ህዝበ ሙስሊሙ የአሻባሪዎች መሸሸጊያና ሰለባ አይሆንም!

  • PDF

ሲኢድ መሐመድ (የካቲት 11/2005)


ሼህ አህመዲን መሐመድ የ45 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። አባታቸወ ሃጂ መሐመድ ትውልዳቸውና እድገታቸው ወሎ ነበር። የእስልምና ሃይማኖት መምህር ነበሩ። በዚህ ምክንያት የሼህ አህመዲን የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት የጀመረው ከቤታቸው ነበር፤ ከልጅነት እስከ እውቀት በሃይማኖት የኖሩና የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮን ለሌሎችም በማካፈል ቀላል የማይባል ተግባር ያከናወኑ ናቸው። የማስተማሩን ስራ የጀመሩት ገና ከወጣትነት ዕድሚያቸው ጀምረው ነበር። አሁንም የማስተማሩን ስራ አላቆሙም። 

ሼህ አህመዲን ከአንድ የቀድሞ ወዳጃቸው ጋር ሃይማኖታዊ ውይይትና ክርክር ያደርጉ እንደነበርና ይህን ሃይማኖት ለበስ የነበረውን ግንኙነታቸውንም በቅንነት ይቀበሉት እንደነበር ያጫወቱኝ በቅርቡ ነበር። ይህ የቀድሞ ወዳጃቸው ይነግራቸው  የነበረውን ሃሳብ በየዋህነትና ለሃይማኖቱ ባላቸው ቀናኢነት ስውር ተያያዥ ነገር ሊኖረው እንደሚችል ሳይጠራጠሩ ቀላል ለማይባል ጊዜ አብረው ሲከራከሩና ሲወያዩ ኖረዋል።

“ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ግን  የግለሰቡ ዓላማ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ እንደሌለው ቀስ በቀስ መገንዘብ ቻልኩ፣“ ይላሉ ሼህ አህመዲን። ለዚህ ደግሞ በውይይታቸው አብዛኛውን ጊዜ ከወዳጃቸው ይቀርብ የነበረው ሃሳብ እስላማዊ ተልእኮ እንዳልነበረው  ለመገንዘብ በመቻላቸው በሁለቱ መካከል የሃሳብ ልዩነት እየሰፋ በመምጣቱ  አይንህን ላፈር ተባብለው መለያየታቸውን ያስታውሳሉ። ሼህ አህመዲን የጠለቀ የሃይማኖት እውቀት ስላላቸው በዚህ መልክ ፈጥነው መለያየት ቢችሉም ግለሰቡ በሃይማኖት ስም መነገዱን በመቀጠል አንዳንድ የዋሆችን ዛሬም ድረስ እያሳሳተ እንደሆነ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። 

ሁሉን ነገር ለአላህ መተውና በንጹህ ልቦና ሰውን መቅረብ  አንድ አማኝ ማድረግ ከሚጠበቅበት ነገሮች አንዱ ነው የሚል እምነት ስለነበረኝ “አንዳንድ ሰዎች  ከሰው ጋር በምናደርገው ግንኙነት መጠራጠር አስፈላጊ ነው፣“ የሚል ሃሳብ ሲያነሱ  በጣም ይከፋኝ ነበር።  አሁን ግን አንዳንድ ሁኔታዎችን መጠራጠርና ነገሮችን ከስር መሰረቱ አጣርቶ ትክክክለኛውን መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ ከሕይዎት ተሞክሮዬ ለመረዳት ቻልኩ። ይላሉ ሼህ አህመዲን።

ህዝበ ሙስሊሙን መቋጫ ወደ ሌለው ደም መፋሰስ  ለማስገባት በተቀደሰው የእስልምና ሃይማኖት ሽፋን ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርጉ  የነበሩ አሸባሪዎችና ጽንፈኞች አሁን ማንነታቸው ይፋ ሆኗል። ይዘዉት የነበረው ህቡእ አጀንዳ ከሃይማኖታዊ ተልእኮ ጋር ምንም ዓይነት ተያያዥነት አንደሌለውም በተጨባጭ እየተረዳነው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሼህ አህመዲን እንዳጫወቱኝ "በሌሎች ሰዎች የሰማሁት ቢሆነ ኖሮ ጥርጣሬ ውስጥ እገባ ነበር፣ አሁን ግን ይፈጽሙት የስለነበረው ተግባርና ለምን ይፈጽሙት እንደነበር ከሁለተኛ ወገን ሳይሆን አንዳንዶች ተሳስተውና ተታለው ማድረጋቸውን ከአንደበታቸው ሲናገሩ የሰማሁባቸው አጋጣሚዎች ለራሴ ብዙ አስተምሮኛል፣" ነበር ያሉኝ።

በተለያየ ጊዜ በሃይማኖት ሽፋን እየተነሳ ያለው የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ሃይማኖታዊ መሰረት እንደሌለው መላው ህዝብ ከተገነዘበ የቆየ ቢሆንም አንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች ለሃይማኖታቸው ካላቸው ቀናኢነት የተነሳ አሸባሪዎቹ የሚያነሱትን ሃይማኖት ለበስ ጥያቄ እውነት አድረገው  ያለምንም ማቅማማት  የወሰዱ  መኖራቸው የሚካድ አይደለም።

