ኮሚሽነር ዓሊ ለአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ አባልነት ተመረጡ

  • PDF

አዱስ አበባ ጥር 30/2005 (ዋኢማ)-የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓሊ ሱለይማን የአፍሪካ ህብረት የፀረ- ሙስና አማካሪ ቦርድ አባል ሆነው ተመረጡ፡፡
አቶ ዓሊ ሱለይማን ለሁለት ዓመታት የአፍሪካ ህብረት የፀረ ሙስና አማካሪ ቦርድ አባል ሆነው እንዲያገለግሉ የተመረጡት ህብረቱ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ጥር 28 ቀን 2013 በአዲስ አበባ ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ መመረጧ ሀገሪቱ ሙስናን በመከላከልና በመዋጋት ረገድ እያካሄደች ላለው አበረታች እንቅስቃሴ እውቅና የሰጠ መሆኑን ያሳያል፡፡

እንዲሁም የሀገሪቷን የፀረ ሙስና ትግል እምነት የሚጣልበት መሆኑንና በትግሉ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት እንደሚያሳይ ለመረዳት መቻሉንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ለአፍሪካ ህብረት የፀረ- ሙስና አማካሪ ቦርድ አባልነት ከኢትዮጵያ የተመረጡትን ኮሚሽነር ዓሊ ሱለይማንን ጨምሮ ከኮትዲቯር፣ ከጋና፣ ከቶጎ፣ ከቡሩንዲ፣ ከሊቢያ፣ ከማሊ፣ ከቤኒን፣ ከናይጀሪያ፣ ከኮንጎና ከታንዛኒያ የተውጣጡ አስራ አንድ አባላት ተመርጠዋል፡፡

ለአባልነት ከቀረቡት እጩዎች መካከል አስራ አንዱ አባላት የተመረጡት ሙስናን ከመከላከልና ከመዋጋት ጋር በተያያዘ ያላቸው መልካም ስብዕና፣ ብቃት ፆታዊ ሁኔታና የአህጉሪቱን የተለያዩ ቀጠናዎች ውክልና ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት የፀረ ሙስና አማካሪ ቦርድ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በአህጉሪቱ ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንዲያገኙና በተጠናከረ ሁኔታ ሥራ ላይ እንዲውሉ መደገፍና ማበረታታት ነው፡፡

በአህጉሪቱ ሙስናና ተያያዥ ወንጀሎች ስለሚገኙበት ሁኔታ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ መተንተን፣ የሙስናን አደገኝነት አስመልክቶ የህዝብን ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ መረጃዎችን ማሰራጨት፣ በጉዳዩ ዙሪያ መንግሥታትን ማማከር የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም የተቀናጀ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሥነ ምግባር ደንብ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል ፣ሙስናን በመዋጋት ረገድ ከተለያዩ አካላት ጋር የሚደረጉ ትብብሮችና ውይይቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ ይገኙበታል፡፡

ፅህፈት ቤቱ ዳሬሠላም ታንዛኒያ ያደረገው የአማካሪ ቦርድ ሊቋቋም የቻለው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2003የወጣውን የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ኮንቬንሽን መነሻ በማድረግ ነው፡፡
የአሁኑ የቦርድ አባላት ምርጫ ሲካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን አንድ የቦርዱ አባል ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ሊመረጥ ኮሚሸኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው ዘገባ አመልክቷል ፡፡