‹‹ለጋሼ የተፃፈ ግልፅ ደብዳቤ›› (ክፍል አንድ)

  • PDF

አሜን ተፈሪ (የካቲት 2005)

ጋሼ፤
እንደምን ሰንብተሃል? ኑሮውስ እንዴት ይዞሃል? ተስማምቶሃል? የእማማ እና የአባባም ፀሎት ይሁንህ ሰላሙን አይንፈግህ፡፡ ዛሬ ይህን ደብዳቤ ሁሉ እንዲያየው አድርጌ፤ በአደባባይ የፃፍኩልህ፤ ሃሳብ የምንለዋወጠው እኔ እና አንተ ብቻ መሆናችንን ዘንግቼ እንዳይመስልህ፡፡ ደብዳቤው በእኔ እና በአንተ መካከል የሚካሄድ የሃሳብ ልውውጥ ቢሆንም፤ የደብዳቤው ይዘት በእኛ የግል ጉዳይ ላይ የሚያተኩር አይደለም፡፡ የሀገር ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ውይይቱ በእኔ በአንተ ብቻ መወሰን እንደሌለበት አሰብኩ፡፡ ሌሎች የሀገራችን ልጆች ውይይቱ ስቧቸው  ቢገቡ ትርፍ ይገኝበታል ብዬ ስላሰብኩ ውይይታችንን አደባባይ አወጣሁት፡፡ መቼም በዚህ ቅር እንዳይልህ ተስፋ አለኝ፡፡ ካልወደድከው በተለመደው የግል መድረክ ውይይታችንን እንቀጥላለን፡፡
ጋሼ፤
በቀደም በላከው ደብዳቤ እንደ ገለፅከው ዘንድሮ በሀገራችን ምርጫ ይካሄዳል፡፡ አሁን የመራጮች የምዝገባ ሂደት ተጠናቅቋል፡፡ ቀሪው ዝግጅት ደግሞ እንደ ቀጠለ ነው፡፡  ባለፈው ወር በላከው ደብዳቤህ በርካታ ጉዳዮችን አንስተሃል፡፡ ሆኖም ከሁሉ በላይ አዕምሮዬን ሰቅዘው የሰነበቱት ያነሳኻቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ‹‹ወቅታዊ የሀገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት እና የምርጫ ፖለቲካ ተግዳሮቶች ምን ይመስሉሃል?›› ብለኸኛል እንዲሁም፤ ‹‹ከምርጫ ፖለቲካ አንፃር በዲሞክራሲ ስርዓታችን ውስጥ ዕድገት የሚታይ ይመስልሃል?›› የሚል ጥያቄም አንስተሃል፡፡
ታውቃለህ፤ እኔ የሀገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳይ ሁሌም ያሳስበኛል፡፡ ያቀረብክልኝ ጥያቄዎች ከባድ ናቸው፡፡ ግን ከራሴ እንድታገል ስለገፋፋኝ አልጠላሁትም፡፡ ልሸሸውም አልፈለግኩም፡፡ ‹‹የዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድነው?›› የሚለው ጥያቄህን ከምርጫ ፖለቲካ ጋር አስተሳስሬ ለማየት ብዙ አሰብኩበት፡፡ ሀሳቤም ከዚህ በታች የምታነበው ነው፡፡
ጋሼ፤
ታዲያ ሐሳቤን ለማደራጀት ተቸግሬ ነገር ሳንቀራብጥ፤ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› የሚል ያልተለመደ ቃል ድንገት መጣብኝ፡፡ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› ስል ትንሽ ግር እንደሚልህ እገምታለሁ፡፡ ‹‹ዐረፍተ ነገር ማለት ያ´ባት ነው፡፡ አሁን ‹ዐረፍተ-መልዕክት› ማለት ምን አማርኛ ነው?›› እንደምትለኝ እገምታለሁ፡፡ ታውቃለህ፤ እኔ እንደ ገጣሚ የቃል ጨዋታ እወዳለሁ፡፡ አንተም ነገረ-ዘርቅ ሲሆን እንጂ ጨዋታ ትወዳለህ፡፡ ያው ዛሬ ውይይታችን አደባባይ ስለወጣ፤ እንደ ሌላው ቀን ‹‹የቤት - የጎረቤት›› ወሬ ጣል ከማድረግ እቆጠባለሁ፡፡ ግን ደግሞ ግል ደብዳቤ የመሆን ለዛውን እንዳያጣ ለማድረግ ሞክሪያለሁ፡፡
ጋሼ፤
አንድ ጊዜ፤ ‹‹አንተ እንደ አማርኛ አስተማሪ ያደርግሃል›› ብለኸኝ ነበር፡፡ መቼም ትረሳዋለህ አልልም፡፡ እናም ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› ስላልኩት ነገር ላጫውትህ አስቤ፤ ‹‹እንደ አማርኛ አስተማሪ ያደርግሃል›› ያልከኝ ትዝ ሲለኝ ሀሳቤን ለመቀየር ዳድቶኝ ነበር፡፡ ኋላ ግን፤ ከዋና ጉዳያችን ወጣ ቢልም ሳትወደው አትቀርም ብዬ ልነግርህ ወሰንኩ፡፡
መቼም፤ የአማርኛ አስተማሪህ ‹‹ዐረፍተ-ነገር›› የሚለውን ቃል ኤቲሞሎጂ እንዳልነገሩህ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናም እንዳሰብኩት የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪህ ሳይነግሩህ ቀርተው እንደሆነ፤ ዛሬ እኔ የ‹‹ዐረፍተ-ነገር››ን ኤቲሞሎጂ እነግርሃለሁ፡፡ አንተም ‹‹እንደ አማርኛ አስተማሪ…›› ላልከው ምስክር ታገኛለህ፡፡ አሁን ልንገርህ፡፡
‹‹ዐረፍተ-መልዕክት› ጥምር ቃል ነው፡፡ የሁለት ቃላት ጋብቻ ያፈራው አንድ ቃል ሲሆን፤ ‹‹ዐረፍተ-ነገር›› የሚለውን የተለመደ ቃል አምሳል አድርጌ የፈጠርኩት፡፡ ታዲያ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እስኪሰለቸን የምንሰማው ‹‹ዐረፍተ-ነገር›› የሚለው ቃል፤ አስገራሚ ፍች አለው፡፡ ታውቃለህ፤ ‹‹ዐረፍተ-ነገር›› የግዕዝ ቃል ነው፡፡ ታዲያ ግዕዝ ‹‹ዐረፍት›› ሲል ‹‹ግድግዳ›› ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ነገር›› የሚል ቃል ዘርፍ አድርጎ ‹‹ዐረፍተ-ነገር›› ሲል፤ በቁሙ የሚሰጠን ትርጉም ‹‹የነገር ግድግዳ›› የሚል ነው፡፡ ‹‹ዐረፍተ-ነገር›› አንድ ባለቤት፣ አንድ ግሥ ይዞ ይቋቋማል፡፡ ባለቤት እና ግሥ ተጋብተው አንድ ሀሳብ ይወልዳሉ፡፡ ሁለቱ ቃላት የሰሩት ጎጆ፤ የሀሳብ ወይም የነገር ቤት ይሆናል፡፡ የሀሳብ ወይም የነገር ግድግዳ ተሰራ ማለት ነው፡፡ በዚህ ጎዳና ስታየው፤ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› የሚለው ቃል ትርጉም እንደሚሰጥህ አልጠራጠርም፡፡ 
ጋሼ፤
እንግዲህ እኔ የዚህን ፅሁፍ (ደብዳቤ) ‹‹ዐረፍት›› ስቀነብብ፤ ‹‹የመልዕክት ግድግዳ›› ሰራሁ ማለት ነው፡፡ ፍቶ በ‹‹ፍሬም›› እንዲቀመጥ ለሀሳብም ‹‹ፍሬም›› ያስፈልገዋል፡፡ እናም የዚህ ደብዳቤ (ፅሁፍ) ሰፊ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› ‹‹ዲሞክራሲ›› ነው፡፡ ‹‹ዲሞክራሲ›› ሲባል ድንበሩ እንደ ሀገር ሰፊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክቱን›› ጠበብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲ የአስተዳደር ዘዬ ነው፡፡ ታዲያ ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓትን ከሌሎች የአገዛዝ ስርዓቶች የተለየ የሚያደርገው ዋነኛ ባህርይው፤ የመንግስት ሥልጣን የሚያዘው በህዝባዊ ምርጫ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ጠበብ ሲደረግ የፅሁፌ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› የዲሞክራሲ ስርዓት መለያ የሆነውን ‹‹የምርጫ ፖለቲካ›› የሚመለከት ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ‹‹ዐረፍተ-መልዕክት›› ውስጥ ሁለት ጥያቄዎች ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ስለሀገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ስለ ምርጫ ፖለቲካው ተግዳሮቶች ያለኝን አስተያየት እገልፃለሁ፡፡
ከምርጫ ፖለቲካ አንፃር የሀገራችን ላነሳኸው ጥያቄ መደላድል እንዲሆነኝ፤ በቅድሚያ ‹‹የዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድነው?›› የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ወስኛለሁ፡፡ ጋሼ ጥያቄህን መመለሱ ባስቸገረኝ መጠን ‹‹እንኳንም ይህን ጥያቄ ጠየቀኝ›› ብዬ በልቤ አመስግኘሃለሁ፡፡
ጋሼ፤
ታዲያ የሀገራችንን የዲሞክራሲ ስርዓት ወቅታዊ ተግዳሮት፤ የስርዓቱ መለያ ባህርይ ከሆነው የምርጫ ፖለቲካ አንፃር ለማየት ስነሳ፤ መጀመሪያ ትኩረት ማድረግ ያለብኝ መዋቅራዊ ሆነው በታዩኝ ችግሮች ላይ መሆን አለበት፡፡ ይህንም ጉዳይ ‹‹የቅርፅ›› ሳይሆን ‹‹የጥልቀት›› መልክ ሰጥቼ መፈተሽ ይኖርብኛል፡፡ ፍተሸዬንም ሀሳባዊ እና ተግባራዊ ሁኔታዎችን መዳሰስ በሚያስችል መንገድ ለማድረስ እሞክራለሁ፡፡ ጥያቄው የተነሳው መሬት ከለቀቀ አካዳሚያዊ የማወቅ ጉጉት አይደለም፡፡ አንተም የጠየቅከኝ ለምን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ጥያቄውን ያነሳኸው ገጣሚው ደበበ ‹‹ወደፊት ለመሄድ እንሩጥ ወደኋላ›› እንዳለው፤ ካለፈው የምርጫ ሂደት የሚገኝ ትምህርት ካለ እሱን እንድንቃርምና እንድንቀምር ነው፡፡ በዚህም ዘላቂ እና መጪ ጉዟችንን የሚያቃና ግንዛቤ መፍጠር እንድንችል ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሁል ጊዜ የምቸገርበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥረታችን እና ብናካሂዳቸው ምርጫዎች ዙሪያ የሚሰነዘሩ፤ በገጽታቸው ትክክል የሚመስሉ በይዘታቸው ግን የተሳሳቱ አስተያየቶች እየሰማሁ ‹‹ ስንቱን ሰው ያሳስት ይሆን?›› እያልኩ የማልፋቸውን ጉዳዮች ለማንሳት የሚያስችል ዕድል ፈጠርክልኝ፡፡ ጉዳዮቹ በርካታና ውስብስብ ናቸው፡፡ ሆኖም ከፊታችን ባለው ምርጫ ላይ የሚሰነዘሩ (አሁን ወይም ወደፊት) አስተያየቶችን ፍሬ - ከገለባ ለይተን፤ እንደ ዜጋ ዳኝነት ማሳለፍ እንድንችል ብርሃን ፈንጣቂ ሀሳቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
ጋሼ፤ እኔ ከአንተ የማገኘውን አንድ በረከት ልንገርገርህ? የምትሰጠኝ በረከት ምን እንደሆነ ታውቃለህ? አዎ፤ ከባድ የሚመስሉኝን ነገሮች ደፍሬ እንድጋፈጥ የሚያደርግ የብርታት መንፈስ ነው፡፡ የገዛ ህይወቴን ሌላ ሰው እንዲተነትንልኝ መጠበቅን አሽቀንጥሬ የመጣል ጉልበት ነው፡፡ 
ጋሼ፤
ታዲያ ዲሞክራሲን በተመለከተ ያነሳኸው ጥያቄ፤ በወቅታዊ ተግዳሮት ላይ ያተኮረ ቢሆንም እንደኔ ወቅታዊ ተግዳሮቶቻችን፤ ከስርዓቱ መዋቅራዊ ችግሮች የሚነሱ በመሆናቸው ወቅታዊ ተግዳሮቶቻችንን ለመረዳት እና መፍትሄም ለመሻት የምናደርገው ጥረት የስርዓቱን መዋቅራዊ ችግሮች ከመረዳት ተለይቶ መታየት የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ መዋቅራዊ የምላቸውን ችግሮች በማንሳት ልጀምር፡፡
ጋሼ፤
ታውቃለህ፤ የሀገራችን ዲሞክራሲ ‹‹የአርሶ - አርብቶ አደር›› ዲሞክራሲ ነው፡፡ ማለቴ፤ የሀገራችን ህዝብ 85 በመቶ ገደማው ‹‹አርሶ - አርብቶ አደር›› ነው፡፡ ገና በመሐይምነት ግርዶሽ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገራችን ‹‹አርሶ - አርብቶ አደር›› በዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ውስጥ የሚኖረው ሚና የተወሰነ ነው፡፡ በስርዓቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ኃይሎች የመግራት እና የመቆጣጠር አቅሙም ውስን ነው፡፡ ‹እናም ያልተማረና የማያነብ ህዝብ ይዘን፤ የህዝቡን ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ በበቂ ማረጋገጥ አንችልም፡፡ ስለዚህ ትምህርትን ማስፋፋት ጥረታችን እና የተገኘው ስኬት፤ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥረትና ስኬት መሆኑን ልብ በል፡፡