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ እየጎላ መምጣቱም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነበር። ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ህቡእ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ ባደረጉት ዘመቻ ጥቂቶችን አሳስተዋል። በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት  ከተመዘገቡ በርካታ መሰረታዊ ለውጦች አንዱ የሃይማኖት ነጻነት መረጋገጥ ነው። በዚህም መሰረት ዜጎች የመረጡትን  ሃይማኖት ያለአንዳች ተጽእኖ የማምለክና ሃይማኖታዊ ተልእኳቸውን ያለምንም መሸማቀቅና መፈጸም የሚያስችላቸው መብት ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት በግልጽ እንዳሰፈረው ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊና እና የሃይማኖትና እምነት ነጻነት አለው።

ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ወይም ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን እንደሚያካትት ያስረዳል። በተጨማሪም ማንም ሰው የሚፈልገውን እምነት ያለውን ነጻነት  በሃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል እንደማይቻል በግልጽ ተደንግጓል።  በመሆኑም ከሃይማኖት ነጻነት ጋር ተያያዥነት ያለው ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችል ክፍተት እንደሌለ እሙን ነው። ይሁንና አክራሪዎች የአገራችንን ሰላም ለመበጥበና ለማወክ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል። ይሁን እንጂ  “ስንቅና ውሸት እያደር ይቀላል” እንዲሉ እኩይ ምግባራቸው ውሎ ሲያድር ግሃድ ወጥቷል።

ቀደም ሲል መንግስትንና ህዝበ ሙስሊሙን ለማለያየት ቀላል የማይባል ዘመቻ አካሂደዋል። መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የማይገባበት፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ እጁን የማይቀላቅልበት ስርዓት ተፈጥሮ ተግባራዊ እየሆነ ባለበት ወቅት ህገመንግስቱን የሚንድና የሌሎች እምነት ተከታዮችን ህገመንግስታዊ መብት የሚጥስ አካሄድን ለመከላከል የሚወስዳቸውን የአስተምህሮትና ሕግን የማስከበር ተግባራት ጣልቃ እንደመግባት አድርጎ በማቅረብ አማኞችን ለማደናገር ጥረዋል።

ጉዳዩን አንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እንዲያራግቡት በማድረግ አሸባሪነት  እንዲስፋፋ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በአገራችን ሰላምን ለማደፍረስ  ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል። አሸባሪዎቹ  የእስልምና ሃይማኖትን ለምድ ለብሰው  በአገራችን ህዝበ ሙስሊሙን እርስ በርስ ለማበጣበጥና የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን በመፈጸም ረገድ ረጅም መንገድ ተጉዘዋል።

በአገሪቱ ለዘመናት የዘለቀውን የሃይማኖ መቻቻል በማደብዘዝ በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ደም መፋሰስንና ግጭትን ለማቀጣጠልና ብሎም ህዝበ ሙስሊሙን ከመንግስት ጋር ለማለያየት በማቀድ የቻሉትን ያህል ተንቀሳቅሰዋል።

የከሰሩ ፖለቲከኞች በእምነት ተቋማት እየተገኙ ከእምነቱ አስተምህሮ የተለየ ነገር  በሚያቀርቡበት ወቅት ምእመኑ እንደ ወረደ ከመቀበል ይልቅ የተለያዩ ጥያቄዎችን  በማንሳትና በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በማየት አሸባሪዎቹ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ተልእኮ እንደሌለላቸው በውል መገንዘብ ችሏል፡፡ መንግስት  ሃይማኖት ላይ የሚያደርገው ምንም ዓይነት ጫና እንደሌለ የሚያየው የእምነቱ ተከታይ ህዝብ  ለምን? ማለት ከጀመረም ቆይቷል። 

“ሃይማኖታዊ ተልእኳችንን በነጻነት እያራመድን እስከሆነ ድረስ ለምን በእምነት ቦታዎቻችንና በሃይማኖታችን ስም  የፖለቲካ ስብከት ይሰበካል?  በእምነት ስፍራዎቻችን ለምን ሃይማኖታዊ ተግባራትን ብቻ አንፈጽምም?” የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አማኞች ቁጥር  እየጨመረ በመምጣቱ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የታቀደው ሴራ  ሳይሳከ ቀርቷል። አሸባሪዎቹ በተለያየ ስልት ያደረጉት ጥረት ለዘመናት የዘለቀውን የሕዝቦችን  የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል ሰብሮ ዓላማቸውን ሊያሳካላቸው ግን አልቻለም።

