ታሪካዊ ስህትት ከመስራት ተጠበቁ

  • PDF

ኢብሳ ነመራ (ጥር 23/2005)
ከጥቅምት ወር ወዲህ ዘንድሮ የሚካሄደውን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር እንዲሁም የአካባቢ ም/ቤቶች አባላት ምርጫ ጋር የታይዞ የጋዜጦች የፊት ገፅ ላይ የተለመደው “33ቱ ፓርቲዎች” የሚል የዜና ርዕስ ባለፈው ሳምንት ወደ ሃያ ስምንት (28) ተቀይሯል፡፡ በሌላ በኩል ምርጫው ላይ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ፓርቲዎች 29 መድረሳቸው ተዘግቧል፡፡ ከፓርቲዎቹ መሃከል ይበጀኛል የሚለውን የሚመርጠውም  ሕዝብ እንዲሁ እየተመዘገበ ነው፡፡
የዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረት ቀደም ሲል “33ቱ” ይባሉ የነበሩት አሁን ቁጥራቸው ወደ 28 ዝቅ ያለው ፓርቲዎች የያዙት አቋም ላይ ነው፡፡ እንደምናስታውሰው ፓርቲዎቹ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመወያየት የጠራው ስብሰባ ላይ፣ ከምርጫው በፊት ምላሽ ማግኘት አለባቸው ያሉዋቸውን 18 ጥያቄዎች አንስትው ነበር ምርጫው ላይ ያለመሳተፍ አዝማሚያ ማሳየት የጀመሩት፡፡ ይህን ተከትሎ የምርጫ ቦርድ ላቀረቡዋቸው ጥያቄዎች በሙሉ አንድ በአንድ ምላሽ ሰጠ፡፡ ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎችና ቦርዱ የሰጠው ምላሽ በተደጋጋሚ የተገለጹ ቢሆንም፣ ለማስታወስ ያህል ጎላ ጎላ ያሉትን እንመልከት
ዋና ዋናዎቹ ጥያቄዎች የምርጫ አስፈዓሚዎችን፣ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን፣ የፕሬስ ነጻነትን  የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎችን በተመለከተ ፓርቲዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ “የገዥው ፓርቲ አባልና ደጋፊ በመሆናቸው በምርጫ ሂደት ላይ ወገንተኝነት ታይቷል” የሚል ነበር፡፡  ምርጫ ቦርድ ለዚህ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ፣ “ሰላሳ ሶስቱ ፓርቲዎች ይህን ቅሬታ ሲያቀርቡ የተባለው ችግር በየትኛው ክልል በተካሄደ ምርጫ፣ የትኛው ምርጫ አስፈፃሚ ግለሰብ ወገንተኝነት እንደታየበት፣ ምን አይነት የወገንተኝነት ድርጊት እንደተፈፀመ በማስረጃ ተደግፎ አልቀረበም”  የሚል ነበር፡፡

እርግጥ ነው በምርጫ ላይ ምንም አይነት ችግር አይፈጠርም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በመቶ ዓመታት የሚቆጠር የምርጫ ታሪክ ባላቸውም አገራትም ችግር ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫን የሚያክል የህዝብ የስልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት የሚረጋገጥበት ትልቅ ጉዳይ ላይ እንደ ችግር የሚነሱ ጉዳዮች ተገቢውን መፍትሄ ማግኘት ይችሉ ዘንድ የተሟላ በማስረጃ የተደገፉ ተጨባጭ መሆን ይግባቸዋ ፡፡
በቂ ማስረጃ ሳይቀርብ የሚነሳ ቅሬታ በዘፈቀደ ከተነገረ አሉባልታ የተለየ ዋጋ አይኖረውም፡፡ በመሆኑም አንድነት/ መድረክ መራሾቹ 28 ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላቀረቡት ጥያቄ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ አይቻልም፡፡ ቦርዱም ይህንኑ ነበር ያስታወቀው፡፡ አንድነት/ መድረክ መራሾቹ ፓርቲዎች “የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች የወከሏቸው ታዛቢዎች በምርጫ ወቅት ታስረዋል፣ ተባረዋል” የሚል ቅሬታም አቅርበዋል፡፡
