ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ስኬት በትጋት እንደሚሰሩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2005 (ዋኢማ) - ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ እና የትግራይ ህዝብ ዛሬም እንደትናንቱ አንድነታቸውን በማጠናከርና ቃል ኪዳናቸውን በማደስ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ስኬት በትጋት እንደሚሰሩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ ።

ህወሓት የተመሰረተበትን የካቲት 11 ቀን 38ኛው ዓመት ምክንያት በማድረግ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊንና በትግሉ የተሰው ሰማዕታትን አደራ ድርጅቱና ህዝቡ በሚገባ ይጠብቃሉ ።

የትግራይ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሓት እየተመራ በተዓምራዊ የትግል ጽናትና ጀግንነት የትጥቅ ትግሉን በማጠናቀቅ የልማት፣ የዲሞክራሲና የሰላም ዋንኛ እንቅፋት የሆነውን የደርግ ስርዓት በመገርሰስ በየጊዜው እየታደሰና እየጎመራ መምጣቱን መግለጫዉ አመልክቷል ።

የዘንድሮው የህወሓት ምስረታ በዓል የሚከበረው በክብርና በጽናት ያለፉት ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ በሌሉበት ቢሆንም ጀግናው መሪያችን በሰሩት ህዝባዊ ገድል ዛሬም፣ ነገም ምንጊዜም ከህዝብ ልብ ውስጥ አይጠፉም ብሏል መግለጫዉ ።

የድርጅታችንን የምስረታ በዓል ስናከብር በየምዕራፉ ሲያጋጥሙን የቆዩትን ውስብስብና መራራ መሰናክሎችን በህወሓት የጠራ መሰመር እና በክልሉ ህዝብ የትግል ጽናት ለመወጣት ተችሏል ብሏል የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት ከትግራይ ህዝብ አልፎ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ መሪር ሀዘን ቢያሳድርም የአንድነት ህዝባዊ ማዕበል በመፍጠር ለተከበረ ስብእና፣ ለትግል ጽናትና በሳል አመራር ህዝቡ የሰጠው ምላሽ ጽናት ሰጥቶናል ብሏል መግለጫዉ ።

በአቶ መለስ በከፍተኛ የትግል ወኔና ጽናት ''ዘመቻ መለስ ለእድገትና ለእምርታ'' በሚል መሪ ቃል ወደ ስራ በመግባትና የክልሉን ህዝብ በልማት ሰራዊት በማነሳሳት ለተፈጠረው ህዝባዊ ማዕበል ህወሓት አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱንም መግለጫው አመልክቷል ።

ቀንደኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማጥፋት መለስ በቀየሰዉ ጎዳና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማያጠራጥር ሁኔታ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ የልማት ጉዞ ላይ እንገኛለን ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው።

በገጠርና በከተማ ያለው የትግራይ ህዝብ ዛሬም እንደትናንቱ ተዓምራዊ የልማት ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝና ይህንንም በማጠናከር በተለይ የታላቁ መሪ ዋንኛ ዓላማ የነበሩ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ፣ እናቶችን ሞት የመቀነስና ሌሎች ስራዎችን እውን በማድረግ ብዙ ርቀት መጓዝ መቻሉን አመልክቷል ።

የዘንድሮው የህወሓት የምስረታ በዓል የሚከበረው የድርጅቱ 10ኛ ጉባኤ በሚካሄድበት ዋዜማ ላይ ሆነን ነው ያለው መግለጫው፣ መለስና ሌሎች ሰማእታት የህዝብ ልጆች የሰጡንን አደራ ይበልጥ እንዲጎመራ የምንረባረብበት ጊዜ እንደሚሆንም አንጠራጠርም ብሏል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ መግለጫው በመጨረሻም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጽናት በመቆም ለሀገራችን ህዳሴ መረጋገጥ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል ።