ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ እንደምትሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጹ

  • PDF

አዲስ አበባ ጥር 29/2005 (ዋኢማ) - ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬት ጋር ያላትን ግንኙነት በይበልጥ ለማሳደግ እንደምትሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው በአገሪቱን የውጭ ንግድ ሚኒስትር ሉብና ቢንት ካሊድ አልቃሲም የሚመራ የልዑካን ቡድን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግሥት የአገሪቱ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች መዋእለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚያደርጉትን ጥረት ትኩረት ሰጥቶ ያግዛል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉ ቢሆንም፤ ባለሃብቶች በተለይ በግብርናና በማምረቻ ኢንዱስትሪ (በማኑፋክቸሪንግ) ዘርፍ ቢሳተፉ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ውይይቱን የተከታተሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡

የውጭ ንግድ ሚኒስትሯ ሉብና ቢንት ካሊድ አልቃሲም በበኩላቸው የአገራቸው ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት፣በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም ጁልፋር የተሰኘ የአገራቸው ኩባንያ ከኢትዮጵያው ሜዲቴክ ኢትዮጵያ ኩባንያ ቅንጅት የተገነባውን የመድኃኒት ፋብሪካ ላይ ለመመረቅ ነው፡፡
ኩባንያው በ50 አገሮች ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ሲሆን፣ በቀጣይም በዘርፉ በስፋት ለመሳተፍ ዕቅድ እንዳለውም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