በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ አደረጉ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2005(ዋኢማ) - በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ 34 ሺ የአሜሪካን ዶላር የቦንድ ግዥ ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ በናይሮቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ትስስር ያላቸው ኬንያውንና ሶማሊያውያን ለታላቁ የህዳሴው ግድብ የቦንድ ግዥ አከናውነዋል።

ናይሮቢ በሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ በተከናወነው የቦንድ ሽያጭ ላይ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሸምሰዲን አህመድ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፈጣን እድገት በዚህ ከቀጠለ እኤአ በ2015 አገሪቱ የምዕተ አመቱን የልማት ግቦች ከሚያሳኩ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ትሆናለች።

የአገሪቱን የሃይል ፍላጎት ለማሟላትም በርካታ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ላይ ከ500 በላይ እንግዶች መሳተፋቸውንም ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።

ባለፈው አመት በኬንያ በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መገኘቱን ሚኒስቴር አስታውሷል።