ሂዮማን ራይት ዎችን ምን አስደነገጠው?

  • PDF

ታከለ ዓለሙ (ጥር 23/2005)

የእንግሊዝ መንግሥት ለኢትዮጵያ ፓራ ሚሊተሪ ኃይል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለሥልጠና ሊሰጥ ነው፡፡ የእርዳታውን መሠጠት ተከትሎ በዘጋርድያን ጋዜጣ ላይ የወጣውን ዜና ተመርኩዘው ሂዮማን ራይትስ ዎችና  ተከታዮቹ የተቃውሞ  ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

የእንግሊዝ መንግሥት በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቱ  አማካኝነት በአምስት ዓመታት ውስጥ የሠጠው ገንዘብ እስከ 15 ሚሊዮን ፓውንድ የሚደርስ ነው፡፡ የተሠጠው ገንዘብ በመሠረቱ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ ለሚካሄደው የሰላም ግንባታ ተግባር የሚውል  ነው፡፡ ድጋፉ የአካባቢው ሰላም የተረጋገጠ ዋስትና ያገኝ ዘንድ የሠራዊቱን ብቃት የማሳደግ  አስፈላጊነቱ ታምኖበትም ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን ቀና ዓላማ ማጣመምና መመንዘር የሚቀናቸው እነ ሂዮማን ራይትስ ዎች ጩኸታቸውን  ሲያቀልጡት ከርመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ አሸባሪነትንና እሰላማዊ አክራሪነትን የማስፋፋት ተልዕኮ ሲያራምዱ የነበሩት አልኢትሃድ አል ኢስላሚያ የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቀው በመግባት በአጋዴን ውስጥ ጥፋት ሲያደርሱ እንደነበርና ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ጦር ሀይል መመታታቸው ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በጎረቤት አገር ሶማሊያ የተንሰራፋው የአልቃይዳው ክንፍ አልሻባብ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ እንደልቡ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ዓለም በይፋ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  በነዚሁ ሀይሎች የሚታገዘውና በገንዘብና በጦር  መሳሪያ የሚረዳው  ራሱንም "የአጋዴን ብሔራዊ ነፃነት  ግንባር" ብሎ የሚጠራው ቡድን /ዛሬ መከፋፈል ጀመረ እንጂ/ የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ  ታላቅ ጥፋት አድርሷል፡፡ በዚህም የተነሳ የኦጋዴንና የአካባቢው ሕዝብ ሰላማዊ ሕይወቱ ስጋት ውስጥ ገብቶ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ደግሞ የሕዝቡን ደህንነት የማረጋገጥ ግዳጅ መወጣት የሚገባው በመሆኑ በእነዚሁ ኃይሎች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን  ወቅታዊ ግዴታውን በብልሃትና በከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጣ በመሆኑ የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ ችሏል ፡፡ ይህንን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ርምጃ በ"ጩኸቴን ቀሙኝ" የሃገራችን ይትባሃል ተጨባጭ ሁኔታውን በተቃራኒው በመገልበጥ የሰብዕዊ መብት እንደተደፈረ፤ የዜጎች መብት እንደተጣሰ፤ ሴቶች በመንግስት ወታደሮች እንደተደፈሩ በማስመሰል እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተደጋጋሚ የሀሰት ሪፖርት በማውጣት ሃሰተኛ ክስና ወንጀላ ሲያሰሙ ኖረዋል፣ አሁንም እያሰሙ ነው፡፡

እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች "ከፍተኛ የሰብዕዊ መብት ጥስትና ግድያ በአጋዴን ክልል ለሚፈፅመው የኢትዮጵያ ፖሊስ ልዪ ኃይል የስልጠና ድጋፍ በሚል የእንግሊዝ መንግስት የመደበው በብዙ ሚሊዮን  የሚቆጠር ፓውንድ አግባብ አይደለም፤ ሰብዓዊ መብትን ለሚጥሱና ለሚረግጡ ኃይሎች ማበረታቻ እንደመስጠት ስለሚቆጠር ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው" ሲሉ የእንግሊዝን መንግሥት ከሰሞኑ ወንጅለዋል፡፡ የእንግሊዙ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት በበኩሉ ለፓራ ሚሊቴሪው ኃይል የሚሰጠው ሥልጠና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት የሚካሄድ መሆኑንና ግቡም በአካባቢው ያለው ሰላም የበለጠ እንዲረጋጋ፣ በሰላማዊ ህብረተሰብ ሙሉ ተሳትፎ በፀጥታ ማስከበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ሙያዊ ክህሎታቸው እንዲያድግ ማድረግ መሆኑን ይገልፃል፡፡ 

በመሠረቱ በአካባቢው የተሠማራውና እስከ 14ሺህ የሚደርሰው ልዩ ሀይል የኢትዮጵያ መደበኛ ሠራዊት ሳይሆን ከኦጋዴን ተወላጆች የተውጣጣ ልዩ የጸጥታ አስከባሪ ሀይል ነው፡፡ የተመለመሉትም ግጭቱ  ይካሄድበታል ከተባለው አካባቢ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና የተሰጠውን ሃላፊነት በሲቪሉ ውስጥ እንዴት አድርጎ መወጣት እንዳለበት በሚገባ የሚያውቅ ነው፡፡ እንኳን ለራሱ ዜጎች ይቅርና ለሌሎችም ቢሆን በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የተመሠከረለት የሲቪሎች አለኝታ ነው፡፡  መሠረታዊ ሀቁን ወደ ጎን በመተው የሂዩማን ራይትስ ዎችም ሆነ የዘጋርድያን ውንጀላ ያው ከአመሠራረታቸው የሚመነጭ መሆኑን ለሰላም የቆሙ ኃይሎች ሁሉ የሚረዱት ጉዳይ ነው፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች ቀደም ሲል ከነበረው ታሪኩና አሁንም ድረስ ሙጭጭ ብሎ ከያዘው ጸረ ኢትዮጵያ አቋሙ በግልጽ እንደምንረዳው ኢትዮጵያን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጊዚያት ያወጣቸው መግለጫዎች በቅጥፈት የተሞሉ እንደነበር በርካታ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል። የዘገባው ሚዛናዊ አለመሆን፣የመረጃ ምንጮቼ የሚላቸውም ያው የታወቁት የጥፋት ኃይሎች ብቻ መሆናቸው፣አልፎ አልፎም ተጨማሪ የመረጃ ምንጮቼ የሚላቸውን ሰዎችና አካላት ማንነት በግልጽ ለመናገር የማይደፍር፣የሚያቀርባቸው ዘገባዎች አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚያሰሙት ሃሰተኛ ክስ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑና ይህንንም በቅብብሎሽና በተመጋጋቢነት የሚያስተጋቡ መሆናቸውና በየጊዜው የሚያወጣው ክስ ልዩነቱ ዘገባው የወጣበት ጊዜ መለያየቱ ካልሆነ በስተቀር ይዘቱና ጭብጡ ምንጊዜም አንድ ዓይነት መሆኑን ከብዙ በጥቂቱ ማንሳት ይቻላል።

ኧረ ለመሆኑ ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ተገደሉ ስለሚላቸው  10 ሰዎች እውነተኛ ማንነት በሚገባ መርምሮና አጣርቶና በትክክልኛ ማስረጃ አስደግፎ እንዳላቀረበው ከላይ የቀረቡት የድርጅቱ ቋሚ የአሰራር ሁኔታዎች ግልጽ ማሳያዎች ናቸው። ትክክለኛ ማጣራት ባላካሄደበት ሁኔታ ከራሳቸው አልሻባብ አባላት በኢ-ሜልና በፋክስ የሚደርሰውን ሃሰተኛ ውንጀላ እውነት እንደሆነ በማስመሰል የኢትዮጵያን መንግስት፤ ሰላምና ጸጥታን  ለማስከበር የተሰማራውን የፖሊስ ልዩ ሀይል በሰብአዊው መብት ጥሰት ቢከስ ሰሚም አድማጭም አይኖረውም፡፡ ሂዩማን ራይት ዎች በኦጋዴን አካባቢ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ስም ለሕዝቡ  የትምህርት፤ የንጹህ ውሀ አቅርቦት እርዳታ እንደርጋለን በሚል ሽፋን ለዓመታት ተሰማርተው የመረጃና የስለላ ስራ ሲሰሩ የነበሩ አንዳንድ የውጭ ድርጅቶች በመንግስት ስለተደረሰባቸውና አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ስለተደረጉ ያደረበትን ንዴትና ብስጭት ለመወጣት ሲል የሚያቀርበው የተለመደ ውንጀላ ነው፡፡

