ከማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ ከ130 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2005(ዋኢማ) - በዘንድሮው ግማሽ የበጀት ዓመት ከማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የተገኘው 130 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ከጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ከፋርማሲቲካልስና የኬሚካል ውጤቶችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ ነው።

ከተገኘው ገቢ 57 ሚሊየን 792 ነጥብ 2 ዶላር ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች የተገኘ ሲሆን፤ 47 ሚሊየን 62 ሺ ዶላር ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ 22 ሚሊየን 344 ሺ 300 ዶላር ከአግሮ ፕሮሰሲንግና 3 ሚሊየን 652 ሺ 200 ዶላር ከኬሚካልና ፋርማሲቲካልስ ምርቶች የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች በምርት ስብጥር ሲታይ ያለቀለት ቆዳ 82.66 በመቶ፣ ጫማ 14.48 በመቶ፣ የቆዳ ጓንት 2 ነጥብ 7 በመቶ እና የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች 0. ነጥብ 16 በመቶ ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ125 ነጥብ 08 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ከማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በግማሽ የበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፤  እቅዱን በቀሪው ወራት ለማሳካት የተለያየ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ዕቅዱን ለማሳካትም ለውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተዋፅዖ በሚያደርጉ ኝዑሳን ዘርፎች ላይ የድጋፍና የክትትል ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም አቶ መላኩ ተናግረዋል።