የመለስ ራዕይ ስለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ

  • PDF

ስሜነህ (ጥር 23/2005)
በቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ በተከበረው የዘንድሮው የአርብቶ አደሮች ቀን በአል ከተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ በመንደር ማሰባሰብን የተመለከተው አጀንዳ ቀዳሚው ነው። አርብቶ አደሩን በመንደር ማሰባሰብ ያስፈለገበት ምክንያት እና  በአርብቶ አደሩ አካባቢ መጀመሪያ ምን ምን ችግሮች ነበሩ  የሚሉት  ነጥቦች ደግሞ በስፋት የተነሱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አርብቶ አደር በተለያየ ቦታ ተበታትኖ ለራሱና ለእንስሳቶቹ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ በዚሀ ምክንያት የተለያዩ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተጠቃሚ አልነበረም፡፡ በተበታተነ ቦታ ላይ ለሚኖር ህዝብ መንግስትአገልግሎት ለማቅረብ ይቸገራል፡፡ አቅምም አይኖረውም፡፡ በተሰባሰበ ሁኔታ ባለመሆናቸው በመጀመሪያ የጤና፣የተምህርት፣የንፁህ መጠጥ ውሃና ሌሎች የተሻሻለ የአሰራር ዘዴና የቴክኖሎጂ ድጋፍ መስጠት አልተቻለም፡፡
ሁለተኛው አርብቶ አደሩ ተበታትኖ በመኖሩ ምክንያት ለፀረ ሰላም ሀይሎች ተጋላጭ ነው፡፡ አርብቶአደሮቻችን   የሚኖሩት በጠረፋማ አካባቢ ስለሆነ ከውጭም ከውስጥም ፀረ ሰላም ኃይሎችና ጉልበተኛ ነን ብለው ያሰቡ አካላት ስለሚያጠቋቸው አስተማማኝ ሰላም እንዳልነበራቸው በየመድረኮቹ ተንጸባርቋል፡፡
ሶስተኛው እጅግ ኋላ ቀር በሆነ አኗኗር ዘይቤ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከሀገራችን ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ኋላ ቀር የሆነ የአኗኗር ዘይቤና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በስፋት የሚከናወንባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ አገራችን በደህነት ላይ የምትገኝ ብትሆንም በእነርሱ ላይ የነበረው ድህነት እጅግ የከፋ ነው የነበረው፡፡     
ስለዚህ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙ አላማ ከዚህ በላይ  የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ማገዝ እንደሆነ ጥናት ያቀረቡ ተመራማሪዎች ለታዳሚያኑ ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት እንዲያገኙ፣ ለፀረ ሰላም ኃይሎች እንዳይጋለጡ፣ ሰላማቸው የተጠበቀ እነዲሆን፤ዘመናዊ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እንዲላበሱና አምርተው የተሻሻለ ኑሮ አንዲኖሩ ፣   አገራችን እያደረገች ካለችው የእድገትና ብልፅግና ጉዞ እነሱም ተቋዳሽ እነዲሆኑ ማስቻል እንደሆነም በተጨማሪነት ተገልጿል ፡፡
ህዝበ ካለበት አካባቢ ብዙም ሳይርቅ በጥናት በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በቀላሉ ተጠቃሚ እነዲሆኑ እየተደረገ ስለመሆኑም  ከሶማሌ ክልል ከቀረበ ተሞክሮ ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ውሃው ከዚያው ከመንደሩ ቀርቦለት  ለእንስሳቱም ሆነ ለራሱ ውሃና ሳር ፈለጋ ከመኳተን መዳኑንም በቪዲዮ ተደግፎ ከቀረበልን መረጃ አይተናል፤   መኖውንም ከዚያው ከመንደሩ ማምረት ጀምሯል፣ ይህ ደግሞ   ጉልበቱ እንዲቆጠብ ይረዳዋል፡፡ ብዙ ጊዜ በጉዞ ላይ የሚሳተፉት ሴቶች ስለሆኑ ይህ ፕሮግራም በዋነኝነት ደግሞ ለሴቶች የተለየ ጥቅም አለው፡፡ የሴቶችን ጉልበት በመቀነስ በሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች እነዲሳተፉ እያደረጋቸው ነው፡፡
