ሊቀመንበሯ የማሊ ብሄራዊ ምክር ቤት ለሽግግር ወቅት ያወጣውን ፍኖተ ካርታ መቀበላቸውን ገለጹ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2005(ዋኢማ) - የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የማሊ ብሄራዊ ምክር ቤት ለሽግግር ወቅት ያወጣውን ፍኖተ ካርታ መቀበላቸውን ገለጹ።

ሊቀመንበሯ ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ-ዙማ  ባወጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ምክር ቤቱ በመንግሥት የቀረበለትን ፍኖተ ካርታ መቀበሉ ተገቢ ነው።

ፍኖተ ካርታው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሊ መንግሥት ሰሜናዊውን የአገሪቱን ክፍል ነፃ ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል ማለታቸውን ኮሚሽኑ ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል።

በአገሪቱ ነጻ፣ ፍትሃዊና ግልጽነት ያለበት ምርጫ በማካሄድም የሽግግሩን ወቅት ለመደምደም እንደሚረዳም ዶክተር ድላሚኒ-ዙማ አስረድተዋል።

የማሊ መንግሥትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመተባበር፣ በመግባባትና በተጠያቂነት መንፈስ በመሥራትም ፍኖተ ካርታውን ማስፈጸም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ፍኖተ ካርታውን ከሚጻረሩ ድርጊቶችም እንዲታቀቡም ሊቀመንበሯ አስገንዝበው፤ በዚህም የአገሪቱ ሕዝብ ሰላም፣ አንድነት፣ ዴሞክራሲና ብልጽግናን ለማምጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደሚሳካም እምነታቸውን መግለጻቸውን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።