‹‹ለጋሼ የተፃፈ ግልፅ ደብዳቤ›› (ክፍል ሁለት)

  • PDF

አሜን ተፈሪ (የካቲት 11/2005)
ጋሼ፤
የምርጫ ፖለቲካ ዕድገቱን ወይም ጉድለቱን ከስርዓቱ ተዋናይ ኃይሎች ጋር በማያያዝ ለማየት ስሞክር ከአንድ- ከሁለት ወር በፊት የሆነ ጉዳይ ማንሳት እወዳለሁ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ›› የሚል እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን፤ እንዲሁም የሲቪል ማህበራትን ይዞ፤ በምርጫ ዋዜማ ብቅ አለ፡፡ የዚህ ድርጅት አመራር በአሜሪካ ድምፅ ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት፤ የስብስቡን ዓላማ አስተዋወቀን፡፡ ሸንጎው ዓላማዬ ያለው ‹‹የኢትየጵያ ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ነው፡፡›› ማለፊያ ነው፡፡ ግን የሸንጎ ጥንቅር ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጠንቅ የሚሆን ነገር ያለው ነው፡፡
እርግጥ ነው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ፤ በፈለገው ዓላማ ዙሪያ መደራጀት ይችላል፡፡ ግን ይችላል ሲባል፤ በሁሉም ሀገር፣ በሁሉም ዘመን፣ በሁሉም ሀገር ይህ መብት ይከበራል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህ ከእኛ ከኢትዮጵያ ህዝቦች የላቀ ምስክር ሊሆን የሚችል የለም፡፡ እንኳን በፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ መሰባሰብ፤ በሱቅ በር ላይ ሦስት-አራት ሆኖ ሰብሰብ ብሎ መቆም አደጋ የሚጎትት ድርጊት እንደ ነበር ለመዘንጋት ገና አልደረስንም፡፡ ‹‹በፈለጉት ዓላማ ዙሪያ የመሰባሰብ እና የመደራጀት መብት የሚከበረው፤ ዲሞክራሲያዊ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓት በሰፈነበት አገር ነው፡፡›› እናም በተጠቀሰው ዓላማ ዙሪያ የመደራጀት መብት፤ በእኛም አገር ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያገኘ መብት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ›› የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪል ማህበራትን ያቀፈው ሸንጎ፤ በውጭ ሀገርም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢቋቋም ከልካይ የለውም፡፡
በነገራችን ላይ፤ ከዚህ ቀደም ‹‹የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት የጋራ መድረክ›› የሚል እና ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሠረተ ነው›› የተባለ፤ መድረክ በኢትዮጵያ ተመስርቶ ነበር፡፡ የዚህ ‹‹ዓለም አቀፍ የጋራ መድረክ›› የኢትየጵያ አስተባባሪ የነበሩት ደግሞ አንዳንዶች ‹‹አንጋፋው›› የሚል ቅፅል አክለው የሚጠሩት ‹‹የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር›› ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታየ ወ/ሰማያት ነበሩ፡፡ ዶ/ር ታየ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት የጋራ መድረክ››ን ዓላማ እና እንቅስቃሴ አስመልክተው በወቅቱ (1997) ሲናገሩ፤ የሲቪል ማህበራት፤ በፖለቲካ ባህል ዕድገት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው እና ‹‹መካከለኛ ድልድይ ሆነው መንግስትና ህዝብን የሚያገናኙ ናቸው›› ብለው ነበር፡፡
የአባሎቻቸውን ጥቅም የማስከበር ዓላማ ይዘው የሚቋቋሙት የሙያ እና የብዙሃን ማህበራት፤ ለዲሞክራሲ ስርዓት መዳበር ልዩ ሚና እንዳላቸው፤ ሥልጣን ለመያዝ የሚሻሙ እንዳልሆኑ፤ ይልቅስ ‹‹የፖለቲካ ውዝግብ ተፈጥሮ በሁለት ኃይሎች መካከል ሥምምነት ጠፍቶ ውጥረት በሚነግስበት ጊዜ በመሀል ገብተው የማስማማት ሚና የሚጫወቱት የሲቪክ ማህበራት መሆናቸውን፤ እነዚህ ኃይሎች የተፈጥሮ ሚናቸውን እና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጠናከር ገንቢ አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችሉት ራሳቸውን ከፖለቲካ ኃይሎች ነፃ ማድረግ ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ገልፀው ነበር፡፡ በወቅቱ እርሳቸው የሚመሩት መድረክ በዚህ ረገድ ቢመዘን ደረጃው ዝቅተኛ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ግን ቢያንስ ‹‹የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረኩ አባላት ናቸው›› ከማለት ለመጠበቅ ዕውቀት ጎድሏቸው አልታየም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ›› የተባለው ድርጅት ግን ‹‹ሸንጎው የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪል ማህበራትን ያቀፈ›› መሆኑን ሳያቅማማ ነግሮናል፡፡ ይህ ድርጅት ገና ከመነሻው የተሳሳሰተ አቋም መያዙን እንኳን ልብ አላለም፡፡ እንዲህ ያለ የሃሳብ መሳከር ካለ የድርጊት መሳከርን ያስከትላል፡፡ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት ዕድገት የሚገቱ እንዲህ ያሉ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡
ጋሼ፤
‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ›› እንደ ዓላማ የያዘው ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው፡፡›› ጥሩ ነው፡፡ ግን ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የማድረግ ጥረት ከህገ መንግስት ይጀምራል ለምሣሌ፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት በአንቀፅ 8 (1)፤ ‹‹የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው›› ይላል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ‹‹ህዝቡን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ እታገላለሁ›› ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለውን ‹‹ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ›› ብዬ ልለፈው፡፡ ነገር ግን የሲቪክ ማህበራት እንዲህ ዓይነት ዓላማ ካለው ሸንጎ ጋር መሰባሰባቸው ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው በሽታ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ልብ በል፡፡
የዲሞክራሲ ስርዓትን በሀገራችን ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት በዲሞክሲያዊ አኳኋን መመስረት፣ በዲሞክራሲያዊ አግባብ መሥራት እና መደራጀት ይኖርበታል፡፡ ሦስቱ የመንግስት አካላት በስርዓቱ ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና በአግባቡ እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት በህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ በሚከናወን ምርጫ ተመርጦ፤ የመንግስት አካላት ሚና ባልተደበላለቀ እና አንዱ ሌላኛውን በአግባቡ መቆጣጠር በሚችልበት ሁኔታ መደራጀት አለበት፡፡ የህግ የበላይነት የተከበረበት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል፤ የግለሰብና የቡድን መብቶች እና ነፃነቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ የማድረግ ባህርያዊ ይዘት ያለው ሆኖ መዋቀር አለበት፡፡ ታዲያ ይህን ለማድረግ የሚያስችል እና ዘመናዊ የሆነ፤ አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ይዞ የተቀረፀ ተራማጅ ህገ መንግስት አለን፡፡
በዚህ ህገ መንግስት ላይ ተመስርተው የተደራጁ የተለያዩ የዲሞክራሲ ተቋማት እና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ እና መጠናከር የላቀ ሚና ያላቸው የህዝብ ማህበራት እና ተቋማት በነፃነት መደራጀት የሚችሉበት ሁኔታ በህገ መንግስቱ ተመቻችቷል፡፡ በዚህ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያ፣ የሙያ ማህበራት እና የብዙሃን ማህበራት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት እና ማህበራት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ማረጋገጥን እንደ አንድ መሠረታዊ መርሆ በሚወስደው የሀገራችን ህገ መንግስት ተፈላጊ ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዓላማችን መሳካት እና የስርዓቱን ተቋማዊ መሠረት ለማስፋት የሚያስችሉ ሁነኛ ተቋማት ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ ድርጅቶች እና ተቋማት በዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ተገቢ ድርሻቸውንና ሊያበረክቱ የሚችሉት፤ ‹‹ሸንጎው›› ከተመለከትነው በሽታ ተጠብቀው፤ የጋራ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት እና እምነት ይዘው ሲገኙ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ በሀገራችን የሚታየው ክፍተት ሰፊ ነው፡፡ የህልውናቸው መሠረት እና ዋስትና የሆነውን ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት እና በህገ መንግስቱ መሠረት የተቋቋሙ የመንግስት ተቋማትን እንደ ህጋዊ ተቋማት ከመቀበል የማይነሱ በመሆናቸው፤ አቋማቸው እና ሥራቸው ፀረ- ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የሚታይበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሂደት መሻሻል ያሳዩበትን አንዳንድ ነጥቦች መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም፤ መሠረታዊ የሚባል ለውጥ ማሳየት አልቻሉም፡፡ በዚሁ መጠን ለዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጠናከር ያላቸው ሚና ደካማ ሆኗል፡፡
