ሸአቢያ ጓዳ የዘለቀ የጥፋት መረብ

  • PDF

አዲስ ቶልቻ (ጥር 23/2005)
ከጥቂት ወራት ወዲህ የሙስሊሞች የአርብ የፀሎት ስነ ስርዓት ላይ የሚታደሙ ሙስሊሞች ውስጥ ተቀላቅለው ከፀሎት ስርዓቱ ማብቃት በኋላ፣ እጃቸውን እያወራጩ፣ ሲላቸውም መፈክር እያሳዩና አያሰሙ ተቃውሞ ላይ ነን የሚሉ ጥቂት ግለሰቦችን ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ የሚሆነው አዲስ አበባ በተለይ በአንዋር መስጊድ ነው።የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎችና መስጊዶች ፍፁም ሰላማዊ ናቸው፡፡

ይህን ትዕይንት ባፉት ሁለት አስርተ አመታት የሃይማኖት ነፃነታቸው አንዳችም ሳይሸረፍ እንደተከበረላቸው የሚያውቁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ኢትዮጰያዊያን በትዝብት ነው የሚመለከቱት።

እነዚህ ሙስለም ኢተዮጵያዊያን በፀሎት ስነስርዓቱ ላይ ቡድኑ ውስጥ መቀላቀል አይፈልጉም። አንዳንድ ወጣት ሙስሊሞች ወደ አርብ የፀሎት ስርዓት ለመሄድ የሚሰግዱበት ቦታ ሲመርጡ “ኤሮቢክሶቹ ጋር  ነው ወይንስ ከዚያ ውጭ” እየተባባሉ በአዋኪው ቡድን ድርጊት ሲቀልዱ መስማት የተለመደ ነው። እጃቸውን እያወራጩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (erobic exercise) መሰል ትዕይንት የሚያሳዩት ጋር ነው ወይንስ ከዚያ ውጭ ማለታቸው ነው።

ይህ የጁሙዓ ፀሎትን ተቀላቅሎ የሚዘባርቀው ቡድን ባለፉት ጥቂት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ የቆየውና በኋላም ከአንድ አመት በፊት በአወሊያ መስጊድ ብቅ ያለው የአክራሪነት እንቅስቃሴ የፈጠረው ቡድን ነው።

ይህ የአክራሪ ቡድን ከአንድ አመት በፊት እንቅስቃሴውን ሲጀምር በቀዳሚነት ያነሳው ጥያቄ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የስራ ግዜውን ስለጨረሰ በምርጫ ይተካ የሚል ነበር። በስራ ላይ የነበረው የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም ይህን ጥያቄ ተቀብሎ ምርጫ እንደሚካሄድ አሳውቆ ነበር።

የአወሊያው አክራሪ ቡድን ጉዳዩ ያለወጉ እንዲጋነን ይህንኑ ጉዳይ ለመንግስትም አቅርቦት እንደነበር እናስታውሳለን። መንግስት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል በሰጠው ምላሽ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ስለሆነ ጣልቃ እንደማይገባ ገልፆ፣ ሆኖም ጥያቄው ተገቢ ስለሆነ ምርጫው እንዲካሄድ የሎጆስቲክስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቆ ነበር።

የአክራሪው ቡድን ዋነኛ አጀንዳ ህዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖት መሪዎቹን እንዲመርጥ ማድረግ ሳይሆን፣ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ለብቻው ተቆጣጥሮ ስውር የፖለቲካ አጀንዳውን ማስፈፀም ስለነበር፣ ምርጫው መካሄዱ ቁርጥ መሆኑን ሲያውቅ በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ በሚፈለገው መንገድ ለማስፈፀም የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሟል።

የአወሊያው ቡድን ምርጫውን ለመቆጠቀጠር የወሰደው ቀዳሚው እርምጃ  በስራ ላይ ያለው የእስልምና ጉዳዮች ምከር ቤት ምርጫውን ማካሄድ አይችልም የሚል ነበር። ይህ ቡደን በስራ ላይ ባለው መጅሊስ ላይ ጠንካራ የማጥላያ ዘመቻ አካሂዶ ስለነበር፣ ምርጫው በዚህ ምክር ቤት ቢመራ ተኣማኒነቱን ስለሚያጎድለው፣ ገለልተኛ በሆነው የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንት (ኡላማዎች) ምክር ቤት መሪነት እንዲካሄድ ተወሰነ።