ይህ ቅሬታ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት የ1997 እና የ2002 ምርጫዎችም ላይ መቅረቡን ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ ምርጫ ቦርድም ለቅሬታው ምላሽ ሲሰጥ “በ2002 ምርጫ ወቅት የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡” በማለት አስታውሷል፡፡ ቦርዱ በዚህ ዙሪያ ላቀረበው ቅሬታ በሰጠው ምላሽ ቅሬታው በቀረበበት የ2002 ምርጫ ወቅት፣ አቤቱታ በቀረበባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ማጣራቱንና የተባለው ችግር ያለመፈጠሩን አረጋግጦ አግባብ አለመሆኑን ማሳወቁንም አስታውሷል፡፡
እንግዲህ ከ2002 ወዲህ ሌላ ምርጫ ስላልተካሄደ ፓርቲዎቹ ማጣራት ተደርጎበት አለማጋጠሙ የተረጋገጠን ጉዳይ ነው በድጋሚ እንደ አዲስ ያቀረቡት፡፡ ይህ ደግሞ ምርጫው ላይ ላለመሳተፍ ሰበብ ለመፈለግ የተደረገ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከዚሁ ከታዛቢዎች ጋር በተያያዘ ሕዝብ የመረጣቸው ታዛቢዎች ለተለያዩ ተጽአኖዎች መደረጋቸውን ፓርቲዎቹ እንደ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ለዚህ ቅሬታ በሰጠው ምላሽ፣ ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄደው የ2002 አገራዊ ምርጫ ላይ ሕዝብ የመረጣቸው የምርጫ ታዛቢዎች ላይ የዚህ አይነት ችግር ስለመኖሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከሕብረተሰቡ የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን አስታውሷል፡፡
በወቅቱ አቤቱታ ያልቀረበበት ይህ ችግር አሁን በመጪው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እንደችግር ሲቀርብ፣ ችግሩ የት እንደተፈፀመና ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ አለመቅረቡንም ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች አሁን “ተፅእኖዎች ተፈፅመውባቸዋል” በሚል ቅሬታ ያቀረቡባቸው የ2002 ምርጫ የሕዝብ ታዛቢዎችን ሕዝቡ በመረጠበት ወቅት “አመራረጣቸው ትክክል አይደለም፣ ገለልተኛም አይደሉም” የሚል ቅሬታ አቅርበውባቸው እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ያኔ ገለልተኛ አይደሉም ሲባሉ የነበሩት የህዝብ ታዛቢዎች፣ አሁን ነገሩ ካለፈ በኋላ እንደተዘነጋ በማሰብ “ተፅእኖዎች ተፈፅመውባቸዋል” መባሉ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
ተቃዋሚዎቹ መገናኛ ብዙሃንን የሚመለከቱ ቅሬታዎችም አቅርበዋል፡፡ በዚህ ቅሬታ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ቀዳሚው “ፍትሃዊ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም የለም” የሚል ሲሆን ሁለተኛው “የግል ፕሬሶችና የፓርቲ ልሳኖች ተዘግተዋል፣ እንዳይታተሙ ተገድበዋል” የሚል ነው፡፡
የመገናኛ ብዙሃንን ፍትሃዊ አጠቃቀም፣ በተለይ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ቅሬታ ብሄራዊ ምርጫ ቦረድ በሰጠው ምላሽ፣ የምርጫ አዋጅ 523/99 አንቀጽ 59ን ጠቅሷል፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት “የፖለቲካ ድርጅቶች የመገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት እንዴት ይጠቀማሉ” የሚለው በግልፅ መቀመጡንና በዚሁ መሰረት የአጠቃቀም ደንብ መውጣቱንም አስታውቋል ፡፡ ደንቡ ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በረቂቁ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት መደረጉንና፣ በዚሁ መሰረት የአየር ሰዓት ድልድል መደረጉን፣ በድልድሉም ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መወያየታቸውንም አስታውሷል፡፡