ጋሼ፤
አሁን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንመልከት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወክሉትን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጭ ሐሳቦችን በማመንጨት፤ ሐሳቦቹ በሚወክሉት የህብረተሰብ ክፍል እና በአጠቃላይ ህዝቡ ተቀባይነት እንዲያገኙ በመጣር፤ ሐሳቦቹ በዲሞክራሲያዊ አኳኋን ተግባራዊ እንዲሆኑ በመታገል ከፍተኛ የአመራር ሚና መጫወት የሚችሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚወክሉት ህዝብ ብቃት ያለው አመራር በመስጠት በዲሞክራሲያዊ አኳኋን መብትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚችሉትበትን ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር፤ ዜጎች የተተነተኑ ሀሳቦችን ይዘው በዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ፤ሰፊ እና የነቃ ተሳትፎ እንዲሆን ለማድረገግ ይችላሉ፡፡
በዚህ መልክ የተደራጀ አመራር በመስጠት የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ከቻሉ የመንገግስት ሥልጣን ይዘው ሃሳባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉትን ዕድል ያገኛሉ፡፡ ሆኖም ይህን ዕድል ማግኘት የሚችሉት በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሲገነባ መሆኑንና ለስርዓቱ መጠናከር እነሱም የላቀ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ረገድ ትልቅ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መምህራን እና ግንባር ቀደም ተዋናይ ተደርገው የሚታሰቡ ቢሆንም ይህን ሚና በአግባቡ መጫወት አለመቻላቸው በግልፅ ይታያል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከላይ የተጠቀሰውን ሚናቸውን ለመጫወት የሚችሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ፤ አንድ የፖለቲካ ዓላማ ለማራመድ፤ በኣላማቸው ዙሪያ ለመሰባሰብ የሚፈለጉትን ዜጎች በሙሉ ለማሰባሰብ የሚጥሩ መነሻ እና መድረሻቸውም ይኸው የፖለቲካ ዓላማ ሆኖ የተደራጁ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ፤ ዓላማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችንም ለመተንተን፣ ለማቀናበር፣ ለህዝብ የማቅረብ አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ቁመና ስንገመግም፤ እንደዚህ ዓይነቱን የፖለቲካ አመራር ለመስጠት የማይችሉ በመሆናቸው የፖለቲካ ፓርቲ መባል የሚበዛባቸው ወይም ተልዕኳቸውን በአግባቡ ለመወጣት የማይችሉ ፓርቲዎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ጋሼ፤
ይህን ለማለት የደፈርኩት፤ የፓርቲዎቹ አመለካከት እና አሰራር ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን በማጤን ነው፡፡ ታዲያ የውስጥ አሰራሩ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር ምን የሚበጅ ነገር ሊፈይድ ይችላል? ፓርቲዎቹ፤ የመንግስትን አሰራር ተከታትለው ድክመቶቹን በማጋለጥ ለመልካም አስተዳደር መስፈን መስራት የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር የሚረዳ ቁመና እና አፈፃፀም የላቸውም፡፡ በመሆኑም፤ ገዢው ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ታማኝ ባይሆንና ለፀረ-ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴያቸው ምላሽ ለመስጠት በማሰብ የሚሰራ ቢሆን ኖሮ ጉዟችን የኋሊት በሆነ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች በየጊዜው የሚመሰረቱት ህብረት ወይም ቅንጅት በየጊዜው እየተፈረካከሰ፤ ሰኞ የመሰረቱት ህብረት ማክሰኞ እየፈረሰ፤ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም ጭምር ግራ እየተጋቡ፤ በዛው መጠን የሚወክሉትን ህብረተሰብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እያዳከሙና ተስፋ እያስቆረጡት ተጉዘዋል፡፡ በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት በአገሪቱ (በፌዴራልና በክልል ደረጃ) የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር 90 የሚደርስ ቢሆንም ህልቆ መሳፍርት በሌለው ችግር የተተበተቡ፤ ከምርጫ ቦርድ ከወሰዱት የህጋዊነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት በዘለለ የፖለቲካ ፓርቲ አቋም የሌላቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ለወጉ እንኳን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዕቅድ፣ የመተዳደሪያ ደንብና ማኒፌስቶም፣ የሌላቸው ናቸው፡፡ የፓርቲ መዋቅራዊ አደረጃጀትና፣ ቢሮም የሌላቸው ናቸው፡፡ ጎላ ብለው የሚታዩትም በስልጣን ሽኩቻ የሚታመሱ፤ ድርጅቱን ለበርካታ ዓመታት በመሩና የረባ ውጤት ማስመዝገብ በተሳናቸውና ተጨባጭ የአመራር ብቃት በሌላቸው ግለሰቦች በአፅመ ርስትነት የተያዙ ናቸው፡፡ በመካከላቸው ሰፊ ገደል ተጋርጦ፤ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የዓላማ አንድነትም ሳይኖራቸው፤ በተቃርኖ እንደተጠላለፉ የሚራኮቱ፤ ጠንካራ የፓርቲ አሰራርና አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ የተሳናቸው ‹‹ከርሞ ጥጃ›› የሆኑ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች›› ናቸው፡፡ ድምፃቸው የሚሰማውም በምርጫ ሰሞን ብቻ ነው፡፡ በአጭሩ በየጊዜው የህዝብ አመኔታ እያጡ የመጡ ናቸው፡፡
ጋሼ፤
መሪዎቹም ይፋ የወጣ ፊውዳላዊ ባህርይ የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡ ለሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ትግል ጠንቅ የሆነ ስብዕና ያላቸውም ናቸው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማብቂያ በሌለው የፖለቲካ ክስረት አዙሪት ውስጥ እየተዘፈቁና የህዝብ ድጋፍም እያጡ ህዝባዊ ስብሰባ ሲጠሩ ባዶ አዳራሽ ይዘው ታቅፈው የሚቀመጡ ሆነዋል፡፡ በውጭም ሆነ በውስጥ የሚገኘው አባልና ደጋፊዎች ድጋፍ እየነፈጓቸው በሞትና በህይወት መካከል የወደቁ ሆነዋል፡፡ ወትሮም ቢሆን በሀገር ውስጥ የሚገኘውን ህዝብ እንደ ሁለተኛ ቆጥረው፤ ከኤምባሲዎችና ውጭ ሀገር ከሚኖሩ አባላትና ደጋፊዎች (ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ) ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ናቸው፡፡ በቅርብ ሆኖ ድርጅታዊ ይዞታቸውን የማየትና የመመዘን ዕድል በሌለው፤ ስለ ሀገሪቱም ተጨባጭና የተሟላ መረጃ ከሌለው ዲያስፖራ ያገኙት የነበረው ድጋፍም ቀረ፡፡ ሲቸግራቸው ፊታቸውን ወደ ውስጥ ቢመልሱም የህዝብ ድጋፍ ማግኘት የማይችሉ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የታየው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዞ የውድቀት እንጂ የስኬት ታሪክ የተመዘገበበት አይደለም፡፡ የትግል ስልታቸው በዴሞክራዊያዊ ስርዓት እሴቶች ያልተመሰረተ፤ ዓላማቸውንም በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማሳካት ቆርጠው የገቡ ባለመሆናቸው፤ ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብና መጠናከር የነበራቸው ሚና አፍራሽ እንደሆነ ዘልቋል፡፡
ከህገ-ወጥ ተግባራት ለመጠበቅ ሰላማዊ፣ ህጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ የትግል መርህን ሳያወላውሉ ለመከተል የሚያስችል ዝግጁነት ወይም እምነት ስላልያዙ፤ በየጊዜው የወንጀል ክስ እየቀረበባቸው በፍ/ቤት ውሳኔ ወህኒ እየወረዱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ ያለባቸውን ችግር መለስ ብለው ለማየትና አባሎቻቸውን ከህገ - ወጥ አድራጎት ጠብቀው ለመንቀሳቀስ ፈፅሞ ዝግጁዎች  ባለመሆናቸው፤ ጉዳዩን የመንግሥት የፖለቲካ እርምጃ አድርጎ በማቅረብ ሊገኝ የሚችልን ተራ የፕሮፓጋንዳ የፖለቲካ ፍርፋሪ ከመለቃቀም ለመውጣትና ለስኬት የሚያግዝ ጎዳና ለመከተል አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጠናከርና ማበብ ሳይሆን፤ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች፣ ለህግ የበላይነትና ለህገ-መንግሥታዊ ስርዓቱ ጠንቅ በሚሆን አሰራር ውስጥ ተዘፍቀው፤ ህልውናቸው በመንግስት ምህረት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ጋሼ፤
