ቤተ ክርስቲያኗ የስድሰተኛውን ፓትሪያርክ የምርጫ ሰሌዳ አወጣች

  • PDF

አዲስ አበባዕ፤ የካቲት 01/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእምነቱ ተከታዮች ስድስተኛውን ፓትሪያርክ የሚመረጡበትን የምርጫ የጊዜ ስሌዳ ማውጣቷን አስመራጭ ኮሚቴው አስታወቀ፤ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የጸሎት ሱባዔም ታውጇል፡፡

የፓትሪያርኩን ምርጫ ለማስፈጸም የተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጅማ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ ሐሙስ ጥር 30/2005 ዓ/ም እንደገለጹት የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅን መሪ ለመምረጥ ከየካቲት 1-24/2005 የሚቆይ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቷል፡፡

በዚሁ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከነገ ጀምሮ እስከ የካቲት 8 ቀን 2005 ድረስ ለቤተ ክርስቲያኗ ቅን መሪ ፈጣሪ እንዲሰጥ ካህናትና ምዕመናን በጸሎት እንዲጠይቁ የአንድ ሳምንት ሱባዔ ታውጇል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች ምዕመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ካህናት በዕጩ ፓትሪያርኩ ጥቆማ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ገልጸው፣ ከብጹዓን ሊቀጳጳሳት መካከል ፓትሪያርክ የሚሆኑትን ለመጠቆም ማንነታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ከየደብራቸው መያዝ እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ ዕጩ ፓትሪያርኩን ጠቋሚዎች በአካል በመቅረብ አስመራጭ ኮሚቴው ጽህፈት ቤት ማቅረብ እንደሚችሉም ገልጸው፣ ከአገር ውጭ ያሉት ግን በፋክስ ቁጥር 011-156711እና 011-1580540 ከየካቲት 1ቀን እስከ የካቲት 8 ቀን 2005 ድረስ ዕጩዎቹን መጠቆም ይችላሉ፡፡

በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የካቲት 16 ቀን 2005 አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚሰበሰቡና በአስመራጭ ከሚቴው ተጣርተው በሚቀርቡ አምስት ዕጩ ፓትሪያርኮች በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ላይ ተወያይተው የመጨረሻ ውሳኔም እንደሚሰጡም አቡነ እስጢፋኖስ አስታውቀዋል፡፡

በምርጫ ሕጉ በተወሰነው መሠረት በኢትዮጵያ የሚገኙ የ53ቱ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ሰብሳቢነት የአገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባዔ አራት ካህናት፣ አራት ምዕመናን፣አራት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ወስነው እንዲሁም የአገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ በድምሩ 13 አባላት በመምረጥ በአካል የካቲት 19ቀን 2005 አዲስ አበባ እንዲገኙ መላክ ይኖርባቸዋል፡፡

ፓትሪያርኩ በድምፅ የሚመርጡ ቁጥራቸው 800 የሚደርሱ ብጹዓን ሊቃነጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፣ ካህናት፣ ምዕመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ/ም በሚካሄደው የፓትሪያርክ ዋናው ምርጫ የዓለም ዐብያተ ክርስቲያናት ማህበር፣ የአፍሪካ ዐብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮች፣ የአራቱ እህት ቤተ ክርስቲያናት ተጠሪዎች ምርጫውን እንደሚታዘቡም ገልጸዋል፡፡

የምርጫው ውጤት በዕለቱ ከምሽቱ በ12 ሰዓት ለሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በፓትሪያርክነት የተመረጡ አባት በሦስተኛው ቀን በዓለ ሲመታቸው በቅድሰተ ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸምም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