አትምረጡ፣ በእንመርጣለን ተሸነፈ!!

  • PDF

ታከለ አለሙ (ጥር 23/2005)

እየተቃረበ ከመጣው የክልልና የአካባቢ ምርጫ ጋር ተያያዞ እንድነትና መድረክ የመሩት የ33ስቱ ፓርቲዎች ስብሰብ ለምርጫ ቦርድ ያቀረብነው ጥያቄ አልተመለሰልንም በሚል እየሄዱበት ያለው መንገድ ከተያዘው ስላማዊ ትግል፤ የአገር ልማትና ግንባታ ጋር የሚራመድ አይደለም፡፡ በቅርቡ ግን ከ33ቱ ፓርቲዎች ውስጥ አምስቱ በምርጫው እንደሚሳተፉ ገልጸው ራሳቸውን ከስብስቡ አውጥተዋል፡፡

መንግስትም ሆነ ምርጫ ቦርድ ጥያቄአችንን በአግባቡ አላስተናገደም፤ ከፓርቲዎቹ ጋር ለመደራደርም ፈቃደኛ አለመሆኑ አስቆጥቶናል፤ ጥያቄአችንን ደፍጥጠውታል ፡፡ ስለዚህም ከባድ ቢሆንም የሕዝብ ንቅናቄ እንፈጥራለን ነው እያሉ ያሉት ፡፡ ይህ ጉዳይ እሰከ ምን ድረስ ይዘልቃል? ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው፡፡ ለምርጫ ቦርድ የቀረቡት ጥያቄዎች ከምርጫ ቦርድ የስራ ባህርይ ጋር የሚሄዱና የማይሄዱ የሚገኙበት ቢሆንም ጥያቄዎቹ ቀድሞ በነበረው ምርጫ በተዘጋጁ የውይይት መድርኮች በቂ ምላሽ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም አሁን እንደ አዲስ ማንሳቱ ሌላ ዙር አለመግባባትና ትርምስ ለመፍጠር የታቀደ መሆኑን ከማሳየቱ ውጪ አዲስ ጉዳይ የለውም፡፡

ይህን ሂደት በበላይነት እያስተባባረና እየመራ ያለው አንድነት ፓርቲና መድረክ  ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር አስቀድመው የመብሩትና ስሩት በዲያስፓራ ከሚገኘው ፅንፈኛ ተቃዋሚ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ በክልልና በአካባቢው ምርጫ ተወዳድረው እንደማያሽንፉ ስለሚያውቁት ይህንን መስረታዊ ድክመታቸውን ከወዲሁ ለመሽፈን ያላቸው አማራጭ ይህን የመለስ የተቃውሞ ድምፅ አስተባብሮ ማሰማት ነው፡፡

በተለይም በአረቡ ዓለም የተካሄዱትን የአመፅ አብዮቶች አነሳስና ውድቀት የእኛ ተቃዋሚዎቸ  በቅጡ አልተረዱትም፡፡ በመሰረቱ ተቃዋሚው ያቀደው ሕዝባዊ ንቅናቄ ምን መልክ ነው ያለው? ወደየትለ ያመራል የሚለውን ማሰብም ተገቢ ነው፡፡ ተቃዋሚው በተለይ አንድነትና መድረክ አጀንዳ አደርገውና ቀን ከለሊት እየሰሩበት ባለው በዚህ ጉዳይ በትልቁ እየተንቀሳቀሱ ያሉት አመፅ እንዲቀሰቀሰ መስራትና ማስተባበሩን ተያይዘውታል፡፡ ለዚህም በዙሪያቸው ለግዜውም ቢሆን ካስተባበሯቸው 33ስስቱ የፓለቲካ ድርጀቶች  ውስጥ አምስቱ ለቀዋል፡፡የሌሎቹም አንዳንድ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በእርግጠኝነት መገመት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ሆኖም እስከመጨረሻው ወጥ የሆነ አቋም ይዘው ይዘልቃሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ህዝባዊ ንቅናቄ የሚሉትን ለማሳካት ሌሎች ሕጋዊ ያልሆኑ ማሕበራዊ መድረኮችንም እየተጠቀሙ ለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አቅም በፈቀደ ውጥናቸውን የማሳካት ስትራቴጂ አውጥተው እየተራመዱ የማስተባበር ስራዎችንም ውስጥ ውስጡን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ዋነኛው "የምርጫ ካርድ አትውሰዱ፣በምርጫው አትሳተፉ፣ "የሚለው ቅስቀሳቸው ቢሆንም ይህ አጉል ጥረታቸው ሰሚም አድማጭም አላገኘም፡፡ በተቃራኒው ህዝቡ በብዛት ወጥቶ እየተመዘገበ ነው፡፡