በ2002 ዓ/ም እና ከዚያ ቀደም በተደረጉት ምርጫዎች ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎችም አቋማቸውንና ፖሊሲያቸውን በመንግስት ሬድዮና ቴሌቭዥን እንዲሁም ጋዜጦች ሲያስተዋውቁ እንደነበር ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩት አብዛኞቹን ፓርቲዎች ያወቅናቸው፣ በዚህ ራሳቸውንና አቋማቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ በተሰጣቸው የሬድዮና የቴሌቪዥን ስርጭት የአየር ሰኣት ነበር፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገለፀው፣ በምርጫ ሂደት ወቅት ወጥተው የነበሩ መግለጫዎችና ዘገባዎች እንዳመለከቱት በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን የአየር ሰዓት በሙሉ አልተጠቀሙም ነበር ፡፡ በተለይ የተሰጣቸው የጋዜጣ አምድ አጠቃቀምን በተመለከተ የተመደበላቸውን የጋዜጣ ስፍራ ጭራሽ ያልተጠቀሙ ፓረቲዎችም ነበሩ፡፡ ይህ የሆነው በውጭ ተፅእኖ ሳይሆን በራሳቸው በፓርቲዎቹ ድክመት ነበር፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሰላሳ ሶስቱ ፓርቲዎች “ፈትሃዊ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም አልነበረም” በሚል ያነሱት ቅሬታ መሰረተ ቢስ ነው፡፡ የግል ፕሬሶችንና የፓርቲ ልሳኖችን በተመለከተ ወደቀረበው ስንመለስ፣ ጉዳዩ ከምርጫ ጋር ያለተገናኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቢሆንም ምርጫና ፕሬስ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ሁኔታው ምን እንደሚመስል እንመልከት፡፡
እርግጥ ነው ከስርጭት ውጭ የሆኑ ጋዜጦች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይ   የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነፃነት የተሰኘ ልሳንን እንዲሁም ነፃ ፕሬስ ነኝ የሚለውን ፍትህ ጋዜጣን የሚመለከት ነው፡፡ የአንድነት ልሳን የሆነው ፍኖተ ነፃነትም ሆነ የግል ጋዜጣ ነኝ ባዩ ፍትህ ለበርካታ ጊዜያት እየታተሙ ሲሰራጩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት በኢፌዴሪ ሕገመንግስት ተረጋግጦ፣ ለዚሁ ነፃነት ተግባራዊነት የፕሬስ አዋጅ በመውጣቱ ነው፡፡
ሀሳብን የመግለፅ - የፕሬስ ነፃነት በሕገ መንግስት የተረጋገጠ ቢሆንም የህዝብን መብትና ነጻነት፣ ሰላም፣ … ለመጠበቅ ዓላማ የህግ ገደብ ተበጅቶለታል፡፡ የፕሬስ ነፃነት፣ በፕሬስ አማካኝነት በአገር ደሕንነት፣ በሕዝብና በግለሰቦች ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ድርጊት መፈፀምን አያጠቃልልም፡፡
በዚሁ መሰረት የተጠቀሰውን ጋዜጣና የፓርቲ ልሳን እንዳይታተሙ ያደረጋቸው በ1997 ዓ/ም ተሻሽሎ የወጣው የወንጀል ሕግ ነው፡፡ በወንጀል ሕጉ ምዕራፍ አራት ላይ “በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት በሚደረጉ ወንጀሎች ተካፋይ መሆን” በሚለው ርዕስ በአንቀፅ 43 ስር በህትመት ውጤቶች አማካኝነት  ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት በተመለከተ ተደንግጓል፡፡