ሂደቱ በእነዚህ አካባቢዎች ፈጣን ልማት እንዲመጣ  የሚያስችል ነው፡፡ ስለዚህ የመንደር ማሰባአቡ ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማመጣጠን ብሎም  ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ ያለመ ሲሆን ፕሮግራሙ የሚካሄድባቸው ክልሎች ደግሞ አፋርና ሶማሌ አርብቶ አደር ክልሎች በተጨማሪ ቤንሻበጉል ጉምዝና ጋምቤላ ናቸው፡፡
በጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ መሪነት በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ከተነሱ አብይ ነጥቦች ውስጥ ፕሮግራሙን ለማስፈፀም በመንግስት የተያዙ ስትራቴጂዎችን  የተመለከተውም ይገኝበታል። ይህ ፕሮግራም ቀደም ብሎ እንደተያዘ በሀገራችን የገጠር ልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ በግልጽ መቀመጡ ይታወቃል፡፡ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ወይም በዱሮ መጠሪያው የሰፈራ ፕሮግራም የተሳተፉ የሶማሌ አፋር ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ አርብቶ አደሮች ውጤታማ ሁነዋል፡፡ ስለዚህ አዲስ ስትራቴጂ ሳይሆን ቀደም ሲል የተያዘና የግብርናና የገጠር ለማት ፖሊሲና ስትራቴጂ አካል መሆኑ በየመድረኮቹ ተወስቷል፡፡
ይህ  አንደኛው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም መነሻ ሲሆን ሁለተኛው መነሻ የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ነው፡፡ የአገራችን የእድገትና  ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ አርብቶ አደሩ በዋነኛነት በእንስሳት ሀብቱ በመሳተፍ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ በወንዞች አካባቢ ማሰባሰብ ሲሆን እነዚህ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ሰፋፊ ወንዞች፣ክረምት ከበጋ የሚፈሱና አገር አቋርጠው የሚሄዱ ወንዞች ያሉባቸወ አካባቢዎች ናቸው፡፡
ለምና ድንግል መሬት፣ሰፊ ተፋሰስ ያለበት ፤ የገፀ ምድር ሀብቱም ሰፊ ስለሆነ በአካባቢው መንግስት የሚከተለው ስተራቴጂ በከርሰ ምድርም ሆነ ገፀ ምድር ውሃ ከአነስተኛ መስኖ ከተቻለም እስከ መካከለኛና ከፍተኛ አካባቢዎች የተስማማ ቴክኖሎጂ በመጠቀም አርብቶ አደሮቹ ህይወታቸውን የሚቀይሩበት አሰራር አንጂ ለሁሉም አንድ ዓይነት ስትራቴጂ እንዳልሆነም አወያዮቹ ነግረውናል፡፡
በእርጥበት አጠሮቹ ይሄን ጉዳት የሚቀንስ፣ የምግብ ዋስትናቸውን የሚያረጋግጥ፤ ሰፊ ውሃ ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ለዚሁ የሚመች የመስኖና የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየተሰ ራ ነውስለመሆኑና ይህም በ2005 ዓ/ም ተጠናክሮ መቀጠሉ ተብራርቷል፡፡
በትግራይ፣በአማራ፣በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ቀደም ሲል የነበረው የሰፈራ ፕሮግራም በተጀመረበት ጊዜ ፕሮግራሙ ምን ያህል ፈታኝ ስራ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እነዚህ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ደግሞ የማስፈፀም አቅማቸው እንደነዚያኞቹ ክልሎች ያደገ አይደለም፡፡ የማስፈፀም አቅማቸው አነስተኛ ቢሆንም እንደመጀመሪያነቱ የተከናወነውን ስንመለከት ከተጠበቀው በላይ የተሳካ ፕሮግራም ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
