ኢትዮጵያና ቦትስዋና በአየር ትራንስፖርት መስክ በጋራ ለመስራት ተስመሙ

  • PDF

አዲስ አበባ ጥር 22/2005 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያና ቦትስዋና የአየር ትራንስፖርት መስካቸውን ለማሳደግ የሚያግዛቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በቦትስዋና የዓለም አቀፍ የትብብር ሚኒስትር ፕሀንዱ ቲሲ ስካላማኒ የተመራው የልዑካን ቡድን ትናንት ከኢፊድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሓኖምና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነቱ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ከውይይቱ በሃላም የሁለቱ አየር መንገዶች ''አምስተኛው የትራፊክ መብት''ተብሎ የሚታወቀውን አሰራር ተግባራዊ ለማደረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የትራንስፖርት ሚኒስትር ድሪባ ኩማ እንደገለጹት ስምምነቱ ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡

ስምምነቱ የንግድ ግንኙነቱ ከማጠናከር በተጨማሪ የባህልና የአኗኗር ግንኙነትን ለማሳደግም ያግዛል ብለዋል፡፡

አፍሪካ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበች ቢሆንም ሌላው አለም ጋር ሲነጻጸር አሁኑም ብዙ እንደሚቀራት የተናገሩት ሚኒስትሩ የንግድ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ግንኙነትን ለማሳደግ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በቦትስዋና በኩል ስምምነቱን የተፈራረሙት የዓለም አቀፍና ትብበር ሚኒስትር ፕሁንዱ ቲሲሰላሚኒ እንደተናገሩት ስምምነቱ የቦትስዋናና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች የሚሰጡትን አገልግሎት ያሳድጋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለአፍሪካ የአየር ትራንሰፖርት ዕድገትም የራሱን ድርሻ እንደሚጫወትም ጠቁመዋል፡፡
የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ኢትዮጵያ ለቦትስዋና በሰው ሀብት ልማት ረገድ ትልቅ ድጋፍ እያደረገች መሆኗን መናገራቸውን አዲስ ዘመን ጋዜጣን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