ሕጋዊውን መድረክ ተጠቅሞ በምርጫ መሳተፍ የሕዝቡን ድምፅ ውጤትም መጠበቅ ሲችሉ አንድነትና መድረክ እንዲሁም ለአጀቢነት ያስለፋአቸው 28ቱ ፓርቲዎች ገና ምርጫው ሳይጀመር ከምርጫው ሜዳ ራሳቸውን ማግለላቸውን ጥር 4/2005 ተሰብሰበው ውሳኔ ያስተላለፋ ሲሆን ቀደም ሲልም በተናጠል ፓርቲዎቹ የየራሳቸውን ውሳኔ አሳልፈው ከመጡ በኋላ ነው ወደ ጋራ አቋም መጥተው የአንሳተፍም ውሳኔ የሰጡት ፡፡

በተገኘው መረጃ መስረት በዚህ ወር መጨረሻ ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት አቅደዋል፡፡ ‹‹ የአንሳተፍም›› ድምጽ ውሳኔውን የሰጡት በአንድ ድምጽ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲ በየግሉ  ምርጫ የማይሳተፍበትን ምክንያትም አቅርቧል፡፡   ህዝቡ ደግሞ እንሳተፋለን በሚለው ውሳኔው የምርጫ ካርድ እየወሰደ ነው፡፡ ምናልባትም በስም ደረጃ ከሁለትና ሶስት ፓርቲዎች በስተቀር ሌሎቹን ህዝቡ ጭርሱንም ግራ አጋቢ ከሆነው ስመ ብዙነታቸው አንፃርም አያውቃቸውም ለማለት ይቻላል፡፡ በህዝብ ስምም መነገድ ይከብዳል፡፡

በጥቅሉ  በሌሎቹ ተቀባይነት እንዲኖረው በማቀድ አንድነትና መድረክ ቀድመው ያወጡት ጥያቄና ምክንያቶቻቸው ሲታይ በአሁኑ ግዜ በሀገሪቱ የተስተካከለ የምርጫ ስርዓት ገልለተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ አለመኖር ኢሕአዴግና፣ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት ለነጻ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ቁርጠኝነት አለመኖር ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበርና ደንታ ቢስ መሆን፤ በሕዝባዊ ጥያቄዎች በጉልበተኛና በመሳሪያ በመፍታት አባዜ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከተደራጁ ሰላማዊ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር አለመፍቀድ የሚሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ጥያቄአቸውን ለጠ/ሚሩ ጽ/ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው መልስ እየጠበቁ መሆኑም ገለጸዋል፡፡ የጋራ ስትራቴጂ መንደፋቸውንና ሕዝብን ሊያንቀሳቅስ የሚችል የትግል ስልት እንጠቀማለን ሲሉ እነ አቶ አስራት ጣሴ ተደምጠዋል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በጋራ 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስብሰባ ለመጥራት ተስማምተዋል፣ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ሂደት በኋላ  ግን ከመካከላቸው አምስቱ ፓርቲዎች ለቀው ወጥተዋል ፡፡

