አልቦ ውስጠ ዴሞክራሲያዊነት የወለደው የአንሳተፍም ጩኸት

  • PDF

ዮናስ  (የካቲት 11/2005)

የፅሁፌ ዋነኛ መነሻ በመጪው ሚያዚያ የሚካሄደው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫን ተከትሎ በመድረክ መሪነት የተሰባሰቡት ፓርቲዎች በምርጫው አንሳተፍም ሲሉ የሚያወጧቸው የመግለጫ ጋጋታዎች ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትሎ የገዢው ፓርቲ (ኢህአዴግ) ጽ/ቤት ሃላፊ የሰጡት መግለጫ የፅሁፌ ዋና መነሻ ይሆናል፡፡ ይህንኑ የተቃዋሚዎችን ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በጥልቀት ለመፈተሽ እንዲቻለኝም በዋቢነት የመድረኮቹ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስና እና ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ከአዲስ ጉዳይ መጽሄትና ከኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እመለክታለሁ፡፡

የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን መጪውን የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ አለመሳተፋቸው ለኢህአዴግ አያተርፈውምም አያከስረውምም” የሚል እንደምታ ያለው አስተያዬት ሰንዝረዋል የሚለው ከሰሞኑ የአንዳንድ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቦ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ 

ስለሆነም አቶ ሬድዋን ሁሴን በቀጣዩ የአካባቢ ምርጫ የተቃዋሚዎች አለመሳተፍን ለኢህአዴግ አትራፊም አክሳሪም አይደለም ማለታቸው   በመሰረቱ ስህተት ነው ብዬ ነው የምሰወስደው፡፡ ተቃዋሚዎቹ እንዳሉትም ከእርሳቸው የሚጠበቅ ነው ብዬም አላስብም፡፡ ሆኖም ግን ያሉበት መንገድ የተለየ ትርጉም እንዲኖረው ፈልገው ከሆነስ? የሚል ጥያቄ አነሳለሁ። 
ምንአልባት ይህን ጽሁፍ እሳቸው የማንበብ እድሉን ካገኙና  ቃል በቃል ከላይ የተጠቀሰውን ትርጉም እንዲኖረው ፈልገው ተናግረው ከሆነ ስህተታቸውን ተቀብለው ያርማሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
ካልሆነ ግን ለእኔ የሚመስለኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአካባቢና በአዲስ አበባ ምርጫ ላይ ማንገራገራቸውና አንሳተፍም ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ባልተማከለ አስተዳደርና ፌዴራላዊ ስርዓቱ አማካኝነት ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የተመቻቸውን እድል ለመጠቀም በርካታ እጩ አባላትን መያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በአካባቢ ምርጫ ላይ እስከታችኛው መዋቅር የሚያስፈልጉ ወደ 3 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ እጩ ተወዳዳሪዎችን ማቅረብ ይቅርና በመቶ ሺህ የሚቆጠር አባላትም የሌላቸው በመሆኑ ለመወዳደር አይሹም ለማለት ፈልገው ይመስለኛል፡፡