በሰብአዊ መብት መከበርና መጣስ ስም በምዕራቡ ዓለም ሊበራል ከበርቴዎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በላይ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ተቆራቋሪ ሆኖ ለመቅረብ መሞከሩ አስቂኝም አሳዛኝም ነው፡፡ ለነገሩ የሰብአዊ መብት አጀንዳን በማራመድ ስም  ጭምብል አጥልቆ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ካላጋበሰ ህልውናው እንደሚያከትም ስለሚያውቅ ለሂዩማን ራይትስ ዎች የዚህ ዓይነት ሃሰተኛ ዘገባና መግለጫ ማቅረብ ዋነኛው የገቢ ማግኛ መንገዱ ነው፡፡  በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሃገራት የውስጥ ጉዳይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን በማራመድና አፍራሽ ሚና በመጫዎት የጎደፈ ታሪክ ያለው እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያን መንግስትና ሰራዊቱን በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሰውና የሚወነጅለው ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሶማሊያ በመነሳት ወደ ምስራቃዊ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በተለያየ መልኩ በመስረግ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሱ ያሉት የአልሸባብና አልቃይዳ ምልምሎች በዓለም አቀፍ አሸባሪነት የተፈረጁ መሆናቸውን ሳያውቅ ቀርቶ ወይንም ጠፍቶት እንዳልሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ዙሪያ በአሸባሪዎች የታጠረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ወይንም የአፍሪካ ቀንድ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ በሶማሊያ ከፍተኛ አሸባሪ የሆነው አልሸባብ የሚንቀሳቀስበትና ከየመን፣ከመካከለኛው ምስራቅና ከሌላው የዓለም ክፍል ከሚገኙ አሸባሪዎች ጋር ሳይቀር በመቀናጀት የሚሰማራበት፣ ለአካባቢውም ሆነ ለዓለም ሰላም አስጊ የሆነው ሀይል የሚገኝበት መሆኑን የዓለም አቀፍ የመረጃ ተቋማትና ሃገራት ያረጋገጡት እውነት መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን በኦጋዴንና ከዚያም ባለፈ በሰሜን ምስራቅ የሃገራችን ክልል አካባቢ በጥፋት ሀይሎች መታፈናቸውን፣መገረፋቸውን፣መቁሰላቸውን መገደላቸውን፣ለስደትና ለእንግልት መዳረጋቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች አያውቅም ለማለት አያስደፍርም፡፡