ሆኖም ችግሩ ያለመማር ብቻ አይደለም፡፡ የተማረው የህብረተሰብ ክፍልም ለምርጫ ፖለቲካ እና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ባይተዋር የሆነ ታሪክና ባህል ያለው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከልምድ፣ ከታሪክ እና ከባህል ጋር በተያያዙ ችግሮች መታሰራቸውን አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል፤ የስርዓቱን ባህርይ ካለማወቅ ሳይሆን፤ ሆነ ብሎ ፈር ለቅቆ በመሄድ፤ የስርዓቱን መርሆዎች በጠባብ የቡድን ፍላጎቱ ሸቅጦ ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኘት በሚፈልግ ቡድን ወይም ኃይል የሚመጣ ችግር ደግሞ አለ፡፡
ሆኖም ፈር የሳተ እና የተወነጋገረ፤ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተቃራኒ በሆነ አቋም የሚነግዱ ኃይሎች፤ ወረት አድርገው የሚይዙት የእኛን የዜጎችን (ወይም የአባሎቻቸውን) አለማወቅ ነው፡፡ ይህ ችግር የእኛን አለማወቅ እየተመገበ የሚኖር ችግር ነው፡፡ እኛ ስለ ስርዓቱ ያለን ዕውቀት እና ልምድ ሲዳብር ድራሹ የሚጠፋ ችግር ነው፡፡ መሠረታዊው ነገር ዕውቀት ነው፡፡
ጋሼ፤
የስርዓቱን ባህርይ በውል ለመረዳት ና ችግሮችን ለይቶ ለማስተካከል ዕውቀት ያስፈልገናል፡፡ የዲሞክራሲያዊ ስርዓታችንን የሚጎዳ ግልፅ እና ስውር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወገኖች ከአድራጎታቸው እንዲቆጠቡ፤ ማድረግ፣ የተፈሩ እና የታፈሩ ዞጎች መሆን የምንችለው በማወቅ ነው፡፡ በእግርጥ፤ እኔ እንደማስበው በጠባብ ፍላጎት ታውረው ፈር በመልቀቅ መሄድ የሚሹትን የሌሎችን መብት በመርገጥ የሚራመዱትን፤ የዲሞክራሲ ስርዓቱን በሚጎዳ መንገድ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉትን ወገኖች፤ አውቆ አጥፊ ከማለት አላዋቂ ብላቸው እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ውሎ አድሮ ድርጊታቸው እነሱንም ጠራርጎ የሚወስድ ጎርፍ እንደሚከፈት የሚዘነጉ በመሆናቸው፡፡ መብት እና ነፃነት ውድ ሀብቶች ናቸው፤ ሆኖም ለሌሎች ሳትሰጥ አታገኛቸውም፡፡  የሌሎችን መብት እና ነፃነት ሳታከብር፤ የአንተን መብት እና ነፃነት ማስከበር አትችልም፡፡ ለሌሎች ሲሰጡት የሚበዛ ሀብት ካለ መብት እና ነፃነት ነው፡፡
ለቡድናዊ ጥቅም ብለህ፤ የዲሞክራሲ ስርዓት መርሆዎችን መናድ ስትጀምር የቆምክበት መሬት ይከዳሃል፡፡ ታዲያ አንዳንዶች ይህን ችግር ካለመረዳት የሚፈጽሙት ስህተት አለ፡፡ ታዲያ እንዲህ ያሉ፤ ከዲሞክራሲ ስርዓት መርሆዎች ጋር የሚያጋጩ፤ ወይም ለስርዓቱ በሽታ የሚሆኑ ሃሳብ እና ድርጊቶች ሊታከሙ የሚችሉት በማወቅ ብቻ ስለሆነ፤ ዋና ትኩረታችን በህዝቡ ማወቅ - አለማወቅ ላይ ነው፡፡ በአንድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሁሉም አባላት ጥቅም ሊጠበቅ የሚችለው የስርዓቱ መርሆዎች (የህግ የበላይነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት ወዘተ) ሲከበሩ ብቻ መሆኑን ማሳወቅ ይኖርብናል፡፡ ይህን ካለማወቅ የሚመጡ ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉትም በማወቅ ወይም በመማር ነው፡፡ ዕውቀትንም ባላሰለሰ ሁኔታ ለማሻሻል በመጣር ነው፡፡ በዕውቀት ላይ በመመስረት፤ በተደራጀ አኳኋን ጥቅምን ለማስከበር በመንቀሳቀስ ነው፡፡
እንዲሁ፤ ዕድገት እና ውድቀት መኖሩን ማወቅ የሚቻለው በማወቅ ነው፡፡ ታዲያ በስርዓቱ ውስጥ የሚታዩትን እነዚህን ጉድለቶች፤ የስርዓቱ ዋና ዋና ተዋናይ ከሆኑት ኃይሎች አንፃር ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም እርሱን ከምርጫ ፖለቲካ ጋር አያይዤ ስለማየው፤ አሁን፤ ‹‹የሀገራችን ዲሞክራሲ ወቅታዊ ተግዳሮት ምን ይመስልሃል?›› ብለህ ለጠየቅከኝ፤ ምላሼን ልንገርህ፡፡ አጭሩ ምላሼ፤ የሐይማኖት አክራሪነት ነው፡፡ ይህም ችግር ከላይ በጠቀስኳቸው መዋቅራዊ ችግሮች ማህፀን የሚወለድ እና የእነሱን ደም እየጠጣ የሚኖር ችግር መሆኑን ልብ በልልኝ፡፡
ጋሼ፤
ታውቃለህ፤ የሐይማኖት አክራሪነት ዓለም አቀፍ ገፅታ ያለው ችግር ነው፡፡ በእኛም ሀገር ችግሩ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ቀደም ሲል፤ በተበታተነ እና በተንጠባጠበ ሁኔታ ይታይ የነበረው የሐይማኖት አክራሪነት ችግር አሁን-አሁን የተደራጀ መልክ መያዝ እና ዓለም የሚደነቅበትን ዘመናትን የዘለቀ ጥልቅ የአብሮ መኖር ቅርሳችንን መገዝገዝ፤ ነባር የመቻቻል ባህላችንን መበዝበዝ መጀመሩን እናስተውላለን፡፡ ችግሩ ከዚህ በላይ ጥልቀት እና ግዝፈት እንዳይዝ መጠበቅ እንዳለብንም የሚያሳስብ ክስተቶችን አይተናል፡፡ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረበው ዘገባ፤ ከተዘናጋን ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለአደጋ የምናጋልጠው መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ ዓለም አቀፍ ትስስር ያለው የአክራሪ ኃይል፤ በህዋስ ደረጃ በሀገራችን ተደራጅቶ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ‹‹ይህ ኃይል በእንጭጩ መቀጨት ይኖርበታል›› ሲሉ በአፅንዖት መናገራቸው፤ የወደፊቱን አደጋ በማሰብ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን ላይ የተደቀነ ወቅታዊ አደጋ መሆኑን በማጤን እንደሆነም አምናለሁ፡፡
