ሉሲ /ድንቅነሽ/ በመጪው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወደ አገሯ ትመለሳለች

  • PDF

አዱስ አበባ ጥር 30/2005 (ዋኢማ)- ለኢትዮጵያ የሰው ዘር መነሻ የዓለም አስደናቂ ቅርስ ሉሲ /ድንቅነሽ/ በመጪው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወደ አገሯ እንደምትመለስ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ሉሲ /ድንቅነሽ/እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 2006 ከአሜሪካ የሂውስተን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዚየም ጋር በተፈረመው ውል መሠረት ኤግዚቪሽን ተዘጋጅቶ በተለያዩ ስቴቶች በብዙ ሰዎች በመጎብኘት ላይ ትገኛለች፡፡

በሙዚየሙ አዘጋጅነት ከጥር 30 ቀን 2005 እስከ ሚያዝያ መጨረሻ በካሊፎሪነያ ግዛት በሚገኘው የባወረስ ሙዚየም ሉሲን ለመጨረሻ ጊዜ ለማሳየት ኤግዚቪሸን መዘጋጀቱን ሚኒስቴሩ ጠቅሷል፡፡
በኢግዚቪሽኑ ላይ ለመገኘት በሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃደር የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ ተጉዟል፡፡

በኢግዚቪሽኑ ላይ በኢትዮጵያ የሰው ዘር አመጣጥና ሉሲ የሁለቱን አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጠናከርና ለአገሪቷ የገፅታ ግንባታ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ በተመለከተ በተጋባዥ እንግዶች ውይይት ይደረጋል፡፡

ከኤግዚቪሽኑ በኃላ ሉሲ ወደ ኢትዮጵያ ትገባላች ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስቴሩ የላከውን መግለጫ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