የአወሊያው ቡድን ግን አሁንም ከእጄ ሊያመልጠኝ ነው ብሎ የሰጋውን የምርጫ ሂደት መቃወሙን አላቆመም። ቡድኑ ምርጫውን የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው የኡላማዎች ምክር ቤት ሃይማኖታዊ ምክንያቶችን አቅርቦ የመራጮች ምዝገባና ምርጫው ከመስጊድ ውጭ በሆነ ስፍራ እንዲካሄድ ያሳለፈውን ውሳኔ ተቃወመ። ምርጫው በመስጊዶች መካሄድ አለበት የሚል አቋም ነበር የያዘው።

የአወሊያው ቡድን ምርጫው በመስጊዶች ይካሄድ የሚል አቋም የያዘው፣ የራሱን ቡድን ታማኞች አደራጅቶ በየመስጊዱ አሰማርቶ ስለነበረ በእነዚህ ታማኞቹ አማካኝነት  ምርጫውን በሚፈልገው አቅጣጫ ለመውሰድ ነበር። ይህም አቋሙ ግን ተቀባይነት አላገኘም።

በመጨረሻም የኡላማዎች ምክር ቤቱ በየቀበሌው በቀጥታ የድምጽ አሰጣጥ ስንስርአት አስመራጮችንና የምርጫ ታዛቢዎችን አስመረጠ፡፡ እነዚህ በሕዝብ የተመረጡ አስመራጮችና ታዛቢዎች ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድ አዳራሽ ታድሞ  ከታዳሚው መሃል እጩዎችን ጠቁሞ አዛው በቀጥታ ድምጽ በመስጠት  ይእስልምና ምክር ቤት አባላትን መርጧል፡፡

ይህ ምርጫ ግልጽ ስለነበረ የአወሊያው ቡድን አንድም እንከን አውጥቶ ሊያጣጥለው አልቻለም፡፡ በዚህ አኳኋን በየቀበሌው በሕዝብ የተመረጡት የሙስሊሙ ተወካዮች በየደረጃው እስከ ሃገር አቀፍ ደረጃ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባላትን መርጠው አመራሮችንም ሰየሙ፡፡ይህ የሙስለም ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት መሪ ተቋም አሁን ስራውን በሰላም አያከናወነ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ እፍኝ የማይሞሉ የአወሊያው ቡድን ጀሌዎች አሁንም፣  “ምርጫው የአህባሽ፣ ምርጫው የቀበሌ፣ … ምንትስ ቅብርጥስ” የሚል የቂል ተቃውሞ በማሰማት ላይ ይገኛሉ። የአወሊያው ቡድን ይህን የሚያደርገው በተለይ አርብ በሚካሄድ የፀሎት ስነስርአትን አስታኮ ነው።

የአወሊያው  ቡድን ለወራት ሲዶልት ከነበረበት መስጊድ የወጣው በሰኔ ወር 2004 ዓ/ም ነበር፡፡ በዚው ወቅት በአዲስ አበባ  የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በመካሄድ ላይ ሳለ ሳያስፈቅድ ህዝባዊ ስብሰባ ይጠራል፡፡  ይህን ያደረገው የውጭ አገራት መሪዎችና አለም አቀፍ ጋዜጠኞች ባሉበት ሁከት አስነስቶ ትኩረት ለመሳብ ነበር።  ቡድኑ በዚህ ወቅት ሳያስፈቅድ ህዝባዊ ስብሰባ  መጥራት እንደማይችል መንግስት ቢያሳውቅም፣ ይህን አሻፈረኝ ብሎ በመላ አገሪቱ ያዘጋጃቸውን ደጋፊዎቹን ወደአዲስ አበባ ጠራ።

ይህ ስብሰባ ህገወጥ በመሆኑ እንዳይካሄድ ለማስቆም የፀጥታ ኃይሎች ሙከራ ሲያደርጉ፣ አስቀድመው በጥቂት የአዲስ አበባ መስጊዶች ለመደቡዋቸው የሁከት አስፈፃሚዎቻቸው ስልክ ደውለው፣ በሌሊት ከሐይማኖታዊ ስርዓት ውጭ ህዝበ ሙስሊሙ ወደመስጊድ እንዲመጣ ጥሪ አስተላለፉ።

ይህን ተከትሎ በየመንደሩ የሰገሰጉዋቸው ጥቂት ስሜታዊ  ወጣቶች በሌሊት ከቤታቸው ወጥተው የሙስሊሞች መኖሪያ ቤቶችን እያንኳኩ “ጀሃድ ነው ውጡ” እያሉ ለአመፅ እንዲወጡ ቀሰቀሱ። በዚህ ቅስቀሳ እንደገመቱት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከቤቱ ወጥቶ ለሁከት አላማቸው ከጎናቸው አልተሰለፈም። ሁከቱም ከሸፈ፡፡