ይሄውም በ2003 እና በ2004 የበጀት ዓመት በተካሄደው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ከ200ሺህ በላይ ሰዎች የተሰባሰቡ ሲሆን እያንዳንዱ በአምስት ቤተሰብ እንኳ ቢባዛ የቤተሰቡ ብዛት እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመት ህዘብ ይሆናል፡፡ እነዚህ ዜጎች የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችንም ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ወደማምረትም ተሸጋግረዋል፡፡
ስራው የመጀመሪያ ቢሆንም ለቀጣይ ጊዜ ተሞክሮ ተግኝቶበታል፤ ከልምዶቹም አቅም ተገንብቷል፡፡ ይህ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ከሁሉም በላይ እርግጠኝነት/ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ፈታኝ ስራ ነው፡፡ በዚህ ቁርጠኝነት በሚጠይቅ ስራ ስኬታማ መሆን  በመጀመሩ   ክልሎቹ ራሳቸውን እያበቁ አንዲሄዱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡   
ስራው ተጠናቋል ሰዎቹ ተሰባስበዋል ተብሎ ግን የሚቆም እንዳልሆነም ተወስቷል፡፡ ስለዚህ የሁለቱ ዓመት ስራን የማጠናከር ዝግጅትና ክንውን እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህም የመንግስት ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ከፍተኛ ሲሆን የቁርጠኝነቱ መንስኤ  ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነው የመንግስት ባህሪ ነው።
መንግስት ዜጎች ከድህነትና ከኋላ ቀርነት እንዲወጡ የሚፈልግ ነው፡፡ በሌላ በኩል በህገመንግስታችን አንቀጽ 89 ንኡስ አንቀጽ 4”መንግስት በእድገት ወደ ኋላ ለቀሩ ክልሎች ብሄር ብሄረሰቦች ህዘቦች የተለየ ድጋፍ ያደርጋል” የሚለውን የፌደራል መንግስትም የክልል መንግስታትም ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ፕሮግራሙ ያጋጠሙት ችግሮችይታወቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከኮንትራከተሮች ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ ስለዚህ በዚሀ ዓመት ከኮንትራክተሮች ድክመትና በጊዜ ግንባታዎችን ካለማጠናቀቅ ጋር የተያያዙ ችገሮችን ለመፍታት አስቀድሞ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም በተሳታፊ አርብቶ አደሮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በተሰጠበት ወቅት ተገልጿል፡፡ አስከ አሁን ምን ያህል አባወራዎችና/እማወራዎች በየክልሎቹ በመንደር ተሰባስበዋልየሚለውን ስንመለከት
በሶማሌ ክልል 140851፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ 33000ና በጋምቤላ 30243 በድምሩ 204094 አባወራዎችና/እማወራዎች ተሰባስበዋል፡፡ ይሄ በ2003 ና በ2004 ዓም ብቻ የተከናወነ ነው፤ በነዚህ ጊዜያቶች ደግሞ ዜጎቹ በተሰባሰቡባቸው አካባቢዎች አዲስ የተገነቡትን ተቋማት ማየትም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ቀደም ብለው የተገነቡት አንደተጠበቁ ሆነው አዲስ የተገቡት ብቻ 532 አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣741 የውሃተቋማት፣409 የሰው የጤና ተቋማት፣244 የአንስሳት ጤና ተቋማት፣360 የገበሬ ወይም የአርብቶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት የተገነቡ ሲሆኑ 120 የእህል ወፍጮዎች 4211የመስኖ ሞተር ፓምፕና 379329 የእጅ የአርሻ መሳሪያዎች ተሰራጭተዋል፡፡
በመንደር የተሰባሰበው ህዝብ እራሱ ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለአከባባዊ የፀጥታ ኃይል የሰላም አጋር መሆን ችሏል፡፡ በሰላም በመኖሩም ወደ ልማት መለካም አስተዳደርና ሌሎች አጀንዳዎች እንዲገባ አድርጎታል፡፡