በቅርቡ በአወሊያ ትምህርት ቤት  ወጣቱን በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን በማታለል ከጎናቸው ለማሰለፍ አቅደው ተንቀሳቅሰዋል። ወጣቱን ከመንግስት ጋር ለማጋጨትና ብጥብጥ ለመጫር በእጅጉ ጥረዋል። የትምህርትና የሥራ ተቋማትና ስፍራዎች ከማናቸውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮና የአምልኮ ማካሄጃነት የጸዱ መሆን እንዳለባቸው በግልጽ ተደንጎ እያለ በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ስራን በትምህርት ቤቶች ለመስራት ያልበጠሱት ቅጠል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።

የኢትዮጵያ ሙስሊም ህብረተሰብ  የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ ያውቃል። በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ልማት ቱርፋት ተቋዳሽ ሆኗል።  ሰላሙን ከምንም በላይ ይፈልገዋል። እነዚህ ወገኖች ይህ ጠፍቷቸው ባይሆንም የኢትዮጵያን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማደናቀፍ የማይሞከር ነገር መኖር የለበትም በሚል እምነት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

አሸባሪዎቹ የእስልምና ሃይማኖትን ለድብቅ  አጀንዳ ማስፈጸሚያነት  መጠቀምን  ለምን መረጡ?  ተግባራቸው በተደጋጋሚ እየተጋለጠ ለምን መቋጫ አላገኘም?  አማኞች እምነቱ ከሚያዘው ውጭ የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማቸው ለምን አፋጣኝ እርምጃ አልተወስደም? የሚሉትንና  ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስ ተገቢነት ይኖረዋል።

ሃይማኖታዊ የመሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አማኞች ውስጥ ሰርጎ በመግባት በመርዝ የተለወሰ ማር  ለማጉረስ ጥረት ማድረግ ያዋጣል የሚል እምነት በመያዝ ጽንፈኞችና የከሰሩ ፖለቲከኞች በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የእልቂትና የትርምስ ጥሪ ለማስተላለፍ ሲጥሩ ተስተውለዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሃይማኖት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች መቋጫ አይኖራቸውም በሚል እምነት ህዝቡን ወደማያባራ ግጭትና ሁከት ለማስገባት በማቀድም ሃይማኖት አዘል ጥያቄዎችን በማንሳት በጥፋት አቅጣጫቸው ገፍተውበታል።

የሚያነሷቸው አጀንዳዎች ትክክለኛ የሃይማኖት ጉዳይ መስለው እንዲታዩ በየወቅቱ ከሚከሰቱ ሁነቶች ጋር እያቆራኙ  ከማቅረባቸው በላይ በእያንዳንዱ እምነት ውስጥ ለተሰገሰጉ አባሎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብና አንዳንድ ፈሪሃ ፈጣሪ የራቃቸው አማኞችንም  በገንዘብ ሃይል በማታለል የእነሱን ፍላጎት እንዲያራምዱ ለማድረግ ይጥራሉ። ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ ያነሷቸው ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተልእኮ እንደሌላቸው  ግልጽ ቢሆንም ከውጭ በሚያገኙት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍና ስልታቸውን በመቀያየር  አፍራሽ ተልእኳቸውን ለማሳካት ጥረት አድርገዋል።

በሃይማኖት ሽፋን ከሚነሱ አንዳንድ የፖለቲካ ውዥንብሮች ውስጥ ጥቂቶች  የሃይማኖቱ አማኞች በፍጥነት ራሳቸውን የማያጸዱበት አንዱ ምክንያትም ራሳቸውን ለጥቅም አሳልፈው የሰጡና  በመካከላቸው የተሰገሰጉ ጽንፈኞች እነሱን መስለው ስለሚቀርቧቸው ነው። የእስልምናም ሆነ የክርስትና  ሃይማኖት አስተምህሮቶች  አንድ አማኝ  ለሁለት ነገር  መገዛት አይቻልም ይላሉ። ገንዘብንም ፈጣሪንም በአንድ ጊዜ መውደድ አይቻልም። ለገንዘብ ያደረ አምላክን ክዷል፤ ገንዘብን የናቀ አምላክን ወዷል። አንዳንድ  አማኞች ለገንዘብ በመገዛት ሌላውን  አማኝ ለማሳመን ጥረት ስለሚያደርጉ የሃይማኖቱ ተከታዮች የጉዳዩን ውስጠ ምስጢር ለማወቅ ጊዜ ይወስድባቸዋል።

የሆነ ሆኖ የጽንፈኞች እኩይ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተጋለጠ በመምጣቱ በውስጥ ሰንቀውት የነበረው  ህቡእ አጀንዳ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ የያዘ መሆኑን መላው ሕዝብ ከተገነዘበ ውሎ አድሯል። በሃይማኖት ስም የሚካሄድ የሽብር፣ የሁከትና የጦርነት አስተምህሮና ተግባሩ ሊፈቀድ እንደማይገባ መላው ህብረተሰብ መገንዘብ ችሏል። በዛሬዋ ኢትዮጵያ አሸባሪዎች በአገራችን መሰረት ይዘውና በስውር የፖለቲካ አጀንዳ እንሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የሚዘውሩት የህብረተሰብ ክፍልና ይኖራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።