በዚህ አኳኋን በሌሊት እንዲቀሰቀስ የተሞከረውን ሁከት ለማረጋጋት የተሰማሩ የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ድንጋይ በመወርወር ጥቂት ፖሊሶች ላይ የመቁሰል ጉዳት አደረሱ። ይህ በሆነ ማግስት ከሰአት በኋላ በአንዋር መስጊድ አካባቢ ፣ በህንፃዎችና በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ላይ ድንጋይ በመወርወር መጠነኛ የንብረት ውድመት አደረሱ።በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በአማራ ክልል ከሚሴ አካባቢም በፖሊስ ሰራዊት አባላት ላይ የሕይወት መጥፋት በንብረትም ላይ መጠነኛ ጉዳት ያስከተሉ ቀላል ሁከቶች ተቀስቅሰው በህብረተሰቡ ሙሉ ትብብርና በፖሊስ ኃይል ብልሃት የተላበሰ እርምጃ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር የዋሉበት ሁኔታ ይታወሳል፡፡

ቡድኑ በዚህ አኳኋን በዚያም በዚህም ቢወራጭም በሃይማኖት ሽፋን የያዘውን ስውር አጀንዳ እንዲያሳከ ከጎኑ የሚሰለፍ በማጣት የጥቂት ስሜታዊ ወጣቶች ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ጩኸቱ ደበዝዞ አሁንም ብልጭ ድርግም ማለቱ አልቀረም። ማንም የማይሰማው በአርብ የፀሎት ስነስርዓት ላይ በተለይ በአንዋር መስጊድ አንድ ጥግ ላይ ብልጭ ብሎ የሚጠፉ ከንቱ ጩኸት ወደ መሆን ተቀይሯል።

የአክራሪው ቡድን እንዳሰበው ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ቢሆን ኖሮ፣ ጩኸቱ ጥቂቶች፣ በአዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባም በአንድ መስጊድ - በአንዋር መስጊድ፣ ከዚህ መስጊድም አንድ ጥግ ላይ ብቻ ከጯሂው ውጪ ማንም ሳይሰማው የሚከስም ባልሆነ ነበር።

ይህ የጁሙዓ (የአርብ) የፀሎት ስነስርዓት ታዳሚዎች ውስጥ ተሰንቅሮ የሚጮሕ ቡድን ባለፈው አርብ ጥር 10 ፤ 2005 ዓ/ም ለወራት ከቆየበት አንዋር መስጊድ እዛው አካባቢ ወደሚገኘ  “በኒን” ወደተባለ መስጊድ መሄዱን ሰምተናል። የሚገርመው እዛው በኒን መስጊድ የሰገዱ ሙስሊሞችም ጯሂው ቡድን እነርሱ ውስጥ ተጠልሎ ሲንጫጫ አልሰሙትም። በዕለቱ አንዋር መስጊድ ደግሞ አንድም አዋኪ ድምጽ አልተሰማበትም፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ሙስሊሞች ቡድኑ በእለቱ ወደ በኒን መስጊድ ተሰዶ እንደነበር አልሰሙም፡፡ የአወሊያው ቡድን እንቅስቃሴ ከአንድ አመት በፊት ሲጀመር አንሰቶ እንደትልቅ ጉዳይ ሲያሟሙቀው ከነበረው  የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም ወሬ ነው የሰሙት።

እንግዲህ ሙስሊሞች በመላው ኢትዮጵያ ነው የሚኖሩት። በተለይ አርብ በሁሉም የአገሪቱ መስጊዶች በነቂስ ወጥተው ነው የሚሰግዱት፡፡  የሁከትና የብጥብጥ አጀንዳ አንግብ የተደራጀውና ጥቂት አባላትን የያዘው ቡድን ባለፈው አርብ ወደ በኒን መስጊድ ሲሄድ አንዋር መስጊድ ያለአንዳች ድምፅና መወራጨት የፀሎት ስነስርዓቱ በሰላም ተካሂዷል።

ይህ ሁኔታ ጉዳዩ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሳይሆን፣ ሃይማኖትን በሽፋንነት የሚጠቀም ስውር የፖለቲካ አጀንዳ ያለው ጥቂቶችን ያካተተ ቡድን ጉዳይ መሆኑን በግልፅ ያመለክታል ።