በዚህ አንቀጽ ላይ የሕትመት ውጤቶች ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ከሕትመት ውጤቶች አዘጋጆችና ከአሳታሚ ድርጅቶች ቀጥሎ በተዋረድ አታሚዎች(ማተሚያ ቤቶች)፣ አታሚዎቹ ባልታወቁበት ሁኔታ ደግሞ የህትመት ውጤቱ አከፋፋዮች  እንደሚጠየቁ ይገልፃል፡፡
በዚህ መሰረት ማተሚያ ቤቶች አትመው በሚያወጡት የህትመት ውጤት ሳቢያ ከሚደርስባቸው የህግ ተጠያቂነት  ራሳቸውን የመከላከል መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ የሚገኙ የተወሰኑ  አታሚዎች (ማተሚያ ቤቶች)፣  አሳታሚዎች በወንጀል የሚያስጠይቅ ይዘት ያለው የህትመት ውጤት ለሕትመት እንዳያመጡ፣  የሚያመጡዋቸው የህትመት ውጤቶች በሕግ ያስጠይቃሉ ብለው ሲያምኑ ለማተም እንዳይገደዱ ውል እንደገቡ ጠይቀው ከአታሚዎች ጋር የስራውል ገብተዋል፡፡ በዚህ ውል መሰረት በሕግ የሚያስጠይቅ ይዘት ያለው የህትመት ውጤት ይዘው የመጡ ጋዜጦችንና የፓርቲ ልሳኖችን እንደማያትሙ አሳወቁ፡፡ አንድነት/መድረክ መራሾቹ ፓርቲዎች በዚህ ዙሪያ ያቀረቡት ቅሬታ ከዚህ የህግ አግባብ አኳያ የሚታይ ነው፡፡
በዚህ አኳኋን ለጥያቄዎቹ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ፓርቲዎቹ ወደ ምርጫ ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ አምስቱ ብቻ ማለትም፤ የኢትዮጵያ የፍትህና የዴሞክራሲ ኃየሎች ግንባር፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ሕብረት፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ የባሕር ወርቅ ምስመስ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና ዱቤና ደጀን ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቀርበው የምርጫ ምልክታቸውን ሲወስዱ የተቀሩት በአሻፈረኝ ባይነታቸው ፀኑ፡፡
የተቀሩት 28ቱ አንድንት/መድረክ መራሾቹ ፓርቲዎች ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ የተደበላለቀ ነገር ነግረውናል፡፡ የፓርቲዎቹ አስተባባሪ ኮሚቴ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ “ከፓርቲዎቹ የቀረቡት ጥያቄዎች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር፣ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የሚያስችሉ ግልፅና የማያሻማ ቢሆኑም ቦርዱ ‘ጆሮ ዳባ ልበስ’ በማለት ለጥያቄዎች መፍትሄ ሳይሰጥ ወደምርጫ አፈፃፀም ገብቷል” ብለዋል፡፡
እርግጥ ነው ቀደም ሲል የተመለከትናቸው ፓርቲዎቹ እንደ ችግር ያነሱዋቸው ጉዳዮች ምርጫው ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ያግዛሉ፡፡ምርጫ ቦርድም ይህን ታሳቢ በማድረግ አንድም ጥያቄ ሳያስቀር ምላሽ ሰጥቷል፡፡ምላሽ ከተሰጠባቸው ቅሬታዎች መሃከል የተወሰኑት ጉዳዮች በቀጥታ ከምርጫው ጋር የማይገናኙ ሰላም፣ ዴሞክራሲንና ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር የተወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎችን የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ ከዚህ ቀደም ተነስተው ምላሽ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከምርጫ ጋር ተያይዞ በቀጣየነት ችግሮቹ ቢያጋጥሙ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ሕግና የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል፡፡