በመጀመሪያ የምናነሳው በሰላም እየኖረ ነው የሚለውን ነው.ሁለተኛ ልናነሳ የምንችለው በፊት የተበታተነ ነበረ አሁን ግን በአንድ ላይ በሆነ ጊዜ በተለያዩ አደረጃጀቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ መታቀፉን ነው፡፡ መደራጀት አቅም ነው፤ መደራጀት ጉልበት ነው፡፡ ስለዚህ መብቶቹን በተሻለ ደረጃ ያስከብራል፤ በመንደር በመሰባሰቡ ምክንያት ልጆቹን በቅርብ ያስተምራል፤ ንፁህ ውሃ ይጠጣል፤ጤንነቱ እየተጠበቀለት ነው፤ የተሻሻለ ኑሮ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ግብርና ምርትና ምርታማነትም ገብቷል፡፡
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ያገኛል፤ ባለሙያዎች ተመድበውለት ገበያ ስላገኘ ምርቶቹን በተሻለ ዋጋ ሽጦ ገቢውን እያሳደገ ነው፡፡ የግብአትና የቴክኖሎጂ ድጋፍም ይደረግለታል፡፡ በሌላ በኩል በፊት በተሟላ መንገድ በእርሻ ውስጥ ያልነበረና እንዲያውም ማረስ የማይታወቅበት አካባቢም ሁሉ አሁን ማረስ ጀምሯል ማለት ብቻ ሳይሆን ከግብርና ውጭ ያሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ላይ መሳተፍ ጀምሯል፡፡ መንደሮቹ የከተማ ባህሪ ስለሚኖራቸው ለከተማ  የሚያስፈልጉ የተለያዩ ነገሮችን የሚሰሩ ሰዎች ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ እንግዲህ የፕሮግራሙ ትሩፋቶች ናቸው፡፡
የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም እንደሚታወቀው ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ተቃቅሞ ሲገጥመው እንደነበር እናስታውሳለን ይህን በተመለከተም የሚመለከታቸው አካላት በጋዜጠኞች ተጠይቀዋል።
እነዚህ ዜጎች የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙን በትክክል ባለመገንዘብ፤ ካለማወቅ፤ጥቅሙን ካለመረዳት እንደሚቃወሙ የገለጹት የስራ ሀላፊዎች፡፡ ግን ደግሞ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ደግሞ አንዳንድ የከሰሩ ፖለቲከኖች መንግስትን ፊት ለፊት የሚታገሉበት አጀንዳ ሲያጡ መንግስትን የሚያጣጥሉበት አጀነዳ ያገኙ እየመሰላቸው፤ መንግስት ለህዝቡ የማይጠቅም ስራ እንደጀመረ፣በመሬት ወረራ ሌሎችን አካላት ለመጥቀም፤ አስገድዶ እንደሚወስዳቸው በማሰብ ከሀቅ ውጭ የሚሄዱበት ሁኔታ እንዳለም አብራርተዋል፡፡
የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም አገራችንን ከድህነትና ኋላ ቀርነት የሚያላቀቀ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ ለዩነት ማሳየት የሚገባ አልነበረም፤ ትክክለም አይደለም፡፡ ይሄንንም መንግስት በየአገኘበት አጋጣሚ ለማስተማርና ለማሳወቅ ይሞክራል፡፡ ስለዚህ የውስጡ በዚህ ላይ ነው ያለው፡፡ የውጩን ስንመለከት ከኢትዮጵያውያን በላይ ለኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪ ሆኖ መገኘት ነው ችግራቸው፤ ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚያስብ የለም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ለማያስቡ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ መስጠት ይቻላል፡፡ በምንም መስፈርት ግን ዜጎች ለራሳቸው ሊቆረቆሩ ከሚችሉበት በላይ ማንም ሰው ሊቆረቆርላቸው አይችልም፤ በዓለም ላይም የለም፡፡ እነዚህ ውጪ ያሉ ሰዎች ሌላ ነው አጀንዳቸው፡፡
በድህነት እንድንማቅቅ ነው የሚፈልጉት፤ በድህነት ስንማቅቅ እርዳታ እንፈልጋለን፤ እርዳታ በምንፈልግበት ጊዜ እርዳታ የሚሰጥ አካል ያስፈልጋል፤እርዳታ የሚሰጠው አካል እኛ አገር በሚቆይበት ጊዜ ብዙ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ስለዚህ አኛ ከድህነት እንድንላቀቅ አይፈልጉም፡፡ እኛ ከነሱ ከምናገኘው ስንዴና ፍርፋሪ በላይ እነሱ በውጪ ምንዛሪ የሚያገኙት ገቢ ይበልጣል፡፡
