ኢትዮጵያ ያሏትን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለውጭ ባለኃብቶች በስፋት ማስተዋወቅ ይጠበቅባታል-የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር

  • PDF

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2005/ዋኢማ/ - ኢትዮጵያ ያሏትን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለኃብቶች በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባት የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርክ ሳይመንድስ ገለፁ፡፡

ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘውንና በእንግሊዝ ባለኃብቶች የተቋቋመውን ፒታርድስ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ፋብሪካ በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት ኢትዮጵያ በተለይም በግብርናና በኢነርጂ ዘርፎች ያሏትን ዕምቅ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በማስተዋወቅ የውጭ ባለሀብቶችን በይበልጥ መሳብ ይጠበቅባታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አመርቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደምትገኘ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ ይህን የጀመረቸውን ፈጣን ዕድገት የውጭ ባለኃብቶችን በስፋት በመሳብ ልታጠናክረው ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ መምጣቱን የገለፁት ሚኒስትሩ የሁለትዮሽ ትስስራቸው በጠንካራ መሰረት ላይ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ የልማት ትብብር ከሚደረግላቸው አገራት መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ናት ያሉት ሚኒስትሩ የምታገኘውን የልማት ድጋፍ ለጀመረችው የዕድገት ጉዞ በትክክል እያዋለች እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡

አገሪቱ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ በሚገባ ለማሳካት እንዲያስችላት ተጨማሪ ማበረታቻዎች ሊደረጉላት እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ድህነትን በማስወገድ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚያስገኙ የቢዝነስ ፕሮጀክቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አስምረውበታል፡፡

በዚህ ረገድ እንግሊዛውያን ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እንዲሳተፉ ለማድረግ መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

እንግሊዛውያን ባለኃብቶች ኃብታቸውን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ የእንግሊዝ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን አገሪቷ ያላትን ምቹ የኢንቨትመንት አመራጮች በስፋት ለባለኃብቶቹ ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባትም አመልክተዋል፡፡

ፒታርድስ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ፋብሪካ ከተቋቋመ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ እንዳስቆጠረና በአንድ ወር 100 ሺ የተለያዩ ዓይነቶች የቆዳ ጓንቶችን በማምረት ወደ አሜሪካ እንደሚወክና ለ414 ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ዋና ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ፀደንያ መክብብ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