የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ያስቀደመው የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት

  • PDF

አሸናፊ ደመቀ

የዛሬውን አያርገውና የደቡብ ኦሞ፣ የቤንች ማጂ እና ከፋ ዞን ይቅርና ገጠራማ የአርብቶአደር እና አርሶ አደር ቀበሌዎች የዞኖቹ እና ወረዳዎቹ ከተሞች ለተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችና ማኀበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ባይተዋር ነበሩና ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ወደ እነዚህ ቦታዎች ለሥራ በምደባም ሆነ በሹመት መሄድ እንደ ቅጣት ይወሰድ ነበር፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ”መሄዴ ነው ማጂ
መሄዴ ነው ማጂ
አንተን ተከትዬ እንደ እናቴ ልጅ” ተብሎ ስንኝ ተቋጥሮ
የሠርግ ማድመቂያ፣ የሙሽሪት የፍቅር መስዋዕትነት መገለጫ ሆኖ የትዳር ጓደኛዋን ተከትላ ወደ ቤንች/ማጂ እና ሌሎች የተጠቀሱት ቦታዎች  ለመሄድ ፈቃደኛ መሆንዋ የመስዋዕትነቷ አስረጂ ሆነው ይቀርቡ የነበሩ የአገራችን ክፍሎች  ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ ምንም እንኳ አንፃራዊ በሆነ መልኩ የዞኖቹ ከተሞች በርካታ ተስፋ ሰጪ የዕድገት ጭላንጭል ማሳየት ቢጀምሩም ገጠራማ ቀበሌዎቻቸው ግን ከመሠረተ ልማት አውታሮችና ማኀበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር ሳይተዋወቁ እስካሁን ዘልቀዋል፡፡ አሁን ላይ ታዲያ ከላይ የተቋጠረውን ስንኝ የሚያስቀይር የልማት ጥንስስ ተጠንስሶ የልማት ቀጠና መሆን ጀምረዋል፤ ለልማት ከጫፍ ጫፍ የአገራችን ክፍሎች ዜጎች ለሥራ የሚተሙባቸው ቀጠናዎች ሊሆኑ ድግስ ተደግሶ ሁኔታዎች መቀየር የጀመሩባቸው እንደ ደቡብ ኦሞዋ ሳላማጎ ያሉ  ገጠራማ ወረዳዎች ላይ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ተራ ጠባቂ የሆኑ የተጠቀሱት ዞኖች ሌሎች ወረዳዎች ነዋሪዎች በጉጉት የሚጠብቁት የልማት ድግስ ተጀምሯል! የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ኦሞዋ ዞን በሰላማጎ ወረዳ ሞቅ ደመቅ ብሎ በመጧጧፍ ላይ ይገኛልና!!

የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አምስት የስኳር ፋብሪካዎች የሚገነቡበት ፕሮጀክት ሆኖ ሲታቀድ መጠነ ሰፊ ጥቅም ላይ ያልዋለ ለሸንኮራ አገዳ ተስማሚ ይዘት ያለው ሰፊ መሬት፣ በውኃ መቀልበሻ ዊር ከኦሞ ወንዝ ተጠልፎ የሚገኝ አስተማማኝ የውኃ ሀብት እና ለስኳር ልማት ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት በእነዚህ ፕሮጀክቱ በሚካሄድባቸው የደቡብ ኦሞ፣ የቤንች ማጂ እና የከፋ ዞን የተመረጡ ወረዳዎች መኖሩ ተጠንቶ ነው፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ከተመረጡት የሳላማጎ እና ኛንጋቶም ወረዳዎች መካከል በአሁኑ ወቅት በሳላማጎ ወረዳ የስኳር ልማት እንቅስቃሴው በስፋት በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየደረጃውም ልማቱ እየተስፋፋ ወደ ከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ እና ወደ ቤንቺ ማጂ ዞን የሱርማ እና ሜኢኒትሻሻ  ወረዳዎች እንዲስፋፋ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ እናም በሳላማጎ ወረዳ ከስኳር ልማቱ ሥራ ጎን ለጎን ስኳር ኮርፖሬሽን ለዘመናት ከማኀበራዊ ተቋማት አገልግሎትና ከመሠረተ ልማት አውታሮች ጋር ሳይተዋወቁ የኖሩትን በወረዳዋ የሚኖሩ የቦዲ፣ ሙርሲ፣ ባጫ እና ዲሜ  ብሔረሰቦች እጅግ ፈታኝ የሆነ የዕለት ከዕለት አኗኗር ሁኔታ የሚቀይሩ ተግባራትን እያከናወነ በመሆኑ ሌሎች ልማቱ ወደፊት የሚደርስባቸው ወረዳዎች ነዋሪዎች ልማቱ ተፋጥኖ ወደ እነርሱ የመድረሱን ጉዳይ በጉጉት እየጠበቁት ይገኛሉ፡፡ አዎ! ለሳላማጎ ነዋሪዎች የፈነጠቀ የልማት ጮራ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሰጠ ነበርና!!፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን በሳላማጎ ወረዳ የስኳር ልማት እንቅስቃሴውን ሲጀምር ከዚሁ ጎን ለጎን ምናልባትም የቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ኋላ ቀር በሆነ የአኗኗር ሁኔታ ለሚኖሩት የወረዳዋ ነዋሪዎች የተለያዩ የማኀበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ነበር የተንቀሳቀሰው፣ ነዋሪዎችም የዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ቀላል እንዲሆን ኮርፖሬሽኑ ስለገነባቸው ማኀበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ወ/ሮ ኮሞቶሪያ ጣጣይ ሲናገሩ “ከዚህ በፊት ወፍጮ ቤትም ሆነ ውኃ አገልግሎት የለም ነበር፤ እህል በእጃችን ፈጭተን እንዲሁም ውኃ ስንፈልግም ብዙ ርቀት ተጉዘን በመሄድ ኦሞ ወንዝ ነበር የምናገኘው፡፡ አሁን ግን ስኳር ኮርፖሬሽን በወረዳችን በአልጎቢያ ቀበሌ ነፃ የወፍጮ አገልግሎት እና የንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት እንድናገኝ አድርጎ በፈለግነው ሰዓት እየተጠቀምንባቸው ነው፡፡ ከቦታ ቦታ ለእኛም ሆነ ለከብቶቻችን ውኃ ፍለጋ መዞር ስለማያስፈልገን በመንደር ተሰባስበናል፤ በዚህም ያሉኝ ሁለት ልጆች ኮርፖሬሽኑ በቀበሌያችን አልጎቢያ በሠራው ት/ቤት ገብተው መማር ጀምረዋል” ይላሉ፡፡

ሌላዋ በወረዳዋ የአልጎቢያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አላይካት ሙኒሲ በበኩላቸው “የወፍጮ እና የንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት በቅርባችን ማግኘት የቻልነው የስኳር ልማቱ እዚህ በመጀመሩ ነው” በማለት “ዛሬ የወፍጮ እና የውኃ አገልግሎት ማግኘት መቻላችን መንግሥትን እንደ እግዚአብሔር እንድናየው አድርጎናል” ሲሉ ስኳር ኮርፖሬሽን በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላት ጋር በመቀናጀት እያቋቋመላቸው ባሉ ማኀበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ወ/ሮ አላይካት አያይዘውም “የመንግሥት ኃላፊዎች መጥተው ስለልማቱ ካወያዩን በኋላ ተስማምተን ነው በመንደር የተሰባሰብነው፤ መንግሥት ወፍጮ፣ የውኃ አገልግሎት መስጫ፣ ት/ቤት፣ ጤና ተቋም፣ ወዘተ. ካቋቋመ በኋላ ነው በመንደር የተሰባሰብነው” ሲሉ  ይገልፃሉ፡፡ ከሁለቱ ልጆቻቸው መካከል አንደኛው በመንደሩ በተከፈተላቸው ት/ቤት ገብቶ መማር የጀመረ መሆኑንና ሌላኛዋ ሴት ልጃቸው ገና ሕፃን በመሆኗ ት/ቤት አለመግባቷን ወ/ሮ አላይካት በመግለጽ ይህን ሁሉ ማግኘት የቻልነው በመንደር በመሰባሰባችን ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን በሰላማጎ ወረዳ የገጠር ቀበሌ በሆነችው አልጎቢያ ቀበሌ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት አስገንብቶና ቁሳቁሶችን አሟልቶ እንዲሁም የወረዳ እና የዞን መስተዳድር የሚመለከታቸው አካላት መምህራንን ለት/ቤቱ መድበው ትምህርት ቤት ምን እንደሆነ የማያውቁ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ጀምረዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ተወካይ ርዕሰ መምህር አቶ አለማየሁ አበራ ሲናገሩም ”ትምህርት በተጀመረበት ታሕሣስ 10 ቀን 2005 ዓ. ም. 35 ተማሪዎችን ተቀብለናል፤ ለአርብቶ አደሩ ልጆቹን ወደ ት/ቤት የመላክ ጉዳይ አዲስ ነገር ነው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቅስቀሳ ሥራ እየሠራን ነው የምንገኘው” ይላሉ፡፡