ችግሮቹን ለመከላከል ከተዘረጉት የአሰራር ስርአቶችና ሕጎች መሃከል ከ2002 ምርጫ ቀደም ብሎ ከአንድነት/መድረክ በስተቀር የተቀሩት ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለወራት መክረውበት ያፀደቁት፣ በኋላም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሆኖ የወጣው የምርጫ ስነ ምግባር ደንብና በዚሁ ደንብ መሰረት የተቋቋመው የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ስርአት ከምርጫ ጋር የተያያዙ ችግሮች ላይ ፓርቲዎች አስቀድመው እንዲወያዩ፣ ከተፈጠሩም በኋላ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ያስችላል፡፡
አሁን ችግሮቹ ገና ለገና በመጪው የአዲስ አበባ፣ የድሬደዋና የአካባቢ ምክር ቤቶች ምርጫ ላይ ያጋጥማሉ በሚል ምናባዊ ስሌት 27 ፓርቲዎችን አስባሰቦ የውዝግብ አጀንዳ ለመፍጠር የሚፍጨረጨረው አንድነት/መድረክ፣ ከምርጫ ጋር ተያይዘው ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት የተዘጋጀውን ሕግና የአሰራር ስርአት አሻፈረኝ ማለቱ ይታወቃል፡፡  ከዚህ አኳያ አንድነት/መድረክ  በመጪው ምርጫ ላይ የያዘው አቋም ዋና ትኩረቱ ምርጫ ላይ ተሳትፎ የህዝብ ውክልና ማግኘት ሳይሆን፣ ምርጫን ለስውር አላማ ማሳኪያነት ለመጠቀም የውዝግብና ጭቅጭቅ መንስኤ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ያመለክታል ፡፡
እንግዲህ አንድነት/መድረክ መራሹ የፓርቲዎች ቡድን ሰብሳቢ የሆኑት የአንድነቱ ከፍተኛ አመራር አቶ አስራት ጣሴ ከአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ወደ ምርጫው እንደማይገቡ አሳውቀዋል፡፡ እርግጥ አቶ አስራት ይህን ከማለታቸውም በፊት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ላይ መወዳደር የሚፈልጉ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክታቸውን እንዲያሳውቁ በስቀመጠው ከአንድ ወር በላይ የግዜ ገደብ ውስጥ ቀርበው የምርጫ ምልክታቸውን ባለማሳወቃቸው በራሳቸው ውሳኔ ከምርጫው ውጪ ሆነዋል፡፡ ቦርዱም ይህን አሳውቋል፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ውጭ መሆናቸው ሳይሆን ከምርጫ ውጭ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምክንያት ምንድ ነው? የሚለው ነው፡፡
ይህ ከምርጫ ውጭ የመሆን ፍላጎት አንድነት/መድረክ ያሰባሰባቸው የሁሉም ፓርቲዎች ከወስጥ የመነጨ ፍላጎት ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ምርጫው ላይ ያለመሳተፍ ጉዳይ በዋናነት የአንድነት/ የመድረክ አጀንዳ ነው ፡፡ ለዚህ አስረጂ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመድረክ አባል መሆኑን የሚናገረው፣ ሆኖም ከመድረክ ውጭ አቋም በመያዝና ጮሆ በመናገር የሚታወቀው የአንድነት አመራሮች በቅርቡ ይፋ ያደረጓቸውን አቋሞች በአስረጅነት እንመልከት፡፡ እነዚህ የአንድነት አመራሮች ሊቀመንበሩ ዶ/ር ነጋሦና የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙላቱ ጣሴ ናቸው፡፡ ሁለቱ የአንድነት አመራሮች በሕዳር ወር ላይ እንዳቀረቡት በተነገረላቸው ጥናት የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ችግሮች ያሉዋቸውን ዘርዝረው፣ ገዥው ፓርቲ “የሕዝብ ድጋፍ የለውም” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡
ሁለቱ የአንድነት አመራሮች “ገዢው ፓርቲ የሕዝብ ድጋፍ የለውም” በሚል ያቀረቡትን ድምዳሜ የተመለከተ ማንኛውም ሰው አንድ የሚገምተውና የሚጠብቀው ነገር አለ፡፡ ይህም ፓርቲው በምርጫ ላይ ተሳትፎ በኢህአዴግ ላይ አኩርፈዋል ያላቸውን ዜጎች ድምፅ ለማግኘት ይሰራል የሚል ነው፡፡ የአንድነት አመራሮች ግን ከዚህ የተለየ አቋም መያዛቸምን ነው የገለፁት፡፡
