ሰላሳ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የምርጫ ካርድ ወሰዱ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2005(ዋኢማ) - ልዩ የመራጮች ምዝገባ ጥር 24 እና 25 እንደሚካሄድና  እስከ አሁንም 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ካርድ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ ።

በሚያዝያ 6 እና 13/2005 የሚካሄደው የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ የአካባቢ ምርጫ ለመሳተፍ ከታህሳስ 22 እስከ ጥር 21/2005 ዓ.ም በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ በአጠቃላይ 29 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ ተመዝግቧል።

የተመዘገቡት መራጮች ህዝብ ብዛት በክልል ደረጃ ሲታይ ትግራይ 2 ሚሊየን 046 ሺ 250፣ አፋር 959 ሺ 884፣ አማራ ክልል 7 ሚሊየን 083 ሺ 405፣ ኦሮሚያ 10 ሚሊየን 458 ሺ 750፣ ደቡብ ክልል 5 ሚሊየን 134 ሺ 287፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 247 ሺ 205፣ ጋምቤላ 145 ሺ 361፣ ሐረር 62 ሺ 383፣ ድርዳዋ 127 ሺ 127፣ አዲስ አበባ 1 ሚሊየን 030 ሺ 744ና ሶማሌ ክልል 2 ሚሊየን 610 ሺ 122 መራጮች በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመዝግበዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ልዩ የመራጮች ምዝገባም ጥር 24 እና 25 እንደሚካሄድ የገለጸው ምርጫ ቦርድ እስከ አሁን ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች እንዲወስዱ ጥሪ መቅረቡን ኢሬቴድ ዘገባ ያስረዳል።