በኢትዮጵያውያንና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለሃብቶች ጥምረት በ170 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ዘመናዊ የመድሐኒት ማመረቻ ተመረቀ

  • PDF

አዱስ አበባ ጥር 30/2005 (ዋኢማ)- በኢትዮጵያውያንና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለሃብቶች ጥምረት በ170 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ዘመናዊ የመድሐኒት ፋብሪካ ተመረቀ።

ፋብሪካው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ በተለምዶ ጃክሮስ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነባው ነው።
ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የፋብሪካው ግንባታ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እያደገ ስለመሆኑ ጠቋሚ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም እንዳሉት ፋብሪካው የሚያመርታቸው መድሐኒቶች ወደ አገር ውስጥ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
መንግስት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ከውጭ የሚያስገባቸውን መድሐኒቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ሰፊ የመድሃኒትና የመድሃኒት መገለገያ ቁሶች ፍላጎት መኖሩን የተጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ኩባንያው በሒደት በአፍሪካ ያለውን ገበያ የመጠቀም እድል እንዳለውም ጠቁመዋል።
መንግስት ፋብሪካው ወደፊት ለሚያደርጋቸው የማስፋፊያ ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች አመቺ ሁኔታ በመኖሩ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ጠይቀዋል።

የፋብሪካው ትልቁ ባልድረሻ የሆነው ጁልፋር ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አይማን ሳልህ እንዳሉት ደግሞ ፋብሪካው የሚጠቅምባቸው የማመረቻ መሳሪያዎች አለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉና ከአለም ጤና ድርጅት ጭምር እውቅና የተሰጣቸው ናቸው።
ፋብሪካው በአመት 350 ካፕሱል፣500 ሚሊዮን እንክብል እና 400 ሚሊዮን ሽሮፕ መድሃኒቶችን የማምረት አቅም ያለው ነው።ለ500 ኢትዮጵያውያንም የስራ እድል ፈጥሯል። የፋብሪካው መቋቋም ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጥራት ያለው መድሐኒት በዝቅተኛ ዋጋ እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት ፋብሪካው ኢትዮጵያ በያመቱ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባው መድሃኒት መካከል ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ ምንዛሪ ያድናል።

የጁልፋር ኩባንያ ሸሪክ የሆነው ሜዲቴክ ኢትዮጵያ የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር መሐመድ ኑሪ የፋብሪካው ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ሜዲቴክ ኢትዮጵያ ከፋብሪካው ድርሻ 45 በመቶ ያህሉን መያዙን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው በ350 ሚሊዮን ብር ለማስፋፋት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ 25 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ጥያቄ መቅረቡን አስረድተዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው ፕሮጀክት የቅድመ ጥናት ስራው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የተናገሩት ዶክተር መሃመድ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ አዲሱ የማስፋፊያ ፋብሪካ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።

ሁለተኛው የፋብሪካው ማስፋፊያ አንደተጠናቀቀ ምርቶችን ወደ ውጭ መላከ ይጀመራል። በፋብሪካው የምርቃ ስነ ስርዓት ላይ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አልካይማ ግዛት ልኡል ሼህ ፋይሰል ቢን ሳካር አልቃሲሚን ጨምሮ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ሚኒስትርም ተገኝተዋል። (ኢዜአ)