ይህም ቢሆንና በዚህም ምክንያት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ሂደት ላይ ትርፍና ኪሳራ የላቸውም በተለይም ለኢህአዴግ ካሉ ደግሞ ከባድ ስህተት ይመስለኛል። ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ ነው፡፡ መንግስታችን ደግሞ የሚመራው በኢህአዴግ ነው። ስለሆነምና በተለይም እስከታች የወረደና ህዝብን ያሳተፈ መንግስታዊ ቢሮክራሲ ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ የተቃዋሚዎች በአካባቢ ምርጫ ላይ አለመሳተፍ  ለኢህአዴግም ሆነ ለአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጠቃሚ ነው ብዬ አላስብም ፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖና   የአቶ ሬድዋን  የመግለጫ   መልእክት  ተቀዋሚዎች በተረዱት መንገድ ከሆነ ከስህተታቸው እንዲታረሙ እድል መስጠት አልያም መተቸት ሲገባ ተቃዋሚዎቹ ስለእርሳቸው እየጮኹም ከእርሳቸው  በከፋ ስህተት ውስጥ ተዘፍቀው የመገኘታቸው ምስጢር ቤታቸው  በውስጠ ዴሞክራሲያዊ የነጻነት እጦት   መታመሱን   የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስለሆነም ተቃዋሚዎች ምርጫ በደረሰ ቁጥር  የማላዘናቸው ጉዳይና የመታመሳቸው ምክንያት እራሳቸው እንጂ በምንም መመዘኛ ኢህአዴግ ወይም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ሊሆን አይችልም፡፡
ይህን ሃሳብ ለማጠናከርና በአቶ ሬድዋን ላይ የተጮኸው ጨኸት የለበጣ እና ዝንጀሮ የራሷን . . . ሳታይ መሆኑን የበለጠ ለማረጋገጥ አንድ ወሳኝና ተጨባጭ የሆነ ዋቢ አቀርባለሁ፡፡  ይኸውም ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ከ ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ አቶ ሬድዋን ሁሴን የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊነታቸውን መሰረት አድርገው   የሰጡት መግለጫ እንደሆነው ሁሉ ዶ/ር ነጋሦም አንሳተፍም የሚሉትን ፓርቲዎች የሚመራው መድረክ ሊቀመንበርነታቸውን መሰረት አድርገው ነው ከጋዜጣው ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፡፡ ታዲያ ዶክተሩ ስለመጪው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ በተመለከተ ከኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ምን አሉ?
“በዚህ ምርጫ አለመሳተፋችን አይጎዳንም------ሰውንም በዚህ አይነት ምርጫ ተሳተፉ ብሎ መቀስቀስ የኢህአዴግ ምርጫ አጃቢ ከመሆን ያለፈ ዋጋ ስለሌለው ይህንን አናደርግም፡፡  ስለዚህ አንጎዳም፣ የምንጎዳበትም ምክንያት የለም፤ ይህንንም ህዝቡ ውስጥ ልታይ ትችላለህ፣ ይህንን ስላላደረገ አንድነት ተጎዳ የሚባል ነገር እስካሁን አልሰማንም፡፡”
ዶ/ር ነጋሦ ይህን ያሉት “. . የ1997 ዓ/ም ምርጫ ወቅት ህብረትም ሆነ ቅንጅቶች ሰውን በመጀመሪያ ካርድ አውጡ እያሉ አብረው ይቀሰቅሱ ነበር?” በሚል ኢትዮ ምህዳር ከተሰኘችው  ጋዜጣ ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ነው፡፡
ለዚህ ጥያቄ እንደመድረክ ሊቀመንበርነት የሰጡት አስተያየት እንድምታው ምንድነው? የሚለውን ስንመለከት ዶ/ሩ እና መሰሎቻቸው ሌላ ጊዜ እንደሚለፍፉት ትግላቸው ስለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ስለደሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሳይሆን ስለአንድነት ፓርቲና ፓርቲውን ተንተርሰው ስለሚሹት ስልጣን መሆኑን ነው፡፡
አቶ ሬድዋን ለኢህአዴግ ትርፍና ኪሳራ የለውም ማለታቸው የሚያስጮሃቸው እነመድረክ መቼም ጩኸታቸው የጤነኛ ከሆነ መሳተፋቸው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ከማመን ነው የሚሆነው ። ነገር ግን እሳቸው ላይ እየጮኹ "አንድነት አይጎዳም" ብለው መናገራቸው በራሱ  የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች አይነት ነገር ነው የሆነብኝ፡፡