ጋሼ፤
በሐይማኖት አክራሪነት ላይ የሚደረግ ትግል እጅግ ከባድ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ከድህነት ጋር ተያይዞ የሚወለድ፣ በድህነት ማህፀን የሚፋፋ፣ ድህነትን ነዳጅ አድርጎ የሚስፋፋ፣ ከድህነት ጋር የሚደረገውን ትግል የሚያወሳስብ ችግር ነው፡፡ እና የሐይማኖት አክራሪነትን በመታገል ረገድ የጋራ እምነት ሊያዝበት የሚገባው ዋና ጉዳይ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጠንቅ የመሆኑ ነገር ነው፡፡ የሐይማኖት አክራሪነትን ለመታገል የምናደርገው እንቅስቃሴም ግልፅ የሆነ አቅጣጫ ሊቀመጥለት ይገባል፡፡
ሆኖም እዚህ ማንሳት የምፈልገው ነጥብ፤ ‹‹አክራሪ አቋም (የሐይማኖትም ሆነ የፖለቲካ) የሚያራምዱ ኃይሎች በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሚስተናገዱት እንዴት ነው? ለምንስ ይስተናገዳሉ?›› የሚል ጥያቄ ነው በዚህም ጉዳይ የጠራና የጋራ ግንዛቤ መያዝ ይገባናል፡፡ አክራሪ ኃይሎች የዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያጎናፅፈውን ነጻነት ተጠቅመው፤ በህገ መንግስት የተረጋገጡ መብቶችን መሠረት አድርገው ሊደራጁ ይችላሉ፡፡ ግን የመደራጀት መብት ያጎናጸፋቸውን እና መብቴ ተነካ ሲሉ የሚጠቅሱትን ህገ መንግስት የሚያከብሩ ኃይሎች እንዳልሆኑ እናውቃለን፡፡ በታሪክ እንዳየነው የጀርመኑ ናዚ በዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ተጠቅሞ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ሲያፈራርስ አይተናል፡፡ ችግሩ፤ How do we tolerate the intolerants? (መታገስ የማያውቁ ኃይሎችን የምንታገሳቸው እንዴት ነው) በሚል የሚገለፅ ነባር የስርዓቱ እንቆቅልሽ ነው፡፡
ይህን እንቆቅልሽ ለመፍታት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት መሠረታዊ እሳቤዎችን፣ መርሆዎች እና አመለካከቶችን ማየት ጥሩ ነው፡፡ የዲሞክራሲ መሠረታዊ መነሻ፤ ‹‹ሁሉም ሰው በመሠረታዊ ባህርይው ጥሩ ነው›› የሚል ይመስለኛል፡፡ ደግሞ፤ ‹‹ሁሉም ሰው ራሽናል ነው፡፡ በአዕምሮው የሚመራና የሚያስብ ፍጡር ነው›› ብለን መነሳት ይኖርብናል፡፡ ሆኖም፤ ‹‹ሁሉም ሰው በመሠረታዊ ባህርይው ጥሩ ነው፡፡ ራሽናል ነው፡፡ በአዕምሮው የሚመራና የሚያስብ ፍጡር ነው›› ማለት፤ ‹‹ማንም ሰው ወንጀል አይሰራም፡፡ ሁሌም ሰው በእርሱ እንዲደረግበት የማይፈልገውን በሌሎች ያለማድረግ ወርቃማ መርህን አክብሮ ይኖራል፡፡ ማለት አይደለም፡፡ እንዲህ ብሎ መደምደም፤ ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚያቃርን ነው፡፡
ስለዚህ ማንኛውም ሰው ወንጀል ሊሰራ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ የዘር፣ የዕድሜ፣ የፆታ፣ የቀለም ወይም የሐይኖማት ወዘተ ልዩነት፤ ልዩነት አያመጣም፡፡ በሁሉም መልክዐ ምድር የሚኖሩ ሰዎች ወንጀል የሚሰሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሆኖም የዘር፣ የዕድሜ፣ የፆታ፣ የቀለም የሐይማኖት ወዘተ ልዩነት ሳይኖር፤ በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈፀም ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉንም የሰው ልጆች ይነካናል፡፡ ሀዘን ወይም ቁጣ ይፈጥርብናል፡፡ እናዝናለን፡፡ ይኸ ጉዳይ ሰዎች ሁሉ የጋራ ነገር እንዳንለን ጠቋሚ ነው፡፡ አንድ ሰው ድንጋይ ሲፈለጥ ከማየት ዛፍ ሲቆረጥ ማየት ስሜት ይፈጥርበታል፡፡ ዛፍ ሲቆረጥ በማየት ከሚፈጠርበት ስሜት ደግሞ ውሻ በመኪና ሲገጭ በማየት የሚፈጠርበት ስሜት ይበልጣል፡፡ ይህን በገዛ ልምዳችን እናውቀዋለን፡፡ ምሁራን ይህን ጉዳይ በዝምድና ይፈቱታል፡፡ ዝምድናው ከሌላ ሰው ጋር ሲሆን ጥብቅ ይሆናል፡፡ ይኸ ዝምድና ሰብአዊ ፍጡራን ከዘር፣ ከሐይማኖት… የተሻገረ የጋራ ነገር መያዛችንን ያመለክታል፡፡
ጋሼ፤
ሆኖም ይህ የጋራ ነገራችን፤ በብሔር፣ በዘር፣ በቡድን፣ በግለሰብ ወዘተ  ጥቅም ሚዛን ታይቶ ሊጠፋና ሊጣስ ይችላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የጋራ መጠቀሚያ የሆኑትን የስልክ እና የመብራት ምሰሶዎች ወይም ሽቦዎች ሲቆርጡ እንደምናየው፤ የመንግስትን ሥልጣን የያዘ ሹመኛ፣ ለቤተሰቡ፣ ለጓደኛው፣ ለራሱ ጥቅም ብሎ ህግ ሲያጣምም እናስተውላለን፡፡ ግን ይኸ የሰው ልጅ በመሠረታዊ ባህርይው ጥሩ መሆኑን አያጠፋውም፡፡ ብዙው ሰው ያስባል፡፡ ስለዚህ ከቻለ ጥቅሙን ሌሎችን በማይጎዳ መንገድ ለማራመድ ይሞክራል፡፡ ሆኖም ይህን የሚያበላሹ አንዳንድ ወገኖች መኖራቸው እርግጥ ነው፡፡ ደግነቱ፤ በቁጥር ጥቂቶች ናቸው፡፡ ህግ መደንገግ የተቻለው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ወንጀል የሚደነገገው ጥፋት