ይህ ችግር የገዥውን ፓርቲ ኃላፊነትና ሥራ እጅግ አክብዶበታል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የህብረተሰቡን ክፍሎች የተደራጀና የተተነተነ አቋምና ጥቅም የሚያራምዱና አቀናብረው የሚያቀርቡ ባለመሆናቸው፤ መንግሥት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄ ለመረዳት ተጨማሪ ጥረት ለማድረግ የሚገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የፓርቲዎቹ መድረኮች፤ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ እሴቶችና አሰራሮች እየተካኑ የሚወጡባቸው አልሆኑም፡፡ ይልቅስ፤ ለፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና አሰራር የሚጋለጡ መድረኮች ሆነዋል፡፡ በዚህም የተነሳ፤ ለአንድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር ዋስትና የሚሆን የጋራ እምነትና አመለካከት እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ አስተዋፅዖ  አላደረጉም ማለት ይቻላል፡፡ ይልቅ ይህ አመለካከት እንዳይፈጠር እንቅፋት የመሆን የጎላ ሚና ነበራቸው፡፡
ሌላው ቀርቶ፤ የሃገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት በሚመለከት ወሳኝ ጉዳይ ላይ እንኳን በልዩነት አቋም ሲይዙ የሚታዩ ናቸው፡፡ ከዚህም አልፈው መሳሪያ አንስተው ህገ-መንግስታዊውን ስርዓት ለመጣል ጦርነት ካወጁ ወገኖች ጋር ግልፅና ስውር ትብብር ከማድረግ የማይታቀቡ ናቸው፡፡ አገራችንን ለማመስ ምሎ ከተገዘተው የኤርትራ መንግሥት ጋር በመተባበር ከመስራት ወደ ኋላ እንደማይሉም እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ለህግ የበላይነት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር ለመሥራት የሚያስችል የአመለካከት ጥሪት መያዝ ያልቻሉ ናቸው፡፡ በውስጣዊ አሰራራቸውም ዴሞክራሲያዊ አሰራርን እያዳበሩ አልመጡም፡፡
በውስጥ አሰራሩ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከዜሮ ፈቀቅ የሚል አይሆንም ለዴሞክራሲያዊ ባህል ማዳበር የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ የማይሆን ፓርቲ፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ አይችልም፡፡ የስርዓቱ ምሰሶ በሆኑ እሴቶች ዙሪያ የጋራ አመለካከትና እምነት እንዲፈጠር፤ በፓርቲዎች መካከልም ጤናማ ግንኙነት እንዲመሰረትና ስርዓቱ እንዲጠናከር የሚያደርግ ሥራ ሊሰራ አይችልም፡፡ ይህም መንግሥት በሚመራባቸው መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ የሚነሳው የአቋም ልዩነት ሰፊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልዩነት በስርዓቱ መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ እናም ባለፉት ዓመታት በተደረገው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት  ግንባታ ጉዞ፤ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዳላቸው ሀገሮች፤ የተለየ የፖሊሲ አማራጭ በማቅረብ የገዥው ፓርቲ ተፎካካሪ የመሆን አዝማሚያ የያዘ ታማኝ ተቃዋሚ (ሎያል ኦፖዚሽን) ማየት አልቻልንም፡፡ እናም ጎላ ብለው የሚታዩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስርዓቱን የሚንድ ሃሳብና ተግባር ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ በመሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ አንድ የጋራ አገራዊ አመለካከትና እምነት እንዲፈጥር በማድረግ ረገድ የተቃዋሚዎች ሚና አፍራሽ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በመሆኑም የምርጫ ፉክክሩ፤ የጋራ አገራዊ አመለካከት በያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውድድር ሳይሆን፤ ለመጠፋፋት ዝግጁ በሆኑ ድርጅቶች መካከል የሚካሄድ፤ ፉክክር ሆኖ ይታያል፡፡ ስለሆነም ምርጫው ውጥረት የነገሰበት ይሆናል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል የሚያደርገው የሃሳብ ትግል፤ አማራጭ ፖሊሲን በመተንተን የተወሰነ ሳይሆን፤ ከዚህ ውጭ በራሱ በምርጫውና በምርጫ አስፈፃሚው፤ ህግን የጣሰ አካሄድ ተከትለሃል አልተከተልኩም በሚሉ አጀንዳዎች ላይ እሰጥ - አገባ የሚያደርግበት ሆኗል፡፡ ታማኝ ተቃዋሚ የሚባል ነገር የሌለበትና ተቃዋሚ መሆን ማለት መናድ፣ማፍረስ፣ በተገኘው አጋጣሚና ባመቸ ስልት በመጠቀም የሚቀናቀኑትን ድርጅት፣ ግለሰብ፣ መንግሥት በመዘርጠጥና በማደናቀፍ የተወጠረ ሂደት ይሆናል፡፡ አንዳንዴም የምርጫ ሂደቱ በዴሞክራሲያዊ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች መካከል የሚካሄድ ትግል ሆኖ ይታያል፡፡ ስለሆነም፤ የሀገራችን የምርጫ ፖለቲካ መድረክ ህገ-መንግስቱን እና በህገ-መንግሥቱ መሰረት የተቋቋሙ የመንግሥት አካላትን ህጋዊነት መቀበል የማይፈልጉ ተቃዋሚዎች የሚራኮቱበት ሆኗል፡፡