ዶ/ር ነጋሦ ኢህአዴግን ሕዝቡ እንደማይደግፈው በእርግጠኝነት ተናግረው ሲያበቁ፣ ምርጫ ላይ ተሳትፈን በሕዝብ ውክልና ወደ ስልጣን እንመጣለን ከማለት ይልቅ “ገዢውን ፓርቲ ለለውጥ የሚያስገድደው ሰፊ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ገዢውን ፓርቲ ለማስወገድ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የሚፈጠርበትን መንገዶች መቀየስና በእርሱ ላይ መስራት የወደፊት የትግል አቅጣጫችን ነው” ነበር ያሉት፡፡ በተመሳሳይ የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሙላቱ ጣሰው “ሕዝቡ ለውጥን ከተቃዋሚዎች መጠበቅ አይኖርበትም፣ ሕዝቡ በራሱ ትግል ነፃ መውጣት አለበት፣ ፓርቲዎች የሕብረተሰቡን ትግል ይመራሉ ” ብለው የሕዝባዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊነትንና የፓርቲያቸውን ሚና ነግረውናል፡፡
ዘንድሮ ሚያዚያ ወር ላይ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫ በሂደት ላይ እያለ፣ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በይፋ የገለፁዋቸው እነዚህ አቋሞች፣ ፓርቲው ምርጫ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ውሳኔ ላይ መድረሱንም ያሳያል፡፡ እናም አንድነት/መድረክ መራሹ ቡድን ምርጫው ላይ ላለመሳተፍ የሚያቀርቡዋቸው ጉዳዮች፣ ሕዝብንና ሌሎች ታዛቢዎችን  ሊያታልል የሚችል ሰበብ ለማቀረብ የተደረገ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድነት/መድረክ ይህን በምርጫ ከሚገኝ የሕዝብ የስልጣን ውክልና ውጭ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ በሌላ አነጋገር በኃይል  ለስልጣን ሊያበቃ ይችላል ያለውን  አካሄድ ለምን መረጠ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በተለይ ሕዝቡ ገዢውን ፓርቲ እንደማይደግፍ እርግጠኛ ነኝ እያለ ምርጫን መሸሹ ብዙዎችን ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡
ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ቀዳሚው ግን በተለይ አንድነት ያያዛቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ያረጁና ያፈጁ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀባይነት ሊኖራቸው የማይችሉ በመሆኑም በምንም አኳኋን ለስልጣን የሚያበቃ የሕዝብ ድምፅ ሊያስገኙ የማይችሉ ከመሆናቸው የነመጨ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ነች፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው እውቅና ተነፍጎት፣ በማንነታቸው አንገታቸውን እንዲሰብሩ የሚያደርግ በረጅም ዘመን ጭቆና ውስጥ አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለዋ አገር ከተመሰረተች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ የጭቆና ቀንበር ከላያቸው ላይ የወረደው በ1983 ዓ/ም የመጨረሻው ጨቋኝ የሆነው የወታደራዊው ቡድን አምባገነናዊ ስርዓት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ባካሄዱት መራራ ትግል ተገርስሶ መውደቁን ተከትሎ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሉአላዊት ኢትዮጵያ ባለቤቶች ሆነው በእኩልነትና