የአሸጎዳ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 95 በመቶ ተጠናቀቀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2005(ዋኢማ) - በሰሜን ኢትዮጵያ እየተሰራ ያለው የአሸጎዳ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 95 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ እንደገለጹት፤ በፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ዙር በተሰራው ስራ በአንድ ተርባይን 30 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል መንጭቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

አሁን እየተሰራ ያለው የፕሮጀክቱ አካል 90 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሲሆን፤ የግንባታው 95 በመቶ መጠናቀቁን ኃላፊው ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቱ የሚመነጨውን ሃይል ወደ ሀገራዊ ቋት ማስተላለፍ የሚችሉ ባለ 33 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችና ባለ 33 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ስራም ተጠናቋል በማለት ገልፀዋል።

ቀሪው 34 ታወሮችን የመትከሉ ስራ በቅርብ ወራቶች ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በሙሉ ሃይሉ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገር አስረድተዋል።
ሀገሪቱ እያከናወነች ያለው የንፋስ የሃይል ማመንጨት ስራ አካባቢን ከሚበክሉ ጋዞች ነፃ በመሆናቸው አገሪቱ ለተያያዘችው የአረንጓዴ ልማት እገዛ እንደሚኖረው ኃላፊው ተናግረዋል።

የአሽጎዳ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው የኤፍቢሲ ዘገባ ያስረዳል።