መምህር ኦኒዮ ጫኖ በበኩሉ  ”የዚህ አካባቢ ተወላጅ በመሆኔ የማስተማር ሥራዬን በጥሩ ሁኔታ ተወጥቼ ይህ ት/ቤት ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ማዬት እጓጓለሁ” በማለት አርብቶአደሩ ልጆቹን ወደ ት/ቤት እንዲልክ ተቀባይነት ባላቸው የአካባቢው ተወላጆችና የአገር ሽማግሌዎች አማካይነት የቅስቀሳ ሥራ በመሥራት እየተሳተፈ እንደሚገኝም ይገልፃል፡፡ ”በወረዳችን በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ስለማያውቅ በዚህ አጋጣሚ ስኳር ኮርፖሬሽን እያከናወነ ላለው አኩሪ ተግባር ምስጋናዬን መግለጽ እወዳለሁ” ሲል መምህር ኦኒዮ አስተያየቱን ይሰጣል፡፡

ታዲያ በአልጎቢያ ቀበሌ በተቋቋመው የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርታቸውን የጀመሩት ሉቶቢሪ ናጳዴሮ፣ እግር ቢዮቱላ፣ ዋንጮ ጌሊዮ እና ሎውጌ ማትቢ በወረዳቸው ሰላማጎ እየተካሄደ ያለ የስኳር ልማት እንቅስቃሴ ከአሁን በፊት ሊያስቡትና ሊመኙት የማይችሉት በነበረው የሥራ መስክ ከትምህርት በኋላ ለመሰማራት እንዲያልሙ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከትምህርት በኋላ ምን ዓይነት ሥራ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ መሆኑን ሲጠየቁ ሐኪም፣ ሾፌር፣ የመንግሥት ሠራተኛ መሆን እንደሚፈልጉ ይናገራሉ!! የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎችና በተለያዬ ሙያ የተሰማሩ የመንግሥት ሠራተኞች የመኖራቸውን ምስጢር ስኳር ልማቱ አስተዋውቋቸዋልና!! ታዲያ እኒህ እምቦቃቅላ ልጆች መንግሥት ልብስ እንዲያለብሳቸው ይጠይቃሉ- አንትሮፖሎጂስቶችና ጥናት እናካሂዳለን የሚሉ የውጭ አገር ምሁራን እንደሚመኙላቸው በወረሱት ኋላቀር አኗኗር መቀጠል አይፈልጉምና!!

በኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አማካይነት ወደ አስር የሚሆኑ የአገር ውስጥ እና የውጭ የግልና የመንግስት ተቋማት በተለያዬ ግን ከስኳር ልማቱ ሥራ ጋር ተያያዥ በሆነ ተግባር በሰላማጎ ወረዳ በአማካሪነትና በኮንትራክተርነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የፌዴራል እና የክልል እንዲሁም የውጭ አገር የግንባታ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ታዲያ ለአካባቢውና ለሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥረው በርካታ ወጣቶች በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተዋል፡፡  ከእነዚህ መካከል 202 የሚሆኑ በስኳር ኮርፖሬሽን እና በደቡብ ኦሞ ዞን መስተዳድር ድጋፍ በጂንካ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በተግባር የታገዘ አንድ ወር ከአንድ ሣምንት የፈጀ ሥልጠና ወስደው በማኀበር በመደራጀት በፕሮጀክቱ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ይገኙበታል፡፡

ወ/ት አለሚቱ ጋለሺ የአሪ ብሔረሰብ ተወላጅ ናት፡፡ በጂንካ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በቀለም ቀቢነት እና ፕላስተሪንግ ሙያ ሰልጥና ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የሚያስገነባቸውን መኖሪያ እና መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶችን በማኀበር ተደራጅታና ማኀበሩ ከፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ጋር ውል ፈጽሞ የቀለም ቅብና ፕላስተሪንግ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደምትገኝ ትናገራለች፡፡ አያይዛም ”ሥልጠናው ስለሙያው የማናውቀውን በርካታ ነገር እንድናውቅ አድርጓል፤ ቀደም ሲል ሥራ አልነበረኝም፤ አሁን ሥራ ኖሮኝ የራሴን ሕይወት መምራት በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ስትል ገልፃለች፡፡