በመከባበር ላይ ተመስረተው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ መኖር የሚያስችላቸውን የቃል ኪዳን ሰነድ - የኢፌዴሪ ሕገመንግስት ቀርፀዋል፡፡ በዚህ የቃል ኪዳን ሰነድ መሰረት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ከሌሎች ጋር በእኩልነት መኖር የሚያስችል ፌደራላዊ ስርዓት መስርተዋል፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እስከመገንጠል የዘለቀ መብትና ነፃነትም አላቸው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት አይነ ግብ ነን ከሚሉት ፓርቲዎች መሃከል ይህን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሕገ መንግስቱ የተጎናፀፉትን የብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብት መከበሩ ዋነኛ ማረጋገጫ የሆነውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመቃወም ቀዳሚው አንድነት ነው፡፡
በመድረክ ውስጥ ከብሄራዊ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት መመስረቱን ከተናገረ በኋላ እንኳን በዚህ አቋሙ ላይ ለውጥ አላሳየም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ሳይቀይር በመድረክ ስር ከብሄራዊ ፓርቲዎች ጋር ተጣምሬያለሁ ማለቱ ብዙዎችን የሚያስገርም እንቆቅልሽ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥምረቱ የሌለ ያህል ከሌሎቹ ተጣማጆቹ ተለይቶ ለብቻው አቋም እንዲይዝ የሚያስገድደው ከሌሎቹ ጋር ሊዋሃድ የማይችል ውሃና ዘይት መሆኑ ነው የሚል አስያየት የሚሰጡም አሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር በኢፌዴሪ ሕገመንግስት ላይ ከተደነገገው በተቃራኒ በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አሰፋፈር ሳይሆን፣ በመልክአ ምድር - በወንዝ፣ ተራራ ሸለቆ መከለል አለበት የሚል ፅኑ አቋም ነው ያለው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን በመበታተንና የተለያዩትን በመቀላቀል በኢፌዴሪ ሕገመንግስት የተጎናፀፉትን ራስን በራስ እያስተዳደሩ በእኩልነትና በመከባበር አንድ የጋራ አገር መስርተው የመኖራቸውን ጉዳይ የማይቻል ያደርዋል፡፡
በመሆኑም አንድነት በተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚገለፁትን ኢትዮጵያውያን ድጋፍና ለስልጣን የሚያበቃ ድምፅ ማግኘት እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ ስልጣን ላይ ወጥቶ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በመራራ ትግል አሸቀንጥረው የጣሉትን ስርዓት ዳግም የመመለስ አቋሙን ተግባራዊ ለማድረግ ከምርጫ የተለየ አካሄድ መከተል አለበት፡፡ ይህም አነሰም በዛም በተለይ በከተማዎች አካባቢ የሚገኙ ከባለፉት ዘውዳዊና ወታደራዊ ስርአቶች አመለካከት ውርዴነት ያልጸዱ ደጋፊዎቹን አስተባብሮ በኃይል የመንግስት ስልጣን ለመያዝ መንቀሳቀስ ነው፡፡