የሚፈፅሙት ጥቂት ሰውዎች ብቻ በመሆናቸው ነው፡፡ ነገሩ ሁሉም ሰው የሚፈፅመው ከሆነ ባህል እንጂ ወንጀል ሊሆን አይችልም፡፡ የህግ ሰዎች እንደሚሉት አንድ ህግ የሚወጣው፤ ማህበረሰቡ ጥቅም ብሎ የሚያስበውን ጉዳይ ከጥቃት ለመከላከል ነው፡፡ ያ ማህበረሰብ ጉዳት የሚለው ነገር እንዳይፈፀም እና ጥቅም ብሎ የሚያስበው ነገር እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ወንጀል ያልተባለ ነገር፤ በሌላ ጊዜ ወንጀል ሲደረግ የምናየው ለዚህ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ጥቅሜ ብሎ የሚያስበውን ነገር የሚረብሽ ድርጊት ሁሉ ወንጀል ያደርጋል፡፡ መንግስትም የህብረተሰቡን ሰላማዊ ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ አጥፊዎችን በመከታተል ለመቅጣት ይታገላል፡፡ አሁንም የትግሉ መነሻ ማስተማር ነው፡፡ እንደኔ ሀሳብ የሰው ልጆችን ህይወት፣ ንብረት፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ጥቅም፤ የቡድን የግል መብቶች እና ነፃነቶችን የሚያስከብረው ማህበራዊ ስርዓት ዲሞክራሲ ነው፡፡ ይህን ስርዓት መጣስም የህብረተሰቡን ጥቅም መጣስ ነው፡፡ ታያ አክራሪነት (የሐይማኖትና የፖለቲካ) የጋራ ጥቅም ማስከበሪያ ስርዓታችንን ለሚጥስ ተግባር ዝግጁ ያደርጋል፡፡
ጋሼ፤
መሠረቱን ሐይማኖት አድርጎ የቆመ ኃይል፤ በእምነት የሚመስሉትን ብቻ የሚፈቅድ እና የሚያቅፍ አግላይ ኃይል ነው፡፡ ስለዚህ እምነትን ሳይሆን ሰው መሆንን ብቻ መሠረት አድርጎ ለሚንቀሳቀሰው ሁሉን አቃፊ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ፀር ነው፡፡ የዲሞክራሲ መሠረቱ የመንግስት እና የሐይማኖት መለያየት ነው፡፡ ይህን ልዩነት የሚያፈርስ ኃይል የዲሞክራሲ ፀር ነው፡፡ የሐይማኖት አክራሪነት፤ እምነትን አጥብቆ ከመያዝ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አይደለም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት፤ ማንኛውም ሰው እምነቱን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የማከናወን መብቱን የሚያረጋግጥ እና የሚያስጠብቅ ስርዓት ነው፡፡ ስለዚህ እምነትን አጥብቆ መያዝ ለዲሞክራሲ ችግር አይደለም፡፡ ችግር የሚመጣው፤ እምነቱን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመተግበር መብት ተጎናፀፈው ኃይል፤ ሐይማኖታዊ መንግስት መመስረት አለበት ብሎ ሲነሳ እና ይህንም ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ የሐይማኖት አክራሪነት፤ የዲሞክራሲ እሴቶች የሆኑትን መመቻመችን፣ መቻቻልን፣ ሰጥቶ መቀበልን የሚጠላ በመሆኑ የዲሞክራሲ ፀር ነው፡፡       
እንደዚህ ያለ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች፤ ልዩነቶቻችንን ሁሉ ተሻግረን አንድ የምንሆንበትን፤ ሰው በመሆን የምንሰባሰብበትን፤ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በጋራ የምንታይበትን ድንኳን ይጠሉታል፡፡ ‹‹በእምነት ከእኛ ጋር ያልሆነው ሁሉ፤ የእኛ ጠላት ነው›› የሚሉ በመሆናቸው፤ ከነመፈጠራቸውም የማያውቋቸውን እና በእምነት እነሱን የማይመስሉትን ሰዎች ሁሉ እንደ ጠላት ይመለከታሉ፡፡ በዚህ መነሻም፤ በቀላሉ ወደ ጅምላ ግድያ ይሸጋገራሉ፡፡
ጋሼ፤
እነዚህ ኃይሎች በተለይ እንደኛ ባሉ እና ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው መዋቅራዊ ችግሮች ባሉባቸው ሀገሮች ውስጥ አደገኛ ውጤት የማስከተል ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በበለፀጉት ምዕራባዊ ሀገሮች ውስጥ በቸልታ እና በትዕግስት ሊስተናገዱ የሚችሉ አንዳንድ አክራሪ ኃይሎች እንኳን፤ በድሆቹ ሀገሮች አስፈሪ ይሆናሉ፡፡ ምዕራባውያን ዜጎች በዲሞክራሲያዊ ስርዓት እሴቶች የታነጹ በመሆናቸው፤ የአክራሪ ኃይሎችን አፍራሽ ቅስቀሳ መቋቋም ይችላሉ፡፡ ቅስቀሳቸው ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉም ለዜሮ የቀረበ ነው፡፡ ስለዚህ መንግስታት አክራሪዎችን ቸል ሊሏቸው ይችላሉ፡፡ ሆኖም ያላደጉ ሀገሮች መንግስታት፤ ከአቅም ውሱንነት፣ ከድህነት መስፋፋት፣ ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ እና ግፊት፣ ከዲሞክራሲያዊ ባህል አለመጎልበት ወዘተ ጋር ተያይዞ፤ የአክራሪ ኃይሎቹ እንቅስቃሴ ያሰጋቸዋል፡፡ አጠቃላይ የሆነ ህገ መንግስታዊ ቀውስ የመፈጠሩ ዕድልም ዝግ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ፤ የሁሉንም ዜጎች መብት የማስከበር ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት የሐይማኖት አክራሪነትን እንደ ትልቅ የቤት ሥራ አይቶ በንቃት መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡
ጋሼ፤
