የመስቀል አደባባይ-ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መንገድ በመጪው ግንቦት ወር ለትራፊክ ክፍት ይሆናል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2005(ዋኢማ) - ከመስቀል አደባባይ-ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመገንባት ላይ ያለው መንገድ በመጪው ግንቦት ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፍቃዱ ኃይሌ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉና የተጠናቀቁ የተለያዩ መንገዶችን ትናንት በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት፤ መንገዱ በርካታ ወጪና ገቢ እንግዶች የሚስተናገዱበት በመሆኑና በመጪው ግንቦት ወር በአዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል የሚከበር በመሆኑ ከወዲሁ ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ ነው።

ከመስቀል አደባባይ - ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እየተገነባ ያለው ይኸው መንገድ 4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡

በዚሁ መንገድ ግንባታ ምክንያት በአካባቢው ተቋርጠው የነበሩ የመብራት፣ የውሃና የስልክ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ እንደሚስተካከሉና በቅርቡም የመተላለፊያ ቦዮቹ እንደሚከፈቱ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ባስቀመጠው የአንድ ወር ፈጣን መፍትሄ አምጪ ዕቅድ መሰረት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው የዘገየና በህብረተሰቡ ቅሬታ የተነሳባቸውን መንገዶች በእቅዱ ውስጥ በማካተት በመስራቱ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡

በዚህም በዋነኛነት እየተፈጠረ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅና የትራንስፖርት ችግር ለማስወገድ እንዲቻል በግንባታ ላይ ያሉ ሁሉም መንገዶች ጠዋትና ማታ ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በማስተካከል አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ኢንጅነር ፍቃደ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ሕብረተሰቡ እየተፈጠረ ያለው የትራፊክ መጨናነቅና የትራንስፖርት ችግር እየተከናወነ በሚገኘው ከፍተኛ የመንገድ ግንባታ ስራ ምክንያት መሆኑን በመረዳት እስካሁን እያደረገ ያለውን ትብብር እንዲቀጥልበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአጠቃላይ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የመንገድ ግንባታ ስራ አበረታች መሆኑንና ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን እየተካሄደ ያለው የከተማ ቀላል ባቡር ግንባታ ስራም በትስስር እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሲሳይ ወርቅነህ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ ካለፉት ዓመታት የተሸጋገሩና በበጀት ዓመቱ የተጨመሩ 109 ያህል መንገዶችና ከመንገድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ፕሮጀክቶችን ይሰራል፡፡

ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት የመደበ ሲሆን፤ በከተማዋ የማጠናቀቂያ ስራ እየተካሄደላቸው ካሉት መንገዶች መካከልም በጣም በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ካሉት የአያት አደባባይ-ቦሌ አያት ኮንደሚኒየም አስፋልት መንገድ በተጨማሪ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር-አድዋ ድልድይ መንገዶችን ጠቅሰዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት በግንባታ ሂደት ላይ የቆዩት የቀለበት መንገድ 3ኛ አካል የሆነው የዊንጌት ቀለበት መንገድ አደባባይ-ጎጃም በር የ4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር መንገድና የዊንጌት ቀለበት መንገድ አደባባይ-አስኮ-ሳንሱሲ መንገዶችም በበጀት ዓመቱ ከተጠናቀቁት ውስጥ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በመጪዎቹ ጥርና የካቲት ወራት መጨረሻ በተለያዩ የወሰን ማስከበርና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ተጓተው የቆዩ መንገዶች እንደሚጠናቀቁ አቶ ሲሳይ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