በውጭ አገራት በተለይ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የሚኖሩ - ገሚሶቹ የዋህ የመኖሪያ ፍቃድ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ፣ ገሚሶቹ  የባለፉት ስርዓቶች ታሪክ ሆኖ መቅረት የከነከናቸው፣ የተቀሩት ደግሞ በተለይ በአፋኙ የደርግ ስርአት በፈፀሙት ወንጀል በሕግ ስለሚፈለጉና እንፈለጋለን ብለው ስለሚጠራጠሩ ወደ አገር ቤት መመለስ የማይችሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከጀርባ ሆነው የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አንድነት በአቋሙ እንዲፀና ምክንያት መሆናቸውንም የሚያመለክቱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የአንድነት/መድረክ አመራሮች ከሁለት ወራት በፊት በመጪው ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ የሚያመለክት አዝማሚያ ከማሳየታቸው በፊት ወደ አሜሪካ ተጉዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በምርጫው ላይ ድምፅ እንደማይሰጡ ይታወቃል፡፡ ታዲያ የአንድነት/መድረክ አመራሮች ወደ አሜሪካ የተጓዙት ለስልጣን የሚያበቃ መራጭ ፍለጋ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ተልዕኮ አስታጥቆ ማስፈፀሚያ ገንዘብ የሚሸጉጥላቸው ፍለጋ ነው፡፡ በዚህ ጉዳው ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች እዛው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጰያዊያን ምስክርነታቸውን ሰጥተውበታል፡፡
ከዚህ ቀደም ካለን ልምድ በውጭ አገር የሚኖሩ በመሰረተ ቢስ ጥላቻ የሚነዱ ስሜታዊ ተቃዋሚ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጰያዊያን “ምን እናድርግ?” ብሎ ለሚሄድላቸው ፓረቲ “ምርጫ ላይ ተሳተፍ” የመል አደራ እንደማይሰጡ  ይታወቃል፡፡ እናም አንድነት በቅርቡ የተቀበለ ተልዕኮ ሊሆን የሚችለው፣ ከጠቅላላ የአገሪቱ ሕዝብ አብላጫ ባይሆንም፣ ምርጫን አስታካችሁ ደጋፊያችሁን በማስተባበር “በሕዝባዊ እንቅስቃሴ” የመንግስት ለውጥ አምጡ የሚል ነው፡፡የአንድነት አመራሮች ከአሜሪካ መልስ ባካሄዱት ስብሰባ ይህንኑ ነው በይፋ ተናግረዋል፡፡
ፅንፈኛ ተቃዋሚውን ዳያስፖራ በተመለከተ የመድረክ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ከአንድ ወር በፊት ሰንደቅ ከተባለው ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የነገሩንንም ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፕ/ር በየነ “ዲያስፖራው አንድ ስብሰባ ላይ መጥቶ 50 ዶላር ከፍሎ በዛች 50 ዶላር መንግስት ለምን አትገለብጡም ይላል። ያለው ኢህአዴግ ደግሞ የማይፈለጥ አለት ነው።” ነበር ያሉት፡፡
ያም ሆነ ይህ አንድነት/መድረክ ይህን ዓላማውን ማሳካት እንደማይችል ያውቀዋል፡፡ስለዚህ አጋር ይፈልጋል፡፡ በቅርብ ያገኛቸው አጋሮቹ ከምርጫ ጋር አያይዞ በቅቤ ምላሱ ያልሆነ ነገር ቀባጥሮ ሊሸውዳቸው የሚችላቸውን ተቃዋሚ ፓረቲዎች ነው፡፡ በዚህ አካሄድ “በምርጫው ላይ ተሳትፋችሁ ላታሸንፉ ኢሕአዴግን ከምታሩዋሩጡ፣ ከምርጫ ውጭ ሆናችሁ እኔን አሩዋሩጡ” ብሎ ጀንጅኖ እስካሁን ባለው ሁኔታ 27 ያህል ፓርቲዎችን ለአሯሯጭነት አዘጋጅቷል፡፡
እነዚህ አንድነት/መድረክ አደናግሮ የመለመላቸው አሯሯጮቹ ከሩጫው አንዳችም ጥቅም አያገኙም፡፡ እርግጥ አንድነት/መድረክ ዶላር ሊያገኝ ይችላል፡፡ ፓርቲዎቹ የተጠቋቋሙለትን አላማ የማሳካት እድል ያገኙ የነበረው በምርጫው ላይ ቢሳተፉ ነበር፡፡ ቢያንስ ከሕዝብ ጋር የመተዋወቅ እድል ያገኙ ነበር፡፡ ለአንድነት/መድረክ ብለው ይህን እድል መስዋዕት አድርገዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ግን አልረፈደባቸውም፡፡ በአንድነት/መድረክ ስር ሆነው ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ለመስራት መመልመላቸውን ተገንዝበው፣ ከዚህ በመራቅ ቢያንስ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ መስራት የሚችሉበት እድል አሁንም ክፍት ነው፡፡