የወለጋ ስታዲዮም ግንባታ ከ71 በመቶ በላይ ተጠናቀቀ

  • PDF

ነቀምት፤ የካቲት 5/2005/ዋኢማ/ - በነቀምት ከተማ በ208 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የወለጋ ስታዲዮም ግንባታ በአሁኑ ወቅት 71 በመቶ ያህሉ መጠናቀቁን የኦሮሚያ ውኃ ስራዎች ድርጅት አስታወቀ።

በድርጅቱ የግንባታ ሳይት ማናጀር አቶ ሰለሞን ለገሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ከአራት አመት በፊት በ16 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የወለጋ ስታዲዮም ግንባታ አለም አቀፍ ደረጃ ያለው ነው።

ስታዲዮሙ በአስራ ሁለት ብሎኮች ከአስራ አንድ እስከ ሃያ ሰባት የሚደርሱ ደረጃዎች የሚኖሩት ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ ከሃያ ሺ በላይ ተመልካቾችን እንደሚያስተናገድ አስታውቀዋል።

ስታዲዮሙ በውስጡ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳን ጨምሮ የመሮጫ መም፣ የመረብና የቅርጫት  ኳስ ሜዳዎችና ሌሎች የስፖርት ሜዳዎች እየተዘጋጁለት መሆኑን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የትጥቅ መቀየሪያ፣ ቢሮዎች፣ የመታጠቢያ ቤቶች፣ ጂምና የኢሮቢክስ እንቅሰቃሴ ማካሄጃዎች፣ ካፊቴሪያዎች አካቶ መያዙንም ተናግረዋል።

የስታዲዮሙን ግንባታ በ2004 ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በበጀትና በግንባታ ቁሳቁስ እጥረት የተፈለገውን ያህል ሊራመድ አለመቻሉን ገልፀው፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ህብረተሰቡ ድጋፉን እያጠናከረ በመሆኑ ስራውን ለማጠናቀቅ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።