አንድ በሕዝብ የተመረጠና ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ለሕዝቡ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ መስራት ያለበትን ያውቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆኑ  ክልላዊ መንግሥታት ነጋሪ ሳያስፈልጋቸው  ተግባራቸውን ይረዳሉ፡፡ የግዛቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥትና በአካባቢው የተሰማራው የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ ሃይል ደግሞ የክልሉን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት የማስከበር፤ የአሸባሪዎቹን ጥቃት የመከላከልና የማምከን፤  ተከታትሎ  የመምታት ከተቻለም ይዞ ወደ ሕግ የማቅረብ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ማንም ሰው የሚረዳውና የሚቀበለው እውነት ነው፡፡ በፀጥታ ማስከበር ተግባር ላይ የተሰማራ የፖሊስ ልዩ ሀይልም ሆነ መደበኛ ሠራዊት፤ ከጥፋት ኃይሎች ጥቃት ሲሰነዘርበት፤ ቦምብ ሲወረወርበት፤ ፈንጂ እየተጠመደ በየመንገዱ መኪኖች ሲጋዩበት፤ ሲቪሉም ወታደሩም ሲሞት ሲቆስል፤ የመንግሥትና የህዝብ ንብረት ሲወድም፣የመሰረተ ልማት አውታሮች ከጥቅም ውጭ ሲደረጉ ለምን በአሸባሪዎቹ ላይ ተኮሳችሁ፤ ለምን ራሳችሁን ተከለከላችሁ፤ እነሱ ሲተኩሱ እናንተ መሞት ብቻ ነበረባችሁ የሚል ሕግ በዓለም ላይ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ሀይል ሆኖ በሕብረ ብሔራዊነት በአፍጋኒስታን ዘምቶ ከዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ጋር ሲዋጋና ሲፋለም የነበረው የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የካናዳ፣ የአውስትራሊያና የሌሎችም ልዩ ሀይል በአፍጋኒስታን ገጠሮች በሕዝቡ መሃል የመሸጉ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎችን  በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከኢትዮጵያ ምስራቃዊ ክፍል ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሲዋጋና ሲፋለም ነበር፡፡ በዚህ ዓይነቱ የጦር ቀጣና በሚኖር ፍልሚያ ሰላማዊና ንፁሃን ዜጎች ሰለባ የሚሆኑበትም አጋጣሚ በተደጋጋሚ ተከስቶ  እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ መሃል ከመሸገ ሀይል ጋር የሚደረግ ውጊያ ከየትኛውም ዓይነት የውጊያ ዓይነቶች ሁሉ እጅግ አስቸጋሪው መሆኑን ዓለም አቀፍ የጦርነትና የወታደራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ አልሻባብ አልኢትሀድና ኦብነግ የሚንቀሳቀሱት በሕዝቡ ውስጥ መሸገውና ሕዝብን በማስገደድና በማስፈራራት እንደ ከለላ እየተጠቀሙ  ነው፡፡ ፀጥታ ለማስከበር አሸባሪዎቹን ነጥሎ ለማውጣት ይህ ምን ያህል ከባድና አስቸጋሪ ተግባር መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎችና ሌሎችም ቢያውቁም እውነቱን ለመናገር ግን ድፍረቱ የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ልዩ ፖሊስ ሀይልም ሆነ የመከላከያ ሰራዊት ሰላም ለማስከበር በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ላይ አሸባሪዎችንና ተባባሪዎቻቸውን በከፍተኛ ስልትና ወታደራዊ ጥበብ ከሕዝብ ነጥሎ በማውጣት የመምታት ልምድ ያጎለበተ እንደሆነ በሚገባ የሚታወቅ ሲሆን፣ያለው ተጨባጭ ተሞክሮ የሚያሳዬውም ይህንኑ ሃቅ ነው።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ተመራማሪ ተብላ የተመደበችው ክሌር ቤስተዳ የእንግሊዝ መንግስት ልዩ ሀይሉን ለመርዳት እቅድ ማድረጉ አሳሳቢ ነው  በማለትም  ሃሰተኛ ክሶችን ክሶችን ደርድራለች፡፡ የእንግሊዙ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት  ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ አክራሪ እስላማዊ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎችን በመዋጋት ረገድ ለእንግሊዝ ቁልፍ አጋር በመሆኗ ለኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የተሰጠው የእርዳታ ፕሮግራም በራሱ ቡድን የሚመራ ሲሆን፤ ዓላማውም በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን  ማድረግ  ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የፀጥታ ሀይሎች እንዲሁም የፍትሕ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ናቸው  ሲል ነው ያስታወቀው፡፡