እንኳንስ ዘንቦብሽ… እንዲሉ፤ ቀድሞም ከልክ ባለፈ ሸፍጥ የተበከለ የፖለቲካ ባህል በገነገነበት፣ ኃላፊነት የጎደለው ፖለቲካ በሚሰራበት፣ የመቻቻል ፖለቲካ እንግዳ በሆነበት የሀገራችን የፖለቲካ መድረክ፤ በሐይማኖት አክራሪነት የሚፈረጁ ኃይሎች ሲጨመሩ፤ ነገሩ ሁሉ የእብድ ገበያ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ እምነተ ብዙ በሆነ ሀገር፤ የሐይማኖት አጀንዳ አንግበው፤ ሐይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት የሚያስቡ ኃይሎች፤ ሀሳብ እና ዓላማቸው የበላይነት ሊያገኝ የሚችለው በኃይል እንጂ በይሁንታ እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ አክራሪዎች በህገ መንግስቱ የተደነገጉ መብት እና ነፃነቶችን እየጠቀሱ - እየተጠቀሙ፤ መብት እና ነፃነትን ለማጥፋት የሚሰሩ ናቸው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ሳይሆን በሐይማኖታዊ ህግ ለመመራት የሚፈልጉ መሆናቸውንም እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ህገመንግስቱን ማቃጠል የሚፈልጉ አክራሪ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ቸል ልንለው አንችልም፡፡
ጋሼ፤
እንግዲህ ቅድም በይደር ያለፍኩትን (ዲሞክራሲን ከዋና ተዋናዮቹ አንፃር) እና የሀገራችንን የምርጫ ፖለቲካ ዕድገት ወይም ጉድለት ወደማየት አልፋለሁ፡፡ መቼም ‹‹ዕድገት አለ?›› ሲባል የምንሰጠው ምላሽ፤ በጥቅሉ ‹‹አዎ ዕድገት አለ›› ወይም ‹‹አይ እጥረት - ጉድለት አለ›› የሚል ከሆነ አይጠቅምም፡፡ ዕድገት አሳይቷል ከተባለ፤ ዕድገቱ በምንድነው የሚለካው? የሚል ጥያቄን በገዛ ራሱ ይጋብዛል፡፡ ጥያቄው ሳይጠራ ይመጣል፡፡ ጉድለት አለ ከተባለም ያው ነው፡፡ የመለኪያ ጉዳይ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡
ለዚህ ውይይት፤ የዲሞክራሲ ስርአት ዋና ዋና ተዋናይ ቡድኖችን እና ተቋማትን መለየት፤ ዕድገቱ በማን ጥረት - ብርታት፤ ጉድለቱም ከማን እጥረት - ስህተት የመጣ እንደሆነ መለየት ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የምርጫ ፖለቲካ ዋና ዋና ተዋናዮች የሚባሉትን ኃይሎች እንመለከታለን፡፡ ዋና ተዋናዮቹ፤ ዜጎች (ህዝቡ)፣ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማህበራት፣ ሚዲያ ናቸው፡፡ እነዚህ ዋና ዋና ተብለው የተጠቀሱት ኃይሎች ራሳቸው ብዙ አባል እና አካል ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሣሌ፤ መንግስትን በሁለት መክፈል ይቻላል- የክልል እና የፌደራል በሚል፡፡ በሁለቱ ደረጃ ያሉት መንግስታት ብዙ ተቋማት አደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከብዙዎቹ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ለዲሞክራሲ ስርዓቱ መጠናከር ጉልህ ድርሻ ያላቸው የሚባሉ ወይም ‹‹የዲሞክራሲ ተቋማት›› በሚል የሚጠቀሱ ተቋማት አሉ፡፡ ለምሣሌ፤ የተወካዮች ምክር ቤት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የዕንባ ጠባቂ ኮሚሽን እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ ቀዳሚ ተጠቃሽ የዲሞክራሲ ተቋም ተቋማት ናቸው፡፡
እንዲሁ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን -ገዢ እና ተቃዋሚ፡፡ ሚዲያዎችን፤ የግል እና የህዝብ ማለት ይቻላል፡፡ ማህበራትን፤ የሙያ እና የብዙሃን ብለን ማየት እንችላለን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚቆመው በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ተዋናይ በሆኑት ሁሉም ወገኖች የጋራ ጥረት ነው፡፡
ጋሼ፤
የዲሞክራሲ ስርዓት የዓለም ምርጥ ድንቅ ህግ በማፅደቅ ብቻ አይቆምም፡፡ በጥቂት ሊሂቃን ዕውቀት እና ተሳትፎም ተጠብቆ ሊኖር አይችልም፡፡ ስርዓቱ የሚቆመው፤ ሁሉም ተዋናዮች ለስርዓቱ ታማኝ፤ ለመርሆዎቹ ተገዢ ለመሆን ባላቸው ፍላጎት ወይም ፅናት ነው፡፡ ሆኖም ተዋናዮቹ ለዲሞክራሲ ስርዓት መከበር የሚኖራቸው ፍላጎት፣ ብቃት፣ ፅናታትና ታማኝነት ወዘተ የሚወስነው በእኛ በዜጎቹ ዘንድ በሚታይ ብቃት ነው፡፡ ዜጎች የስርዓቱን ባህርያት አውቀውና ተደራጅተው ለመቀሳቀስ፤ ንቁ ተሳታፊም ለመሆን ባላቸው ተነሳሽነት ነው፡፡ ዜጎች እንዲህ ዓይነት ብቃት ሲኖራቸው፤ በሁሉም ኃይሎች ይታፈራሉ፡፡ ዕውቀት፣ ትጋት፣ ንቃት እና የተደራጀ እንቅስቃሴ ሲኖራቸው፤ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ስርዓቱን የሚሸፍጡ ወገኖችን አደብ ማስገዛት እና ማረቅ ይችላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ዲሞክራሲ ሊጠናከር አይችልም፡፡ ጥቂት አርቀው የሚያስቡ ሰዎች በመኖራቸው ዲሞክራሲ ሊጠበቅ አይችልም፡፡ ሁላችንም የሚታፈር እና የሚከበር ዜጎች ሆነን መገኘት አለብን፡፡ እንዲህ ሆነን ካልተገኘን ይደፍሩናል፡፡ ድንገት በምርጫ ወቅት እየመጡ ያደናግሩናል፡፡
ጋሼ፤