የኛንጋቶም ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነው ወጣት አይጥለው መኮንን በጂንካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በግንባታ ሙያ ሰልጥኖ በኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በመስኖ አውታር ግንባታ ከሚሳተፈው የደቡብ ብ/ብ/ሕዝቦች ክልል ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር በተደራጀበት ”የተሐድሶ ግንባታ ማኀበር” አማካይነት የሥራ ውል በመዋዋል እየሰራ እንደሚገኝ ይገልፃል፡፡ ‹‹ ለአንድ ሜትር ኩብ የግንባታ ሥራ  ብር 19ዐ ሂሳብ ተስማምተንና ተዋውለን እየሰራን ነው ፤ በግል የሚሰሩ  ተቋራጮች  ለዚህ የሚከፍሉት  ከ6ዐ እስከ 1ዐዐ ብር ነው፣ ስለዚህ እዚህ የማኅበሩ አባላት  የተሻለ  ተጠቃሚ ነን››  የሚለው ወጣት አይጥለው ‹‹ ከሥልጠናው ለአንድ ጆንያ ሲሚንቶ ምን ያህል አሸዋና ጠጠር እንዲሁም የውኃ መጠን እንደሚያስፈልግ  በተግባር የተደገፈ  ሥልጠና በማግኘታችን ሥራችንን ያለምንም ችግር  እያከናወን   እንገኛለን ›› ይላል፡፡  ስኳር ኮርፖሬሽንም  ወደ ሥራ በተሰማሩበት  በዚህ ወቅት በመኝታ እና በምግብ አገልግሎት  እያደረገላቸው  ላለው ድጋፍ ምስጋናውን ይገልፃል፡፡

በሰለማጎ ወረዳ በመካሄድ ባለው የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀከት በሸንኮራ አገዳ ዘር ተከላ  በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ አጠቃላይ ቁጥራቸው 1ዐ1 ከሚሆኑ የእርሻው ዘርፍ ሠራተኞች መካከል 35 የሚሆኑት  የቦዲ ፣ መርሲ፣ ኛንጋቶም ፣ አሪ እና ሌሎች  ብሔረሰቦች ተወላጆች  መሆናቸውን አቶ አበበ አሰፋ በኘሮጀክቱ  የአገዳ ተክል ልማት  ዲቪዥን  ሥራ አስኪያጅ ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በሸንኮራ አገዳ  ተክል ጥበቃ ሥራ የተሰማራው አቶ ጋጁዋ ዋራኒመራ አንደኛው ነው፡፡  ‹‹ ቀደም ሲል ይህ አካባቢ ጫካ  ነበር፤ ስኳር ልማት ተጀምሮ እኔም በጥበቃ ሥራ በወር ብር 1ዐ67 እየተከፈለኝና   በተሽከርካሪ  እየተመላለስኩ እየሰራሁ  እገኛለሁ፤ እንደእኔ የቦዲ ብሔረሰብ ተወላጅ  የሆኑ አስር ወጣቶችም  በእኔ ዓይነት ሙያ በኘሮጀክቱ ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ ››  ሲል አቶ ጋጁዋ ይናገራል፡፡ 

የሙርሲ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነው ወጣት ስንታየሁ  ደርባ በበኩሉ የእርሱ ብሔረስብ ተወላጅ የሆኑ ሦስት ወጣቶች  በእርሱ ዓይነት ሥራ በኘሮጀክቱ  ተቀጥረው እየሰሩ እንደሚገኙ  ገልæ  ‹‹ የአካባቢው  ሰዎች በፊት እህል በእጃቸው ነበር  የሚፈጩት ፤ ውኃ ኦሞ ወንዝ ሄደው ነበር የሚቀዱት፤ ስኳር ልማቱ ለእኛ ለወጣቶች  የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ  ባሻገር  ቤተሰቦቻችን የወፍጮ፣  የውኃ፣ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ  እድርጓል፡፡ የስኳር ልማቱ ገና ባልደረሰባቸው አካባቢዎች  የሚኖሩ ዘመዶቻችን  መቼ ነው ልማቱ እኛጋ የሚደርሰው ሲሉ በጉጉት ይጠይቃሉ ››  በማለት የስኳር ልማቱ ከጅምሩ እየሰጠ ላለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይናገራል፡፡