ሰሞኑን ከወደኤርትራ አፈትልኮ የደረሰን ዜና ደግሞ ይህንኑ ያረጋግጣል። ይህ ዜና ከ200 በላይ የኤርትራ ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች በአስመራ ባካሄዱት ዝግ ስብሰባ ላይ የተነገረን ጉዳይ የያዘ ነው።

በዚህ ዝግ ስብሰባ ላይ የኤርትራ መንግስት የፀጥታ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ተኸለ ክፍላይ በቅፅል ስማቸው ተኸለ ማንጁስ ባቀረቡት ሪፖርት ኢትዮጵያ ላይ በተከተልነው የስለላና የፕሮፓጋንዳ መንገድ ምክንያት የሃገሪቱን ህዝብ መቆጣጠር ችለናል ያዘዝነውን ተቀብሎ፣ ችግሮች ቢያጋጥሙም ተቋቁሞ እንዲኖር አድርገነዋል፣ ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ “የወያኔን ቀልብ ለመቆጣጠር ባለፉት ሰባት አመታት አልሸባብን ተጠቅመናል። አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ በፈጠርነው አልሸባብ ችግሩ ወደኢትዮጰያ ተሸጋግሯል። እስላማዊ አጀንዳ ያለው በሚመስል መልኩ በኢትዮጵያ መስጊዶች የሚታየው ብጥብጥ የጥረታችን ውጤት ነው” ብለዋል።

ይህ ከአንድ ዓመት በፊት ከአወሊያ መስጊድ ከተጀመረውና፣ አሁንም ከላይ አንደተገለፀው በአንዋር መስጊድ አካባቢ የማይጨበጥ ጩኸት ከሚያሰማ ቡድን ጀርባ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሰው የሸአቢያ እጅ እንዳለበት የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ ይህን የነገረን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሳይሆን ገለልተኛ የውጭ ሚዲያ ነው፡፡

ይህን የአወሊያውን እንቅስቃሴ  ሻዕቢያ ራሱ አላስጀመረውም ሊባል የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር እንኋን፣ ሻአቢያ ጉዳዩን ኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ ለመቀስቀስ አመቺ ሆኖ ስላገኘው ጠልፎት አጀንዳ እያቀበለው ሊሆን መቻሉ ግን የሚያጠያይቅ አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ የአወሊያው ቡድን አንቅስቃሴ ከሻአቢያ ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል የሚያመለክቱ ነገሮችን ቀደም ሲልም አስተውለናል፡፡ ኢትዮጰያን ለማበጣበጥ ባለው ፍላጎት የሸኣቢያን ጡት የጠባው ግንቦት ሰባት የተባለ አሸባሪ ቡድን ጉዳዩን ያለወጉ ሊያጋግል አበክሮ መስራቱ፣ ሸአቢያ ከጀርባ መኖሩ አይቀሬ መሆኑን እንድንገምት አድርጎን ነበር፡፡

በተለይ የግንቦት ሰባት ባለሟልና አፈ ቀላጤ የሆነው ታማኝ በየነ የተባለው የመድረክ አስተዋዋቂ “አላሁዋ ኩበር” የሚል ሙስሊሞች የፈጣሪን ታላቅነት የሚገልፁበትን የተከበረ ሃረግ፣ ሃይ ሎጋ ሽቦ የሚያወጣ ያህል በቆሻሻ አፉ አንደዋዛ እያንቧረቀ መድረክ ላይ ሲያቅራራ የሰማንና የተመለከትን ደግሞ እርግጥም ሸኣቢያ በጉዳዩ ውስጥ እጁ እንዳለበት ተረድተን ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ በተለይ አርብ እርብ በአንዋር መስጊድ የሚሰማው ጫጫታ ከጀርባው ሸኣቢያ መኖሩን በቅርቡ ከሸኣቢያ የደሕንነት  ኃላፊዎች ሰምተናል፡፡

እናም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን፣ በዚህ ቡድን ውስጥ የተሰባሰቡ ስሜታዊ ወጣቶች አውቀው አለያም ባለማወቅ ተደናግረው የኢትዮጵያና የህዝቧ ጠላት የሆነውን የሻዕቢያን አላማ እያሳኩ መሆናቸውን ተገንዝበው፣ ሊያርሟቸው፣ አልታረም ያሉትን ደግሞ ለሕግ አሳልፈው ሊሰጡ ይገባቸዋል። ይህን የማድረግም ሃይማኖታዊ፣ ሞራላዊ እንዲሁም የህግና የዜግነት ግዴታ አለባቸው።