ይህ የሰላምና የእድገት ፕሮግራም ተግባራዊ የሚሆነው መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ሲሆን ምንም ዓይነት ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ካዝና አይሄድም ወይንም አይደርስም ብሏል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያካሂደውን ስም የማጥፋት ዘመቻ የለጋሾች ቡድን የአውሮፓ ሕብረት አባላት ባደረጉት ጉብኝት፣ አሜሪካና እንግሊዝ፣ እንዲሁም  በአካባቢው የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባደረጉት ምርመራና ማጣራት የሂዩማን ራይትስ ዎችን ክስና ውንጀላ በማስረጃ ለማረጋገጥ ባለመቻላቸውና ሃሰተኛ በመሆኑ ሁሉም ውድቅ አድርገውታል፡፡ ይሄንን የሂዩማን ራይትስ ዎች ጩኸት በመደገፍ የሚያስተጋቡት በውጭ የሚገኙ አንዳንድ ተቃዋሚዎችና የትጥቅ ትግል እናደርጋለን ብለው የተሰለፉ አንድ ወይም ሁለት የሚሆኑ የተቃዋሚ ሀይሎች ርዝራዦች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አሸባሪዎች በኦጋዴን ክልል ሰላማዊ ዜጎችን፣ የመንግስት ሃላፊዎችንና የሕዝብ አስተዳዳሪዎችንና ሕዝቡን በማገልገል ሥራ የተሰማሩ የልማት ባለሙያዎችን ሲገድሉ የህዝብ ንብረት ለበርካታ ዓመታት ሲያወድሙ በነዚህ  ወቅቶች ሁሉ ሂዩማን ራይትዎች አንድም ጊዜ ትንፍሽ አላለም። ከዚህ ይልቅ የመረጠው የጆሮና አይኔን ይድፈነው ዝምታን ነው። ምክንያቱም ሃቁን መቀበል አይፈልግማ።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት በኦጋዴን ክልል ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት የጦር መሳሪያ ይዞ ከሚዋጋው ኦብነግ ጋር የጦር መሳሪያቸውን አስቀምጠውና ሕገመንግሥቱን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ አብዛኛዎቹ ወደ ሰላማዊ ሕይዎት መመለስ ችለዋል፡፡ ብዙዎችም ተጨባጭ ሁኔታውን ራሳቸው በሚገባ ተገንዝበው በሶማሊ ክልል ለእድገት  በሚበጁ በርካታ የልማት ስራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ የቀሩትም ቢሆኑ እንደሚመለሱ ተስፋ ያለ ሲሆን፣ ከዚህ በተጻራሪው የተሰለፈው የጥፋት ኃይል ግን የሰላም ወዳዱ የኦጋዴን ክልል ሕዝብ ድጋፍ እንደሌለው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰብአዊ መብት ስም በአለም አቀፍ አሸባሪነት ከተፈረጀው አልቃይዳ ጋር አባልና ተባባሪ ሆነው በመሰለፍ የአፍሪካን ቀንድን ብሎም ዓለምን በሽብር ለመናጥ ከተሰማሩት የአልሻባብ ተዋጊዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ሀይሎች ጥብቅና ቆም መከራከሩ ሁኔታውን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡  አሸባሪዎቹ ሰው ይግደሉ፤ ይሰሩ፤ ይግረፉ ፤ ይስቀሉ፤ ሴቶችን ይድፈሩ፤ ቤት ያቃጥሉ፤ ንብረት ይዝረፉ፤ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ዜጎቹን ከጥፋት መጠበቅ የለበትም፣ እጁን አጣጥፎ  ይቀመጥና በዝምታ ይመልከት የሚለው አቋሙ ግን በምንም ዓይነት መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይሆንም፡፡ ይህን የመሰለ የቀጥታ ጣልቃ ገብነትና ወገንተኛ አቋም ከአንድ የሰብአዊ መብት ተማጓች ነኝ ከሚል ዓለም አቀፍ ተቋም ሲሰማ በእጅጉ አሳፋሪ ነው፡፡ ተቃውሞውም ሆነ ክሱ እንደተለመደው ውድቅ ነውና ሂዩማን ራይትስ ዎች እጁን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሳ እንላለን፡፡