ለምሳሌ  በደቡበ የአገራችን ክፍል ቱርሚ አካባቢ ልብስ ያለበሱ የማህበረሰቡ ክፍሎች አሉ፡፡ ይሄ መልካም ነገር አይደለም። ሰው ልብስ መልበስ አለበት።  እነዚህ የውጪ ሰዎች ግን ከነሱ ጋር ፎቶ ግራፍ እየተነሱ እንደ አንስሳ፣ አንበሳን እያየን አንደምንዝናናው ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ፊት ለፊት ወጥተው እነዚህን ሰዎች ለምን ታስተምራላችሁ ለምን ህይወታቸው ይቀየራል አስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ “ስለዚህ ዓላማቸው በኛ ድህነት ላይ እነሱ መዝናናት ነው፤ ይሄንን ደግሞ እኛ መፍቀድ የለብንም፤” በሀገራችንም ለነሱ መረጃ በመስጠት በባንዳነት የሚያገለግል ካለ ፊቱን ወደ ራሱ መመለስ አለበትም ተብሏል፡፡
ከዚህም ውጭ የተፈጥሮ ሀብት ተቆርቋሪ መስለው ይመጣሉ ያሉት ጥናት አቅራቢዎች በመንደር ስታሰባስቡ ለተፈጥሮ ሀብታችሁ አልተጨነቃችሁም ብለው እንደሚሞግቱም ተናግረዋል፡፡ መንግስት  የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ ግልጽ የሆነ ስተራቴጂ አለው፡፡ አስከ አሁንም በሄደበት የተሳካ ስራ መሰራቱ ሊጤን ይገባል፡፡ 
መሬት ለኢንቨስተር ለማስለቀቅ ነው የመንደር ማሰባሰቡን የምትሰሩት  የሚሉትንም በተመለከተ የሚመለከታቸው አካላት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህ ጉዳይ የሚነሳው በቤንሻንጉል ጉምዝና በጋምቤላ አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሰፊ መሬት ያለው እዚያ አካባቢ ስለሆነ፡፡ አፋርና ሶማሌ አርብቶ አደሮች አካባቢዎች ቢሆኑም አስከ አሁን ባለው ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሰፊ መሬት ያለባቸው አካባቢዎች ግን አይደሉም፡፡  አንዱን መረጃ ብቻ ብናይ ጋምቤላ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር ሊለማ የሚችል መሬት አለ፡፡ ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ 300 ሺህ ሄክታር አልተሰጠም፤ ማለትም 1/10ኛው ብቻ ነው እስከ አሁን ለኢንቨስተሮች የተሰጠው፡፡ በጣም እጅግ ሰፊ የሆነ መሬት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ሰፊ መሬት ባለበት መሬት ፍለጋ ብሎ ሰውን ማፈናቀል አያስፈልግም፣ የመጀመሪያው እና ተጠየቃዊ የሆነው ምላሽ ይሄ ነው፡፡
የመሬት እጥረት በሌለበት ብዙ ያልለማ “መሬት በተትረፈረፈበት አገር ውስጥ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ይሰራዋል ተብሎ አይታሰብም።  ለህዝብ ሚቆረቆር መንግስት ይህን አያደርግም፡፡ በሌላ በኩል በመንደር ለሚሰባሰቡ ዜጎች ደግሞ እያንዳንዳቸው ሦስት ሄክታር አንዳንዱ ጋር ደግሞ አስከ አራት ሄክታር ይሰጣቸዋል፡፡ አንድ ሰው ቤተሰቡን ጨምሮ አራት ሄክታር ማረስ አይችልም፣ በጣም ብዙ ጉልበት ነው የሚፈልገው፡፡ እናም በተግባር እንዳየነው ብዙዎቹ አንድ ሄክታር አንኳን ለማረስ ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች የመሬት ወረራ የሚሉት መሰረት የሌለው ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ እነዚህን መረጃዎች ግብርና ሚኒስቴር ስንት መሬት እንዳለው፣ መሬቱ ለነማን እንደተሰጠም ጭምር በየወቅት በድረ ገጹ ላይ ያስቀምጣል) ጋምቤላም፣ቤንሻንጉልም ስንት መሬት አለ ስንቱ መጠን በኢንቨስተሮች ተይዟል እስከ አሁን ስነቱ ደግሞ ነፃ ነው የሚለውን ወቅታዊ መረጃ ከዚሁ ማየት ይቻላል፡፡