ጋሼ፤
እኔ የሚገርመኝ ህገ - መንግሥቱን መሰረት አድርገው የተቋቋሙት ፓርቲዎች፤ ህጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥላቸውን፣ በደል ደረሰብኝ ሲሉም አቤቱታ የሚያቀርቡትን እንደ ምርጫ ቦርድ ያለ ተቋም፤ እንዲሁም ጭምር ፍ/ቤቶችን አንቀበልም እያሉ፤ ተቋማቱንም በይፋ እያወገዙ በስርዓቱ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እናያለን፡፡ ይህ አካሄድ ፓርቲዎቹ ስለ ስርዓቱ የጠራ ግንዛቤ እንደሌላቸው፤ የስርዓቱንም ባህርይ የመረዳት ችግር እንዳለባቸው ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ እነሱንም መምታታት ውስጥ የሚከታቸው ነው፡፡ ሥራቸውንም የጅል ስራ የሚያደርግ ነው፡፡ በጠራ የስርዓት አረዳድ ላይ ተመስርተው እንዳልተነሱ የሚያጋልጥ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በህብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ በቆየው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህል እየታገዘ ትርጉም ያለው አቋም መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ግን የስርዓቱን ዕድገት የሚያቀጭጭ መጥፎ ችግር ነው፡፡
አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለስርዓቱ መሠረት የሆነውን ህገ-መንግሥት እና ህገ-መንግሥቱን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ገለልተኛ ተቋማትን ህጋዊነት ለመቀበል ከተቸገረ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል ለማድረግ የሚያስችለው ሁኔታ አልተሟላለትም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የሰላማዊ ትግል መድረኩ ተዋናይ ለመሆን የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ምርጫው ሌላ መሆን አለበት፡፡ ይህን የማልደግፈው ቢሆንም፤ ግራ የሚያጋባ አቋም አይሆንብኝም፡፡ አሁን ግን በጣም ግራ ያጋቡኛል፡፡
ጋሼ፤
እንደኔ አስተያየት፤ የፖለቲካ ፓርቲ በሚል ለመደራጀት በቻሉበት፤ አማራጭ የሚሉትን ሃሳባቸውን አስተዋውቀው አባላትን በዓላማቸው ዙሪያ ለማሰባሰብ በበቁበት፤ በምርጫ ለመወዳደር ቀርበው ሃሳባቸውን ለመራጩ ህዝብ ለመግለፅ በቻሉበት ሁኔታ፤ አለ የሚሉትን ጉድለት በሚያደርጉት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለማሟላት ቆርጠው በመነሳት፤ ብልሹ አሰራሮችን በተጨባጭ ማስረጃ እያስደገፉ በማጋለጥ፤ የሚሻሻሉበትን አቅጣጫ በመጠቆም ችግሮቹ የሚቀረፉበትን መንገድ ለመሻት በተለያየ አግባብ መሞከርና ገዢው ፓርቲ ያለ ፖለቲካዊ ኪሳራ ጥያቄያቸውን ገሸሽ ለማድረግ በማይችልበት አኳኋን ግፊት እያደረጉ፤ ሳያሰልሱ ጥረት ማድረግ እንጂ፤ ህገ - መንግሥቱንና የመንግስት የተቋማትን ህጋዊነት አልቀበልም ማለት፤ ህገ-ወጥ አቋም ይሆናል፡፡ በተግባር ህጋዊነቱን እየመሰከሩ በቃል ህጋዊነቱን አልቀበልም ማለት ዳር ቆሞ ለሚያይ ሰው ግራ አጋቢ ይሆናል፡፡ እናም በዚህ አይነት አቋም በሥርዓቱ ውስጥ የጎላ አስተዋፅኦ ማድረግ አይቻልም፡፡ እናም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሳዩት ዕድገት ወይም መሻሻል ዕድሜያቸውን የሚመጥን አይደለም፡፡
ጋሼ፤
በተቃራኒው፤ ገዢው ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸውን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሚዲያ፣መንግሥት፣የሙያና የብዙሃን ማህበራት ባሉ ተቋማት ውስጥ ያለው ውሱንነት ምን እንደሆነ በመለየት ለችግሮቹ መፍትሄ ለማበጀት በጠራ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ አቅጣጫ ቀይሷል፡፡ ስለ ችግሮቹም በፖሊሲ ሰነዶቹ ገልጾዋል፡፡ ጥቂቶቹን ልጥቀስልህ፡፡ ለምሳሌ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ አሉ የሚላቸውን ችግሮች ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ይላል፤ ‹‹አንዳንድ ወገኖች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታዩ ችግሮችን በመጥቀስ እንደኛ ባሉ አገሮች ውስጥ ዴሞክራሲ ብሎ ነገር ልማትን የሚያጓትትና ከንቱ ንትርክን የሚያባብስ ነገር አድርገው የሚያቀርቡት ክርክር ፍፁም የተሳሳተ ነው›› ይልና፤ አያይዞ፤ ‹‹ነባራዊ ችግሮቹ፤ እንደኛ ባሉ ሀገሮች ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊኖሩ ወይም የዴሞክራሲ ስርዓት ሊገነባ እንደማይችል የሚያመለክቱ አይደሉም›› የሚል ግልፅ አቋም ይዟል፡፡