ዲሞክራሲ እና ምርጫ በጣም ግራ አጋቢ ነገር አላቸው፡፡ ዲሞክራሲ፤ የሚረባውም ‹‹የማይረባውም›› ኃይል በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ ዕድል ይሰጣል፡፡ ከዚያ ህዝቡ ይረባል የሚለውን ኃይል እንዲመርጥ መድረክ ያመቻቻል፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት የመምረጥ ዕድልን ይሰጠናል እንጂ የሚረባውን ኃይል መርጦ አይሰጠንም፡፡ ታዲያ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሚደረግ ምርጫ፤ የማይረቡ ሰዎች ወደ ፖለቲካ መድረኩ እንዳይመጡ ለመጠበቅ የሚያስችለን፤ እኛ አውቀን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡ ያኔ መምረጥ እንችላለን፡፡ ፋይዳ የለውም፡፡ ምርጫ፤ ምርጫ የሚሆነው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ሲሆን ነውና፡፡
ምርጫ፤ ዞሮ - ዞሮ የህዝብ ፍልጎት እና ጥቅም ማስከበሪያ እንጂ ለራሱ (ለጌጥነቱ) ሲባል የሚካሄድ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው፤ ምርጫ መንገድ እንጂ ግብ አይደለም የሚሉት፡፡ ምርጫ፤ ሀገር የመምራት ኃላፊነትን፤ ምን ለመስራት እንደሚፈልግ እና እንደሚያስብ ለምናውቀው የፖለቲካ ቡድን የምንሰጥበት ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው፡፡
በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ሥልጣን የሚያዘው በህዝባዊ ምርጫ ነው፡፡ እናም ስለ ምርጫ ስናወራ፤ ስለ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያወራን ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በሌለበት ቦታ ምርጫ አይኖርም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን፤ የፖለቲካ ባህላችን መዳበር እና ዲሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ የዲሞክራሲ ባህላችን እንዲዳብር ደግሞ የህዝቡን የተደራጀ ፍላጎት የሚወክሉ እንደ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሙያ እና የብዙሃን ማህበራት፣ እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት አሰራር እና አደረጃጀት ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ሊይዝ ይገባል፡፡
ጋሼ፤
‹‹የኢትየጵያ የምርጫ ፖለቲካ ዕድገት አሳይቷል?›› የሚለውን ጉዳይ ለመመዘን፤ ዋና ዋና ተዋናዮች ያልናቸውን ኃይሎች ያለፉ ዓመታት ሚና ማየት እና መመዘን፤ ልማት - ጥፋታቸውን መገምገም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አካሄድ የምርጫ ውድድሩን የፖለቲካ ባህላችን አጠቃላይ ባህርይ መለኪያ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለምርጫ ፖለቲካ ባህል መዳበር ቁልፍ ሚና ያላቸውንም ተቋማት አስተዋፅዖ መፈተሽ እንችላለን፡፡ ሆኖም በዚህ ደብዳቤ የሁሉንም ተዋናዮች ሚና ማየት አልችልም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱን (የመንግስትን፣ የብዙሃን ማህበራትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን) ኃይሎች ብቻ ለይቼ አነሳለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ለምርጫ እና ለመድብለ ፓርቲ ባህል ባይተዋር ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህርይውን መቀየር ከጀመረ ሁለት አስርት አስቆጥሮ እያለፈ ነው፡፡ ዛሬ ምርጫ እና የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ፤ የህይወታችን አንድ ቀለም ሆኗል፡፡ በመጀመሪያው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ሂደቱን ለመከታተል የመጣ አንድ ተማራማሪ ወደ ሰሜን ሄዶ ‹‹የድምፅ አሰጣጡን ምስጢራዊነት ለማስጠበቅ ምን ጥረት አድርጋችኋል?›› ብሎ ቢጠይቅ፤ አንድ የታችኛ እርከን የአስተዳደር ኃላፊ፤ ‹‹በእኛ ዘንድ ምስጢራዊ የሚባል ነገር የለም፡፡ ምስጢራዊነት ከደርግ ጋር አክትሟል›› የሚል እንደ ሰጠው ገልፆ ነበር፡፡ ዛሬ እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሚሰጥ ፖለቲከኛ ቀርቶ ህፃን አናገኝም፡፡ ዛሬ ሁሉም የምርጫ ተዋናዮች ስለ ምርጫ ሂደት እና ስለ ፋይዳው ያላቸው ግንዛቤ የላቀ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህ በዕድገት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ሆኖም ለታየው ዕድገት ሁሉም ተዋናዮች እኩል ሚና የተጫወቱ አይደሉም፡፡
ጋሼ፤
‹‹የምርጫ ፖለቲካ ዕድገት አሳይቷል?›› የሚል ጥያቄ ሲነሳ፤ ‹‹ዕድገት - ውድቀቱ በምን ይለካል?›› የሚል ወሳኝ ጥያቄ ይከተላል፡፡ ይኸ ዕድገት እና ጉድለትን የመመዘን ጥያቄም ‹‹አንድ የምርጫ ስርዓት ውል ባለው ሁኔታ ሊመዘን የሚችለው እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄን ሳይመልስ ሊሄድ አይችልም፡፡