እነዚህ መሬት ተወረረ ሲሉ የነበሩ ሰዎች መጨረሻ ላይ መሬት ለራሳቸው እንደሚፈልጉ የገለፁበትም ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ መሰረት የሌለው መሆኑን  ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ መሬቱ ደግሞ ለኢንቨስተር የሚሰጠው ለተወሰነ ጊዜ በክራይ ነው፡፡ ለዘለቄታው እየተሸጠ አይደለም፡፡ የመሬት ወረራ የሚያስኘው ነገር የለም፤የተወሰነ ጊዜ ያለማሉ፤ ውል አለው፣ በውሉ መሰረት የማይሄዱ ከሆነ ጊዜው ከመድረሱ በፊት የሚነጠቁበት ስርዓት እንዳለም በዚሁ በግብርና ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ተመልከቷል። 
በመጀመሪያው ክፍል መጣጥፌ እንደጠቀስኩት እነዚሀ የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች  የአገሪቱን የቆዳ ስፋት 60 ይይዛሉ፤ ከ10 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይኖርባቸዋል፤በጣም ሰፊ ፀጋዎች፣ ትላልቅ ወንዞች ሰፊ ተፋሰሶች አሏቸው። ለምና ድንግል መሬት ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የአገራችን አካባቢዎች ሳይለሙ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማሳካት የሚባል ነገር የለም፡፡
የአገራችን በርከት ያለው ክፍል በአግባቡ ውጤታማ ባልሆነበት ሁኔታ እቅዱ ሊሳካ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከህዝቡ አኳያም ብንወስድ 12 ከመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸውና፡፡ በፖቴንሻል አካባቢም ብንወስደው በተለይ ሰፋ ያለው የኢንቨስትመነት አካባቢ የቤንሻንጉል ጉምዝ የጋምቤላ፣አፋርና ሶማሌ እንደገና ደግሞ ኦሮሚያና ደቡብ ለእቅዱ መሳካት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡
ሱማሌና አፋር የልዩ ድጋፍ ክልልም አርብቶ አደርም ናቸው፡፡ ስለዚህ የነዚህ አካባቢዎች ልማት ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ወሳኝ ነው፡፡ የመንደር ማሰባሰቡ ፕሮግራም ዓላማ ተመጣጣኝ ልማት ማረጋገጥ፤ በነዚህ አካባቢዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦችን ማሳካት ነው፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንዲሳካ ካስፈለገ  በአርብቶ አደር አካባቢ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው ጥናቶቹ  ያመለክታሉ ፡፡
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ማሳካትና አርብቶአደሩን በመንደር የማሰባሰብ ስራ በቀጥታ የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ ለምሳሌ በሶማሌና በአፋር ክልሎች ብቻ ዘንድሮ  በፕሮጀክት ተይዘው የሚሰሩ የተፋሰስ ልማት ውሃን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ተይዞላቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው እቅዱን ለማሳካት ተጨማሪ ጥረት መደረጉን ነው፡፡ በጀቱ የክልሎቹ ቢሆንም የተሻለ የማስፈፀም አቅም ስላለው ስራውን የሚያስፅመው የፌዴራል መንግስት ነው፡፡ 
ይህ ወቅት ለአርብቶ አደሩ ህዝብ የተሻለ ህይወት ታላቅ ራእይ የነበራቸውን ታላቅ መሪ  ክቡር   በሞት የተነጠቅንበት ከባድ ጊዜ ነው፡፡  ስለሆነም በታላቁ መሪ  ባልተጠበቀ ጊዜ   መለየት አርብቶ አደሩ የተፈጠረበትን ሐዘን ወደ ቁጭት ቀይሮ እሳቸው ለአርብቶ አደሩ የነበራቸውን ራዕይ እውን ለማድረግ   በወኔ መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡ በመንደር ማሰባሰቡ ፕሮግራም ላይ ማየት የጀመርናቸውን ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን በማስቀጠል፤ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን በማሳካት፤ህያው መሆናቸውን ማረጋገጥ ከአርብቶ አደሩ የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