በህዝብ ንቅናቄ ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እንደሚለማ ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 23 /2005 (ዋኢማ) - በ2005 በህዝብ ንቅናቄ ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እንደሚለማ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ጌታሁን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚከናወኑ የግብርና ስራዎች መካከል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡

በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብ፣ ሐረሪ፣ ድሬዳዋ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ወደ ትግበራው መግባታቸውንም አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው ከ17 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንደሚሳተፍም አቶ ስለሺ ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የሃይል ማመንጫዎችና የመስኖ ግድቦችን በደለል እንዳይሞሉ የተፈጥሮ ሃብት ስራው በከተማም ሆነ በገጠር ተሳትፎው መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

በበጋው የተሰሩትን የተፋሰስ ስራዎችን በስነ ህይወታዊ ዘዴ ለመሸፈን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም አቶ ስለሺ ማሳሰባቸውን የኢሬቴድ ዘገባ ያስረዳል።