የሆነ ሆኖ ግን ተቃዋሚዎች በምርጫው ላይ የመሳተፍና ያለመሳተፋቸው ማማካኛ ኢህአዴግ ሳይሆን የራሳቸው ውስጠ ዴሞክራሲያዊ እጦትና በዚሁ የእጦት ዛር የመለከፋቸው ጉዳይ ነው ያልኩበት መሰረታዊ ምክንያቶች ስላሉኝ ነው፡፡
ይኸውም የታቃዋሚዎችን በምርጫ አለመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ  የማይበጅ መሆኑን  የሚያሳዩና እና ነገር ግን በዋናነት የተቃዋሚዎች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን በምርጫ የመሳተፍ ያለመሳተፋቸው ጉዳይ ሳይሆን ተቃዋሚዎች ስለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከምርጫ አስቀድሞ መስራት ያለባቸውና የሚጠበቅባቸው በርካታ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች መኖራቸውንም  የሚያሳዩ   ምክንያቶች ናቸው ያሉኝ፡፡
ተቃዋሚዎች በውስጠ ዴሞክራሲያዊ እጦት ዛር ስለመናጣቸውና ሁሉን አቀፍ በሆነ ውስጣዊ ድክመት ውስጥ የመገኘታቸውን ሚስጥር ለመመልከት ከራሳቸው የሃይል አሰላለፍና ተቋማዊ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ከገዥው ፓርቲ ተቋማዊ ባህልና አሰላለፍ አንፃር መቃኘቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
የተቃዋሚዎች ድክመት የሚጀምረው ሁሉም የፖለቲካ ስርዓቶች ሊሻሻሉ የሚችሉ እንዳልሆኑ ካለመረዳት ነው፡፡ ይህን የፖለቲካ ሀሁ ካለመረዳት በተነሳም ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የተቃዋሚ ሃይሎች የትኩረት አቅጣጫ  መንግስት  መቀየር እንጂ መሬት ላይ ያለውን ፖለቲካዊ ስርዓትና ባህል በመሰረታዊነት መለወጥ አይደለም፡፡
የዚህና ስርዓትን የመቀየር አቅጣጫ አስተሳሰብና ምንጭ የዜሮ ድምር የፖለቲካ ስትራቴጂ ሲሆን ተቃዋሚ ሃይሎች በአሁኑም ወቅት የዚህ ትግል ልማዳዊ አስተሳሰብ ሰለባ ሆነው የመገኘታቸው ጉዳይ ነው የአንሳተፍም፤ እንሳተፋለን አባዜ ውስጥ ሰንቅሯቸው የሚገኘው፡፡
ከምርጫ 97 ጀምሮ የተመለከትኳቸው ተቃዋሚ ሃይሎች ካሳለፉት የፖለቲካ ትግል ልምድ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ያሳለፉትን የትግል አቅጣጫ በአግባቡ ገምግመው ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ለማጠናከርና ደካማ ጎናቸውን ለመቅረፍ ሲሞክሩ አይታዩም፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ አሰራርም የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ ምርጫቸው በየአጋጣሚውና በምርጫ ወቅት ብቻ መጮህና የመግለጫ ጋጋታ ማውጣት መሆኑ ይህ አካሄዳቸው በመሰረታዊነት ስለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ስለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን በየትኛውም መለኪያ ምንም አይነት ፋይዳ አይኖረውም፡፡
በአንፃሩ ኢህአዴግ በምርጫ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ገና ከጠዋቱ ትግሉን ሲጀምር ተቋማዊና ውስጣዊ ድክመቱን አብጠርጥሮ እየነቀሰና እያረመ የተጓዘ ድርጅት ሲሆን ትግሉን በድል ካጠናቀቀና የመንግስትን ስልጣን በእጁ ካስገባ በኋላ ተቋማዊ አሰራሩን የበለጠ እያጠናከረና በየጊዜው እየታደሰ የመጣ በውስጠ ዴሞክራሲያዊ አሰራርም   አርአያ መሆን በሚችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት  አሁን ለተፈጠረችው ኢትዮጵያና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቷ የኢህአዴግ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችን ልክ እንደቀደመው ሃሳቤ ከ1997 ምርጫ ጀምሮ ስመለከታቸው በመርህ ላይ የተመሰረተ የጋራ አጀንዳና ትብብር መፍጠር እንደተሳናቸው ይኸው አሉ፡፡