ይህ አቋም የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አስመልክቶ የሚይዘውን አቋምና አጠቃላይ አመለካከቱን የሚቃኝ፤ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር፤ ለሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር በር ከፋች ባለ ሰፊ ራዕይ አመለካከት ነው፡፡ ከዚህ አመለካከት ባይነሳ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ፤ በተገኘው አጋጣሚ እና ባመቸው ስልት በመጠቀም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ዕድገት የማደናቀፍ ተግባር ውስጥ መዘፈቁ የማይቀር ይሆናል፡፡
በተለይ አሁን ባለው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አያያዝ፤ ህገ - መንግሥቱን አንቀበልም ከማለት አንስቶ ስርዓቱን በጦር መሳሪያ ለማፍረስ ከተነሳ ኃይል ጋር እስከማበርና በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ የተቃጣ ጥቃትን ለመመከት ዝግጁ ያለመሆን ችግር ሁሉ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማስተናገድ ለመንግስት ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን ለመገንዘብ ቀላል ነው፡፡ ይህም የሀገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዴት እንደሚጎዳው ለመረዳት አይከብድም፡፡
ሆኖም ገዢው ፓርቲ፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ የሚታየውን ችግር፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጠንቅ መሆኑን ሳይክድ ነባራዊ ችግሩን አጢኖ የወሰደው አቋም፤ እንደኛ ባሉ ሀገሮች ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፍጠርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት አይቻልም የሚል ሳይሆን ‹‹ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፍጠርና ዴሞክራሲን የመገንባት ስራው ከፍተኛ ትግልና ጥረት፤ ከፍተኛ ጥንቃቄና ብቃት ያለው የአፈፃፀም ስልትን የሚጠይቅ ስራ መሆኑን ነው›› የሚል ነው፡፡
መንግስት (ገዢው ፓርቲ) የዲሞክራሲያዊ ስርዓታችንን መዋቅራዊ ችግሮች ለይቶ አውጥቷል፡፡ በዚህም በዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ላይ የሚጋረጠውን አደጋ አውቆ፤ ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን አቋም ወስዷል፡፡ ከነዚህ አንዱ መዋቅራዊ ችግር ከህብረተሰቡ አወቃቀር ጋር የተያዘ ነው፡፡ ከህዝባችን ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል አርሶ አደር መሆኑ፤ ይህ የህብረተሰብ ክፍል በቂ ትምህርት የሌለውና በተበታተነ አኳኋን የሚኖር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አርሶ አደሩ በስርዓቱ ላይ በሚኖረው ሚና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ይህ አንድ የመዋቅራዊ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ እናም በዚህ የህብረተሰብ ክፍል ሰፊ ተቀባይነት ያለው ድርጅት ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆን ሌላ ድርጅት የሚፈጠርበት ዕድል አይኖርም፡፡
ይህ ድርጅት በስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይዞ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ዕድል አለው፡፡ ታዲያ ይህ ድርጅት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከባህሪይው የመነጨ ታማኝነት ከሌለው በቀር፤ በቂ ትምህርት የሌለውንና ተበታትኖ የሚኖረውን አርሶ/አርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍል ለማግኘት እስከቻለ ድረስ ዴሞክራሲያዊ ባህርይውን በመቆጣጠር ሊያርቀው አይችልም፡፡ በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ያለው አንዱ ችግር ይኸው ነው፡፡
በሌላ በኩል ሌሎች ድርጅቶች በጠባብ የህብረተሰብ ክፍል የታጠሩና ደካማ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል ይኖራል፡፡ በመሆኑም ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት አንፃር የአርሶ አደሩን ሰፊ ድጋፍ ያለው የፖለቲካ ፓርቲም የማይነቃነቅ ሆኖ መቆም የሚችልበት፤ ሌሎቹ ደግሞ በጠባብ የህብረተሰብ መሰረት ላይ የቆሙ ደካማ የሚሆኑበት ሁኔታ ሁለቱም ለስርዓቱ መጠናከር በሚኖራቸው ሚና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል፡፡