እንደ አዲስ ተነሱ የተባሉት ጥያቄዎች በቀደሙ ዓመታት መድረክን ጨምሮ  በአንዳንድ ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ከ33ቱ ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ ስያሜ ያላቸው ከአራትና ከአምስት አይበልጡም፡፡ ሌሎቹ በክልል ደረጃ ብሔረሰብን መሰረት ባደረገ አደረጃጀት የተዋቀሩና የሚወክሉትም ሕዝብ በአካባቢያቸው ብቻ የተወሰነ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ከአጠቃላይ የአባላት ስብጥር አንጻር ሲታይም በብሔራዊ ደረጃ የተዋቀሩት ፓርቲዎች የየራሳቸው የዓላማና የግብ ልዩነት ያላቸው ሲሆኑ በፊት በቅንጅት ስም ተሰባስበው በኋላ ላይ የተለያዩ ናቸው፡፡ በፓርቲ ስያሜ ደረጃ የተዋቀሩት ደግሞ ስሙን ከመያዛቸው በስተቀር ወይንም በጅምላ የየብሔረሰቡ አባል የእኛ አባል ነው ካላሉ በስተቀር ጥቂት አመራሮችና በነሱ ዙሪያ የተሰባሰቡ  ከ200-300 የማይበልጡ አባላት ነው ያሉዋቸው፡፡
ይህ እንዳለ ሁኖ የቁጥራቸው 33 መሆን "ብዙ ናቸው" የሚል ግንዛቤ ለውጭው ተመልካች ለመፍጠር በተለይም ለነጮቹ ወዳጆቻቸው ካልሆነ በስተቀር የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ ለዲፕሎማቶችና ለውጭ ሰዎች 33 ፓርቲ ሲባል ታዲያ ምን ቀረ ገዢው ፓርቲ ብቻውን ነው የሚወዳደረው የሚለውን ስዕል ለመፍጠር ታቅዶ የተሰራ ነው፡፡ ከነዚህ ውጭ ወደ 45 የሚሆኑት አሁንም ከምርጫ ቦርድ ጋር አብረው እየሰሩ ስላሉና  ከሰላሳሶስቱ ፓርቲዎች ከወጡት አምስቱ ጋር ሲጨመሩ 50 ያህል ፓርቲዎች በውድድሩ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ይታሰባል ማለት ነው፡፡  አንሳተፍም ካሉትና ከፈረሙት ውስጥም ጥቂት የማይባሉት ውሎ አድሮ በሚከሰት ልዩነት የተለየ አቋም በመያዝ ራሳቸውን ከስብስቡ ሊያገሉ እንደሚችሉ እርግጥ ነው፡፡

ከሕጋዊ አካሄድ አንጻር ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚገኙበት የጋራ ፖለቲካ መድረክ እያለ የስነምግባር ደምቡን አይመቸኝም አልፈርምም ባለው አንድነትና መድረክ ፓርቲ ስር መሰባሰብ ለምን አስፈለጋቸው? የስነ ምግባር ደምቡን የፈረሙ ከ28ቱ ፓርቲዎች ውስጥ አሉበት ወይ? የሚለውም ጥያቄ ይነሳል፡፡ ሌላው በምርጫ ስላለመሳተፋቸው በምክንያትነት ያነሱት ነጥብ ኢሕአዴና በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት ለነጻ፣ ፍትሓዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ቁርጠኝነት አለመኖር፤ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር ደንታ ቢስ መሆን የሚለው ነጥብ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ በውል ሊጤን የሚገባው ነጥብ ይኖራልና ይህንኑ በአጭሩ እንመልከት፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርቲ በፖለቲካ አመለካከት በነጻነት የመደራጀት፤ የመሰባሰብ፤ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሕገ መንግስቱ አጽድቆ እውቅና ሰጥቶ የሕግ ጥበቃም አድርጎለት ወደ ተግባር ያሻገረው ኢሕአዴግ በሀገሪቱ ገና ዳዴ በማለት ላይ ያለው ጅምር የዲሞክራሲ ጭላንጭል የበለጠ እንዲጎለብት የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የነጻው ፕሬስ እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ኢሕአዴግ በሕዝብ ስምምነትና ይሁንታ ባጸደቀው ሕገ መንግስት መሰረት ነው፤ የትላንቶቹም የዛሬዎቹም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕልውና እውቅና አግኝተው የተደራጁት፤ የተወለዱት፡፡ ይሄንን መሰረታዊ እውነት መካድ ለተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም፡፡
ሌላው ነጥባቸው ለሕዝባዊ ጥያቄዎች በጉልበትና በመሳሪያ የመፍታት አባዜ ፤በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከተደራጁ ሰላማዊ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆን የሚለው ይገኝበታል፡፡ እዚህ ላይ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ሕጋዊና ሰላማዊ መድረክ ባለበት ሁኔታ የግድ ሁከትና አመጽ እንዲፈጠር ፤ንብረት እንዲወድም ፤የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፤ እሳትና ብጥብጥ በመለኮስና በመጫር ብቻ ነው ወይ ማቅረብ የሚቻለው?