በግለሰቦች ላይ በተንጠለጠለ፣ በትናንት ቅራኔዎች በተተበተበ፣ በበቀል በተሞላ እና በጭፍን አስተሳሰብ በተደገፈ የተቃወሞ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙት ተቃዋሚዎች በባህሪው ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ አሰራር መከተልና ተቋም መፍጠር ሲገባቸው ምርጫ በደረሰ ቁጥር ሆዴን ቆረጠኝ ማለታቸውና የቤታቸንው ችግር ለኢህአዴግ መስጠታቸው ተገቢነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በመሰረታዊነት እስካልተቀየሩና ከላይ የተጠቀሱቱን መስመሮች እንደመርህ ሳይወሰዱ በምርጫ መሳተፍ አለመሳተፋቸው  ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን የሚኖረው ፋይዳ ቀድሞ ነገር የጨነገፈና የመከነ ነው የሚሆነው።
አንዳንድ ፈረንጅ አምላኪ ለሆኑት የሃገሬ ተቃዋሚዎች ፈረንጅ የፖለቲካ ሳይንቲስት አስረጅ አድርጌ ላቅርብማ። ትሬር ካረቭር ይባላል "Dictatership in History and Theory, Bonapartism, Caesarism, and Totalitarianism"   መጽሃፉ የሃገሬን ተቃዋሚዎችን የትግል ስልት በተመለከተ ያነሳኋቸው እና የማነሳቸውን ጭብጦች የሚያጠናክርልኝ አንድ ነጥብ አስፍሯል።
ማንኛውም ትግል የሃይል እንቅስቃሴን በይበልጥ የሚጠቀም ከሆነ ዴሞክራሲያዊ የመሆን እድሉ በዛውልክ በጣም አናሳ ነው የሚል ነጥብ። ስለሰላማዊ ትግል እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውንነት በተደጋጋሚ በአፋቸው የሚዘምሩት ነገር ግን በተግባር ወጣቱን እና ህዝቡን በተደጋጋሚ ለአመጻ ሲጋብዙ የከረሙት የተቃዋሚ ሃይሎች ግብዣቸው ሲከሽፍ የተናገሩቱ እነዚህ ሃይሎች ፈፅሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እና ስለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቁብም የሌላቸው መሆኑን ያረጋግጥልናል። "አሁን ያለውን ስርዓት ለመታገል የአሁኑ ትውልድ ሃገራዊ ፍቅርም ሆነ ወኔ የለውም" ሲሉ በተደጋጋሚ የመድረክ አመራሮች መናገራቸውን እዚህ ጋር ያስታውሷል ።
ሌላውና የተቃዋሚዎች ከምርጫ የመሸሽ ምክንያት የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ የያ ትወልድ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ ማዕከላዊ አጀንዳ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው።
ይኸውም ተቃዋሚ ሃይሎች ኢትዮጵያዊነትን እና የብሄር ብሄርተኝነትን እንደ ሁለት የተለያዩ ማንነቶች ወስደው አቋም መያዛቸው በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ የብሄር ብሄረሰቦች መብቶችን ከግለሰቦች መብት ጋር ማክበር የሚቻልበትን እድል በመጠቀም ኢትዮጵያዊነትና ብሄር ብሄርተኝነት እንደሁለት የተለያዩ ማንነቶች ሳይሆን ተያይዘው በአንድነት ሊከበሩና ሊገለጹ የሚችሉ የአብሮነታችን አንድም ሁለትም፣ ሁለትም አንድም የሆኑ መብቶች ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ በመጓዙ እና ይህንኑም ፍሬ በተግባር ማረጋገጡ ከተቃዋሚዎቹ ስለ ስልጣን ፍለጋ እንጂ ስለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቁብ ማጣት ጋር ተዳምሮ ለሽሽት እየዳረጋቸው መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ነው።