እንደኛ ባሉ አርሶ አደር ህብረተሰብ ላይ የቆሙ ዴሞክራሲዎች በተለያየ አጋጣሚና መልክ ሲከሰቱ አይተናል፡፡ ይህ መዋቅራዊ ችግር በተለይ በአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ውስጥ በከፋ መልክ የሚገለፅ ይሆናል፡፡ የአርብቶ አደሩ ማህበራዊ አወቃቀር በደም ትስስርና በጎሳ ላይ የሚያጠነጥን ስለሚሆን ሰዎች በፖለቲካ አመለካከት ዙሪያ ፓርቲዎችን የማቋቋም ዕድላቸው ጠባብ ይሆናል፡፡ የሚቋቋሙት ፓርቲዎች በመሰረቱ የጎሳና የቤተሰብ ስብስብ ስለሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት የሚያስብል ባህሪይ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ኋላ ቀርና ድሃ በሆኑ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የግል ባለሃብቶቹም ደካሞች ናቸው፡፡ እጅግ ኋላቀር በሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ የሚገኙት እጅግ ደካማ የሆኑ ባለሃብቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ብቃትና ፍላጎትም አይኖራቸውም ስለዚህ ለመክበር ቀላሉና አቋራጩ መንገድ ከመንግሥት ጋር በሚፈጠር ሽርክና፣ በሙስና እና በህገ-ወጥ መንገድ በሚሰራ የንግድ ስራ በመሰማራት ነው፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ከአምራችነት ይልቅ ለጥገኝነት የተመቸ ሁኔታ መኖሩ ተደማምረው የመንግሥት ስልጣን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ መቆጣጠር ሃብት የማካበት ዋነኛው አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በዚህ የተነሳ በበለፀጉ አገሮች እንደሚታየው ሃብት ለማካበት ፖለቲካን ትቶ ወደ ንግድ ስራ መሰማራት ሳይሆን እንደ አፍሪካ ባሉት አካባቢዎች ሃብት ለማካበት የመጀመሪያ ምርጫው ፖለቲካ ሆኖ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚባሉት የግል ጥቅም ማራመጃ ለየት ያሉ ኩባንያዎች ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ መካከል የሚደረገው የፖለቲካ ውድድርም በአማራጭ ፖሊሲዎች ዙሪያ የሚደረግ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ትግል መሆኑ ቀርቶ በተለያዩ ዘራፊ ቡድኖች መካከል የሚደረግ የሞት ሽረት ፍልሚያ ይሆናል፡፡ ይህም ለጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመፈጠር ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር፤ በአገር ግንባታና በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ አንድ የጋራ አመለካከትና እምነት እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡ በተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም መካከል ጤናማ ግንኙነቶች እንዳይፈጠር ከፍተኛ እንቅፋት ይሆናል፡፡ በዚህ ላይ በህብረተሰቡ ውስጥ የተንሰራፋው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህል ታክሎበት በፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ትግል፤ ስርዓቱ ለአደጋ እስከሚጋለጥበት ደረጃ ይለጠጣል፡፡ ምርጫ ግልፅ የአመፅና የሁከት ማቀነባበሪያ መድረክ ይሆናል፡፡ ተቃዋሚ ማለትም መናድ፣ማፍረስ፣በተገኘው አጋጣሚና ባመቸ ስልት የስርዓቱን መሰረታዊ እሴቶች በሚያጠፋ አካሄድ ተቀናቃኝን ማደናቀፍ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታን ያስከትላል፡፡
ሆኖም መንግስት በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግሉ ውስጥ ያሉትን መዋቅራዊ ችግሮች ለማስወገድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ቀይሶ ለመንቀሳቀስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ መዋቅራዊ ችግሮቹም በመንግስት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሙያ እና በብዙሃን ማህበራት፣ በዳኝነት አካሉ እንዲሁም በሌሎች የልማት ኃይሎች ወዘተ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖም ተረድቷል፡፡
ገዢው ፓርቲ ዲሞክራሲን፣ ልማትን እና ሰላምን፣ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ሳይነጣጥል የሚመለከት አስተሳሰብ ያለው መሆኑና ዲሞክራሲን ከሀገራዊ ህልውና እና ከሰላም፤ ሰላምን ከልማት፤ ልማትን ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት፤ ዲሞክራሲን ከመልካም አስተዳደር፤ መልካል አስተዳደርን ከዲሞክራሲ ጋር አስተሳስሮ የሚመለከት የተገጣጠመ የፖሊሲ ማዕቀፍ ይዞ መንቀሳቀስ መቻሉ ለችግሮቹ መፍትሔ የመስጠት ብቃት አጎናፅፎታል፡፡