ይህም ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት መሠረታዊ ባህርያት እና ከሀገራችን መዋቅራዊ ሁኔታ፤ እንዲሁም ከምርጫ ስርዓታችን ጋር ተያይዞ መታየት የሚገባው እጅግ ሰፊ አጀንዳ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስለኢትዮጵያም ሆነ ስለአፍሪካ ምርጫ የሚሰጡ አስተያየቶች ወይም በታዛቢ ቡድኖች የሚወጡ ሪፖርቶች የተሳሳተ የሚሆኑት ለዚህ ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያን ግለሰቦች እና ተቋማት፤ ስለ አፍሪካ ምርጫ የሚሰጡትን አስተያየቶች በመጥቀስ ሀሳቤን ግልፅ ላድርግልህ፡፡ ለምሣሌ፤ ‹‹ዛሬ እንደ በፊቱ በምርጫ ሂደት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ግልፅ እንግልትና ወከባ አይደርስባቸውም፡፡ ሆኖም ምርጫው፤ የስርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ባለ መሆኑ ዲሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም›› ይላሉ፡፡ ስህተት ነው፡፡ በዚህ ስሌት፤ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ የሚሆነው፤ የመንግስት ለውጥ ካመጣ ብቻ ነው፡፡ ሂደቱ ቀርቶ፤ ውጤቱ ታየ፡፡ ውጤቱ የህዝቡ ውሳኔ ነው፡፡ የውጤቱ ጥራት በሂደቱ ጥራት መመዘን አለበት፡፡ የምርጫ ሂደታችን የመንግስት ለውጥ ካልተደረገ›› ብሎ መመዘን ፍፁም ስህተት ነው፡፡ እርሱን ለህዝቡ እንተውለትና እኛ በሂደቱ ጥራት ላይ እናትኩር እላለሁ፡፡ ዜጎች አማራጭ ቀርቦላቸው፤ ስለ አማራጮቹ በውል መረዳት የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቶላቸው፤ ምርጫቸውን በነፃነት መግለፅ በመቻላቸው እንጂ የመንግስት ለውጥ በመፈጠሩ እና ባለ መፈጠሩ፤ የምርጫን ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ መሆን መዳኘት ተገቢ አይደለም፡፡
ጋሼ፤
ሌላም ምሳሌ ልስጥህ፤ የ2002 ዓ.ም ምርጫን አስመልክተው ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል፤ ‹‹ኢህአዴግ 99 በመቶውን የፓርላማ ወንበር አሸነፍኩ ብሏል፡፡ እንዲህ ያለ ውጤት በሌሎች ሀገሮች ታይቶ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ አይደለም›› ብለዋል፡፡ ይህም ስህተት ነው፡፡ ይህን አስተያየት ‹‹ብዙ ሰዎች ኢህአዴግን ሊመርጡት የቻሉት ቢገደዱ ነው›› ከሚል መነሻ የመጣ ወይም እንዲህ ያለ አመለካከት ለመፍጠር ታስቦ የተሰነዘረ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ‹‹ኢህአዴግ 99 በመቶውን የፓርላማ ወንበር ያሸነፈው፤ ከመራጩ ህዝብ የ99 በመቶውን ድምጽ ስላገኘ አይደለም፡፡ በየምርጫ ጣቢያው፤ ከሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ጋር በንጽጽር ታይቶ አብላጫውን ድምፅ ስላገኘ ብቻ ነው፡፡ ይህ ስሌት የምርጫ ሂደቱን ጥራት አያሳይም፡፡ በእኛ ሀገር ላለው የምርጫ ስርዓት (First past the post) ትርጉም የለውም፡፡ ለምሳሌ፤ ኢህአዴግን ጨምሮ 4 ፓርቲዎች የተወዳደሩበትን የምርጫ ሂደት እናስብ፡፡ በአጠቃላይ 10 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ እንበል፡፡ በእያንዳንዱ ጣቢያ 100 መራጮች ቢኖሩ፤ በድምሩ 1000 መራጮች ይሆናሉ፡፡ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ከተመዘገቡት 100 መራጮች ውስጥ ለየብቻ ለተወዳደሩት ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች 60 ሰዎች ድምፅ ቢሰጧቸው ቀሪዎቹ 40 ሰዎች ኢህአዴግን መርጠዋል ማለት ነው፡፡ ሦስቱ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው 20 ድምፅ ሲያገኙ፤ ኢህአዴግ በ40 ድምፅ አብላጫውን አግኝቶ አሸናፊ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ ከ10 ጣቢያዎች በዘጠኙ ቢከሰት፤ ኢህአዴግ 99 በመቶውን ወንበር አሸናፊ ይሆናል፡፡ ከ1000 ሰዎች 360 ሰዎች መርጠውት 99 በመቶውን ወንበር አሸናፊ ሆነ ማለት ነው፡፡ የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት ከተወዳደሩት ፓርቲዎች ውስጥ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ አሸናፊ የሚሆንበት ስርዓት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ፓርቲዎች በአገኙት ድምፅ ልክ ወንበር የሚከፋፈሉበት የምርጫ ስርዓት አለ፡፡ በዚህ ስርዓት የሚመራ ምርጫ ቢሆን ውጤቱ ይቀየራል፡፡ ስለዚህ 99 በመቶውን ወንበር ያሸነፈው 99 በመቶ መራጮች ስለ መረጡት አይደለም፡፡ ከሌሎች ጋር በንፅፅር ሲታይ የአብላጫውን ድምፅ ሰጪዎች ድጋፍ ስላገኘ እንጂ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዓላማ አንድነት ሳይኖራቸው ህብረት ሲፈጥሩና ሲፈርሱ የምናየው ለዚህ ነው፡፡   
ለዚህ የሚሰጡት አስተያየቶች ከተጨባጭ ሁኔታ እና ከሀገራቱ የምርጫ ስርዓት ጋር ተገናዝበው ካልታዩ በቀር ያሳስታሉ፡፡ ዋናው ነገር የሀገሪቱ የምርጫ ስርዓት፣ መዋቅር፣ አስተዳደር እና አደረጃጀት፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በፓርላማ ውስጥ የሚይዙትን ወንበር የተለያየ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ሌሎች የሚነሱ ነጥቦችም አሉ፡፡ እነሱን ከሌሎች ጉዳዮች ጋር አያይዤ አነሳቸዋለሁ፡፡