‹‹ውኃ ለእኛም ሆነ ለከብቶቻችን እንዲህ እንደአሁኑ በቀላሉና  በአጠገባችን  ማግኘት አይታሰብም ነበር፣ እህል በእጃችን ፈጭተን  ነው እንመገብ የነበረው››  የሚሉት በዕድሜ ጠና ያሉት ወ/ሮ ጃይ ታኢሲ በመንደር የተሰባሰብነው  በፍላጎታችን ነው፤ ይህም ለእንደእኔ ዓይነት አሮጊት ኑሮን ቀላል የሚያደርግ ነው››  ሲሉ ይናገራሉ ፡፡  አያይዘውም ‹‹አርብቶአደር በመሆናችን  አርሰን እንድናመርት መሬትና ውኃ የምናገኝበት  መንገድ ተመቻችቶልናል›› ሲሉ ወደፊት ልጆቻቸው ከፊል አርሶ አደር እንደሚሆኑ  ተስፋ መጣላቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ስጦታው ጋርሾ ቡቃር የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳደርና የፍትሕ መምሪያ  ኃላፊ በበኩላቸው ሲናገሩ  ‹‹ በዞኑም ሆነ በክልል ደረጃ ቀደም ሲል ጀምሮ  እየተከናወነ የሚገኘው  አርብቶ አደሩን በመንደር የማሰባሰብ  ተግባር የምግብ ዋስትናችንን ከማረጋገጥ  አንፃር ከአገራችን ብሎም ከክልላችን  የገጠርና የግብርና ፖሊሲ የሚመነጭ ነው›› ይላሉ፡፡ ‹‹የመንደር ማሰባሰቡ ሥራ ስኳር ልማቱ በማይካሄድባቸው  እንደ  በናፀማይ ባሉ የዞኑ ወረዳዎችም  እየተካሄደ የሚገኝና አርብቶ አደሩን  የመሠረተ ልማት አውታሮችና  የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት  ተጠቃሚ ያደርጋል›› በማለትም አቶ ስጦታው የስኳር ልማት ኘሮጀክቱ በዞን አቅም ደረጃ ሊሟሉ  የማይችሉ ትላልቅ  የመሰረተ ልማት አውታሮች በዞኑ እንዲገነቡ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን ይናገራሉ፡፡   

ለኩራዝ ስኳር ልማት ኘሮጀክት የሸንኮራ አገዳ ልማት እንዲውል የኦሞ ወንዝ ውኃን  በኮፈርደም በመዝጋትና  የውኃ   መቀልበሻ  ዊር እና የዋና እና መለስተኛ ካናል ለመገንባት በኘሮጀክቱ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው  የፌዴራል  ውኃ  ሥራዎች  ኮንስትራክሽን  ድርጅት የኩራዝ ኦሞ ወንዝ መቀልበሻ  ኘሮጀክት ሥራ አስኪያጅ  አቶ ሞገስ  ክፍሌ  እንደሚገልጹት   የዋናውን ኮፈርደም  ግንባታ በማጠናቀቅ  ኘሮጀክቱ ለሚያካሂደው  የሸንኮራ  አገዳ ልማት የ24 ኪሎ ሜትር  የዋና ቦይ  ግንባታ ማጠናቀቅ  እንደተቻለ  ይገልፃሉ፡፡
ታዲያ ሁሉም ባለድርሻ  አካላት ማለትም የስኳር  ኮርፖሬሽን፣ የክልል ፣ የወረዳና የዞን  መስተዳድር አካላት፣ የፌዴራል ውኃ ሥራዎች  ኮንስትራክሽን  ድርጅት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለኩራዝ  ስኳር ልማት ኘሮጀክት የሚካሄድ የዋና እና  መለስተኛ  ካናል ግንባታ የአርብቶ አደሩን  ከብቶች እንቅስቃሴ  እንዳያስተጓጉል  ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ  ይገኛሉ፡፡  በዚህም የአርብቶ አደሩ  ከብቶች ቀደም ሲል ይተላለፉባቸው  በነበሩ ቦታዎች በተገነቡ ካናሎች  ላይ የከብቶች መተላለፊያ  ስትራክቸር (Cattle Grossing structure or bridge) እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እናም እውነታው በአንዳንድ ወገኖች እንደሚናፈሰው ሳይሆን ስኳር ኮርፖሬሽን  የኩራዝንም ሆነ ሌሎች የስኳር  ልማት ኘሮጀክቶችን ሥራን ሲያከናውን ለአርብቶ አደሩ  ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ትኩረት እየሰጠ ነው፡፡