ባለሀብቶች የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ ለሃገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ ጥር 30/2005 (ዋኢማ) -በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ ለሃገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የበኩላቸውን ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወጪ ንግድ ዘርፍ እና በሃዋላ ማስተላለፍ ሥራ ላይ ተሰማርተው የላቀ የውጭ ምንዛሪ ላስገኙ 176 ባለሀብቶች ትናንት በሸራተን አዲስ ሽልማት ሰጥቷል፡፡

ባለሀብቶቹ የሠርተፍኬት ፣ የነሀስ ፣ የብር ፣ የወርቅ ፣ የፕላቲኒየም፣ የንስር እና የዝሆን ልዩ ሽልማት ተሸልመዋል፡፡

የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በረከት ስምዖን ባለሀብቶችንን ለማበረታታትና ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በዚህ የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ የአገሪቱ ኤክስፖርት በየዓመቱ ከ30 በመቶ በላይ እድገት እየተመዘገበ ነው ፡፡

ለአገሪቷ ፈጣን እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚያበረክተው የውጭ ምንዛሪ በላቀ መጠን ለማስገኘት መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በበኩላቸው ባንኩ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞችን እየደገፈና እያበረታታ ይገኛል ብለዋል፡፡ ባንኩ ለዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎቶች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ለወጪ ንግድ ግብዓት ለሚሆኑ ግብርና እና ግብርና ነክ ኢንዱስትሪና ለማኒፋክቸሪንግ ዘርፎች በማድረግ ጥረታቸውን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ላኪዎች በሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ ተወዳዳሪ የመግዣ ተመን በድርድር በመስጠት በባንኩ በኩል ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ችሏል ብለዋል፡፡
ባንኩ በተገበራቸው የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች የብድርና የዓለም ዓቀፍ የባንክ አገልግሎቶች ፈጣንና ምቹ እንዲሆኑ ማስቻሉን ጠቁመው በዚህም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በመላው አገሪቱ ከ625 በላይ ቅርንጫፎች ከፍቷል፡፡

ከተሸላሚዎቹ መካከል የሜድሮክ ወርቅ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አረጋ ይርዳው እና የቦሌ አትላንቲክ የሃዋላ አገልግሎት ባለቤት ሀጂ አብዱልውሃብ በየበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ አገሪቱ ከፍተኛ የወጭ ምንዛሪ እንድታገኝ በበለጠ ለመስራት እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡
ለተሻላሚዎቹ የመንግስት ባለስልጣናትና ሚኒስትሮች ሽልማት አበርክተዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሚኒስትሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡(ኢዜአ)