ኢትዮጵያና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረው እንደሚሰሩ ገለጹ

  • PDF

አዲስ አበባ ጥር 23/2005 (ዋኢማ) - ኢትዮጵያና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረው እንደሚሰሩ አረጋገጡ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ ጆኒ ካርሰንን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት አገሮቹ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በዚህም በተለይም በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የተጀመረውን ድርድር ከፍጻሜ ለማድረስ ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ በግንቦት 2005 ለምታስተናግደው የአፍሪካ የንግድና የዕድገት ዕድል (አጎአ) መድረክ ተገቢውን ዝግጅት እያደረገች መሆኗንም ለጎብኚው ገልጸውላቸዋል።

ሚስተር ካርሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአካባቢዋ አገሮች ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለችውን አስተዋጽኦ አድንቀው፤ በተለይ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት እያበረከተች ያለችውንም አሞግሰዋል።
የአፍሪካ ኅብረትም በማሊ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር እያደረገ ላለው እንቅስቃሴም ረዳት ፀሐፊው አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው የሚታወቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።