ አረጋግጠውልናል፡፡ በዚህ ብቻ ያላበቃውና ማእከሉን አወለያው ት/ቤት ያደረገው በነአቡበከር የሚመራ የሚመስለው ኮሚቴ ነገር ግን በነካሚል እና አህመድ የሚሾረው ቡድን ምናልባትም ቀድሞ የሚገባው ስለማይታወቅ በሚል ተተኪ ስለማዘጋጀታቸው ጭምር መሀመድ አህመዲን የተባለንና  በአሁን ሰዓት በሱዳን ቲቪ አፍሪካ በመስራት ላይ የሚገኝን ግለሰብ በዋቢነት ጠቅሰው አቀርበውልናል፡፡

የመጅሊሱ ምርጫን እንደምንም እና የመጨረሻውን መስዋእትነት በመክፈል ወደ መስኪድ በማምጣትም ምልምሎቻቸውን ለማስቀመጥ የበሉ የጠጡትን የመሄዳቸውን ምስጢርም አካፍለውናል፡፡ በእኔ አረዳድ ይህ ነው እንግዲህ የጂሃዳዊ ሃረካት ይዘትና ጭብጥ፡፡ ከዚህ ጭብጥ በመነሳት ቀደም ብለን ወዳነሳናቸው ጥያቄዎች ምላሽ በክፍል ሁለት መጣጥፌ  እንገናኛለን ።