ጎማ ካልተቃጠለ ፤ድንጋይ ተወርውሮ አውቶብስ ካልተሰበረ፤ የሱቆች መስታወት ካልረገፈ ወይንም ድንጋይ በመኮልኮል መንገዶች ካልተዘጉ፤ ወጣቱን ሀይል በዚህ ተግባር በማሳተፍ ብቻ ነወይ ሕዝባዊ ጥያቄዎች የሚቀርቡት ወይንስ የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ደህንነት እንዲሁም የህዝቡን ሰላማዊ የእለት ተእለት ኑሮ በማናጋት አለመረጋጋት በመፍጠር ነው ሕዝባዊ ጥያቄ የሚቀርበው? ሀገሪቱን ወደ ከፋ አዘቅት ከመውሰድ ውጭ  ከዚህ የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ ተቃዋሚዎቻችን ከትውልዱና ከዘመኑ ጥያቄ ጋር መራመድ ተስኖአቸው፤፡የአመለካከትና የጋራ መግባባት ልዩነታቸው በሰፋበት ሁኔታ ላይ ሆነው፤ ጥርጣሬና አለመግባባታቸው ከትላንት አስከ ዛሬ ባልተፈታበት፤ በጋራ  ከሚያቆማቸው የሚለያያቸው ገዝፎ በወጣበት መልኩ በጋራ ተረባርበን ኢህአዴግን መጣል አለብን ከሚል ሀሳብ በመነሳት ብቻ መሰለፉ ትርገም የለውም፡፡

የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ መታገል ወይንም ለመምራት ሲዘጋጁ ፍላጎት ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ የፖለቲካ ሀይል አሰላለፉን፤ የሀገሪቱንና የህዝቡን ተጨባጭ አውነትን፤  ብሄራዊና አለም ቀፋዊ ሁኔታዎችን መረዳትና መተንተንን ይጠይቃል፡፡ ሀገርንና ብሄራዊ ጥቅምን ለአደጋ አሳልፎ በሚሰጥ መልኩ ትርምስና ሁከት ለመፍጠር መሰናዳት፤ህዝቡንም የዚሁ ብጥብጥ ሰለባ ለማድረግ መዘጋጀት የሚያስከትለው ተጠያቂነት የገዘፈና መራር ነው፡፡

ለሁሉም አትምረጡ፤ የምርጫ ካርድም አትውሰዱ በሚል ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ የሰነበተውና እየተካሄደ ያለው ቅስቀሳ በህዝቡ ትክክለኛ ምላሽ አግኝታል፡፡ ህዝቡ በስፋት እየተመዘገበ የምርጫ ካርድም እየወሰደ ነው፡፡ በምርጫ ካርዱም ፍላጎቱን ተከትሎ ለሚሰራለትና ለሚያምነው ወገን ድምፁን ይሰጣል፡፡ በብሄራዊ  ምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት መራጩ ህዝብ መብቱን ተጠቅሞ በስፋት ተመዝግቧል፣ እየተመዘገበም ነው፡፡ ስለዚህም ኮረም ሞልቷል ማለት ነው፡፡የአትምረጡ ቅስቀሳ በእንመርጣለን ውሳኔና ካርድ መውሰድ ተሸነፈ ማለትም ይኸው ነው፡፡