ሌላውና የተቃዋሚዎችን የምርጫ ዋዜማ ጩኸትና በኢህአዴግ የማላከክ ክፉ ልማድ እያጎለበተ የሚገኘው ከተቃዋሚዎች ድርጅታዊ አደረጃጀትና ድርጅታዊ ስርዓት ጋር በተያያዘ ተቃዋሚዎቹ ያለባቸው ከፍተኛ ድክመት ነው። ይህንኑ ድክመት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ቀደም ብዬ በዋቢነት ካቀረብኩትና ኢትዮ ምህዳር  ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንዲህ ሲሉ ያረጋግጣሉ "በየአመቱ እቅዶች እናወጣለን። በእቅዳችን መሰረት ሰርተናል። ደክመናል ወይስ አልሰራንም የሚለውን እንገመግማለን። በዛ መሰረት ድክመቶቻችንን አይተናል። በተለይ በድርጅት ስራ በኩል አባላትን በማስተባበር ስራ ላይ ድክመት እንዳለብን አይተናል።" ይላሉ።
ታዲያ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መዘወሪያ የሆኑትን የአደረጃጀት ስርዓትና ድርጅታዊ ስራዎች ያመከነ ፓርቲ እንዴትስ ሆኖ ነው ምርጫ ሊሳተፍ የሚያስችለው ቁመና ላይ መድረስ የሚቻለው? ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ ይመስለኛል። እራሱን ያላደራጀና ድርጅታዊ መዋቅሩ የላላ ፓርቲ በምን ምክንያትስ ይሆን ገዢው ፓርቲ ላይ ቢያላክክ ተቀባይነት የሚኖረው? ብሎ መፈተሽም አስፈላጊ ነው።
የሀገሬ ተቃዋሚዎች ምርጫ በደረሰ ቁጥር ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት የውስጥ ችግሮቻቸውን ሁሉ ኢህአዴግ ላይ ስለ ማላከካቸው ሌላም አስረጅ ማቅረብ እንችላለን፡፡
እነዚህ ተቃዋሚዎች ውስጣዊ አቋማቸው የሟሸሸ እና የተፈረካከሰ ነው፡፡ ውስጣዊ አቅሙ ያልተገነባ ተቃዋሚ ሃይል የገዥውን ፓርቲ ድክመቶችና ጥፋቶች እያመለከተ አማራጭ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ መቃወምን ብቻ እንደ ግብ ወሰዶ የሚንቀሳቀስ ሃይል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተጨባጭ በሀገሬ ተቃዋሚዎች ላይ የሚገለጽ ነው፡፡
በሀገሬ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቋማዊ ቅርፃቸው ከግለቦች ስብእና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ እየተስማሙና የሃሳብ ልዩነትን እንደ ተፈጥሯዊ ህግ ሲቀበሉ ተመልክተናቸው አናውቅም፡፡ ዋናው ችግራቸው ግለሰባዊ ስብእና ከፓርቲዎች ህብረተሰባዊ ተቀባይነት በላይ የሆነና ፓርቲዎቹም እንደግለሰባዊ ፓርቲነት የሚታዩበት አግባብ መከተላቸው ነው፡፡ በውስጣቸው የሚታየው የሃሳብ ልዩነት ሳይሆን የግለሰቦች ግላዊ ጥላቻዎች ናቸው፡፡
በተመሳሳይም እርስ በርሳቸው በጠላትነት የመታየታቸው ጉዳይ ነው ከምርጫ የሚያሸሻቸውና የአንሳተፍምን አማራጭ እንዲወስዱ የሚያደርጋቸው እንጂ የገዥው ፓርቲ ተጽእኖ አይደለም፡፡
ለዚህና ለመጠፋፋት አጀንዳቸው ተጨባጭ አስረጅ ለማቅረብ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። ከሰሞኑ ለህትመት ከበቃቸው አዲስ ጉዳይ መጽሄት ጋር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ካደረጉት ምርጫ ነክ ቃለምልልስ እና ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ከኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ጥቂት ነጥቦችን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡
የገዥው ፓርቲ ሃላፊዎች ተቃዋሚዎች ምርጫ በመጣ ቁጥር አንሳተፍም የሚሉት ምንም እንደማይለውጡ ስለገመቱ ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምስክር የ2002 ምርጫ 99.6 በመቶ እንዳሸነፉ ይናገራሉ በማለት መጽሄቱ ለፕ/ሩ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “- - - - በጣም የሚገርመው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በ2002 ምርጫ አንድ ግለሰብ ከመድረክ ውስጥ   አሸንፏል  ማለቱ እስከ ዛሬ የማይገባኝ ነው፡፡ ለምን እንደዚህ አልክ ብለው ያኮረፉኝ የፓርቲዎቼ ሰዎች አሉ፡፡ ስንትና ስንት የዴሞክራሲ አርበኛ ባለበትና ስንት ጊዜ ደጋግመው ያሸነፉ ህዝብ የሚያውቃቸው እያሉ ሁሉንም ተሸንፈዋል ብሎ አንድ ከመርካቶ አካባቢ የተወዳደረን ሰው አሸንፏል ብሎ ማወጅ ያሳፍራል”
ስለ እውነት ለመናገር የሚያሳፍረው የተከበሩ የአቶ ግርማ ሰይፉ ማሸነፍ ነው ወይስ የፕ/ሩ ካለእኛ ማንም የዴሞክራሲ አርበኛ የለም ፤ሊኖርም አይገባም አይነት የትምክህት   አስተያየት ነው፡፡
ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ታቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው ያልተግባቡ በጥላቻና በኩሪፊያ ቤታቸውን የገነቡ በዚህም ለሰው የማይተርፉ ናቸው የምለው፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ከዚህ ቀደምም ሆነ ሰሞኑን በፅ/ቤት ሃላፊው በኩል ምርጫ ላይ አወሩም አላወሩ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሌላቸው በመሆኑ ለውጥ አያመጡም ሲል የሚከራከረው፡፡
ፕ/ሩ ሌላም አሳፋሪ ነገር በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው አንስተዋል። ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር በአንድ ወቅት ባህርዳር ከተማ ላይ  በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተገናኝተን ነገሩኝ ያሉትን   በማንሳት "በእኔ የትውልድ ስፍራ ካለ እኔ ማንም እንደማያሸንፍ መስክረውልኛል" ሲሉ የጅል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ 
ለነገሩ ህብረት የተባለው ፓርቲ ለፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የግላቸው ኩባንያ እስኪመስል ድረስ “ህዝቤ” በማለት መናገር ከጀመሩ የቆዩ ቢሆንም አሁን ድረስ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ተነክረው የመቆየታቸው ጉዳይ ያሳፍራል፡፡ 
ስለሆም ነው በምርጫ ወቅት ከማላዘን አስቀድሞ ተቃዋሚዎች ያልጨረሱትን የቤት ስራ መጨረስ አለባቸው ሲል ኢህአዴግ የሚከራከረው፡፡ 
ወደ ዶ/ር ነጋሦ ስንመጣ የምናገኘውም ከፕ/ሩ ተመሳሳይና የጥላቻ፣ የመጠላለፍና የኩርፊያ ፖለቲካቸውን ነው።
ዶ/ር ነጋሦ ከኦፌዴኑ  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ጋር በአንድ አፍ እንናገራለን፣ በአንድ ትሪም እንበላለን እንዳላሉት ሁሉ አቶ ቡልቻ የወቅቱን ፖለቲካ በተመለከተ የሰጡትን ነፃ አስተያየት ተንተርሰው ፕ/ሩ የተከበሩ አቶ ግርማን እንደወረዱባቸውና ከኢህአዴግ ጋር እንዳጠጋጓቸው ሁሉ ዶ/ር ነጋሦም በተመሳሳይ አቶ ቡልቻ ላይ በኢትዮ ምህዳር ዘምተውባቸዋል፡፡
ስለሆነም እላይ በተጠቀሱት መከራከሪያዎችና ጭብጦች መነሻነት የተቃዋሚዎች በምርጫ መሳተፍም ሆነ አለመሰተፍ  ለእኔ አያሳስበኝም ፤የሚያሳስበኝ  ከላይ የተጠቀሱትን እና እና ሌሎቹንም ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚበጁትን የቤት ስራዎች አለማጠናቀቃቸው ነው።