የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ንዶላ በረራ ይጀምራል

  • PDF

አዲስ አበባ ጥር 22/2005 (ዋኢማ) -የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዛምቢያዋ ንዶላ ከተማ በመጋቢት ወር የበረራ መሥመር እንደሚከፍት አስታወቀ።

አየር መንገዱ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው አየር መንገዱ ወደ አገሪቱ ሦስተኛ ታላቅ ከተማ በረራውን መጋቢት 22 ቀን 2005 ይጀምራል።

ንዶላ በመዳብ ማዕድን በሚታወቀው የአገሪቱ ክፍል የምትገኝ የኢንዱስትሪና የንግድ ከተማ መሆኗንም አመልክቷል።

አየር መንገዱ ወደ ከተማዋ የሚያደርገው በረራ በአፍሪካ 45ኛ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 72ኛው እንደሚያደርገውም መግለጫው አስረድቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ''ንዶላን በበረራ መሥመራችን ውስጥ በማካተታችን ተደስተናል።

አፍሪካን ከሌላው ዓለም ለማገናኘት የያዝነው ጥረትና ግብ አካልም ነው።በአህጉሪቱ ተጨማሪ ጣቢያዎችን በማከልም የአየር ግንኙነቱን በማሳደግም ፍላጎቷን ለማሟላት እንሰራለን''ብለዋል።

በአዲሱ የበረራ መሥመር በመጠቀም የንዶላ መንገደኞች እንደ ሙምባይ፣ ዱባይ፣ ለንደን፣ ሆንግ ኮንግ፣ ባንኮክ፣ ካይሮና ፔኪንግ የመሳሰሉ ከተሞች መጓዝ እንደሚችሉም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ከሚታወቁ አየር መንገዶች መካከል ሲሆን፣በእንቅስቃሴው በርካታ ሽልማቶችን ማግኘቱን ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘገባው አስታውሷል።