ለጤናው ዘርፍ ግቦች መሳካት የተጣለ ጽኑ መሰረት!

  • PDF

ሲኢድ መሐመድ (ጥር 16/2005)

የኢትዮጵያ መግስት በጤናው ዘርፍ የነደፈውና እየተገበረው ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ የአገሪቱን ራዕይ ዳር ለማድረስ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል። መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ለመፍጠር  ጤነኛ አምራችና ብቁ ዜጐች ሊኖሩ የግድ ነው።  ፖሊሲው አጠቃላይ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ሆኖ በጣም ወሳኝ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ  ይሰጣል።

በዚህ መነጽር  በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የእናቶችን ሞት መቀነስ፣ የህፃናትን ሞት መቀነስ፣ የኤች አይ.ቪ/ኤድስን ስርጭት መግታት፣ ሳንባ ነቀርሳንና የወባ በሽታዎችን ስርጭት  መቆጣጠርና አጠቃላይ መሰረታዊ የጤና መከላከል ተግባራትን መፈጸም የሚሉ  አጀንዳዎችን ያቀፈ ነው። 

በዚህ መሰረት በተደረገው የተቀናጀ የጤና ፕሮግራም ርብርብም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በቀደሙት ስርዓታት ተንሰራፍቶ የነበረውን የጤና ችግር ትርጉም ባለው መልክ መፍታት የቻለበት ሁኔታ እንዳለ ማየት ይቻላል።  ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የጤና አጀንዳዎች በቅደም ተከተል በመተግበር አገሪቱን ማልማት የሚችል ጤናማ ህብረተሰብን ለመፍጠር ቀጣይነት ያለው የተቀናጀ ጥረት በመደረግም ላይ ይገኛል።
ጤናማና  አምራች ሕብረተሰብ ባልተገነባበት መደላድል  ልማት የሚታሰብ ባለመሆኑ የጤና ዘርፉ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በዋናነት ከሚወሰዱት የተለያዩ መሳሪያዎች እንደ አንድ ተደርጎ በመወሰዱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል። 
የደርግን ውድቀት ተከትሎ መንግስት ከወሰዳቸው ዓበይት እርምጃዎች አንዱ ጤናማ ትውልድን መገንባት ነው። ጤናማ ትውልድን ማፍራት ዋነኛው የልማት አካል ተደርጎ በመወሰዱ ይህንን ያገናዘቡ የአጭርና የረጅም ጊዜ የጤና ፕሮግራሞችን ተነድፈው  በተገቢው መንገድ በመተግበራቸው ለዘመናት የዘለቀውን የህብረተሰቡ የጤና ችግር ለመቅረፍ  የተቀናጀ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡
የጤና ስትራቴጂው ገጠርን ከከተማ ሳይለይ ሁሉም ሕብረተሰብ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በቀደሙት ስርዓታት በአገሪቱ የነበረው የጤና ሽፋን በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም ባሻገር ስርጭቱ በዋና ዋና ከተሞች ላይ ያተኮረ ስለነበር ይህንን ገጽታ ለመቀየርም ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ቀላል የማይባል ስራ ተሰርቷል። በበ1985 ዓ/ም በአገሪቱ የነበረው የጤና ሽፋን ከ38 በመቶ በታች ነበር፡፡
ከተሰጠው አሃዛዊ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ህክምና አገልግሎት የማያገኘው ህዝብ ቁጥር በጣም ከፍተኛ  ነበር።  የስርጭቱ ፍትሃዊነት መጓደልም በብሄሮች፣  ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የተጠቃሚነት ልዩነትን የፈጠረ ነበር።  በተለይ በገጠር የሚኖረው  አርሶና አርብቶ አደር ተዘንግቶ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። 
በአዲስ አበባና በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የነበረው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥም ቢሆን ለገዢው መደብ መጠቀሚያ እንጂ ድሃውን ህብረተሰብ ሙሉ በሙሉ የሚያገለግል አልነበረም። እንዳልነበረ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።  ህዝባዊ መሰረቷ አርሶ አደርና በገጠር የሚኖር ህዝብ በሆነበት  አገር በጣት የሚቆጠሩ የህክምና ተቋማትን በዋና ዋና ከተሞች ብቻ በማቆም የህዝብን ጤንነት ማረጋገጥ እንደማይቻል መገመት የሚያዳግት አይሆንም።
በአገሪቱ ገጠር ይኖር የነበረው ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ካለመሆኑም በተጨማሪ ራሱን በቀላሉ ሊከላከላቸው የሚችለውን በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል አስተምህሮና ድጋፍ የማያገኝበት ሁኔታ ነበር። 
በአገሪቱ የተቀረጸው የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ መከላከልን ማዕከል ያደረገበት ዋናው ምክንያትም ይህንን ሰፊ ህዝብ መሰረት በማድረግ ነው። አገሪቱ ያላትን ውስን ሃብት የገንዘብ አቅም በመጠቀም ሽፋኑን የማስፋት እንቅስቃሴ በማድረግ ተባብሶ የነበረውን የጤና ችግር ለማቃለል በተደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። ከ38 በመቶ በታች በከተሞች ታጥሮ የነበረው የህክምና አገልግሎት ሽፋንም አሁን ወደ 92 በመቶ ለማድረስ ተችሏል።  
የጤና አገልግሎት  ወደ ገጠር በሰፊው ዘልቆ ገብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጤና ጣቢያ አለያም የጤና ኬላ የሌለበት የገጠር ቀበሌ እንደሌለ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ ለረጅም ዓመታት የሚዘልቅ የጤና ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ተቀይሶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመደረጉ ምክንያት ተደራሽነትን ለማስፋት ተችሏል። ሽፋንና ተደራሽነትን በማስፋት ብቻ ሳይወሰን  ጎን ለጎን  የጤና አክስቴንሽን ፕሮግራም ተቀይሶ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ የነበረውን የጤና ሽፋን በማስፋፋት፣ የእናቶችንና የሕፃናት ሞትን በመቀነስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን በመቆጣጠር የኢትዮጰያ መንግስት መሰረታዊ ለውጥ መምጣቱን ዓለም አቀፍ ተቋኘማት ሳይቀሩ ይስማሙበታል። መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እያደረጉ የአገሪቱን   የጤና ሽፋኑ ማስፋት  ወሳኝ በመሆኑ እንቅስቃሴው በዚህ ቅኝት እየተደረገ ይገኛል። በዚህ  እሳቤ ጤና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን  የሀገሪቱ የገንዘብ አቅም በፈቀደው መሰረት እየተገነቡ ጎን ለጎን የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን በማስፋፋት በአብዛኛው በመከላከል ላይ ያተኮረና በተወሰነ መልኩ ደግሞ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተቀጾ በመተግበሩ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ ችሏል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሁለተኛው  የጤና ዘርፍ ልማት አንድ አካል ሆኖ እንዲካሄድ በመደረጉ በመከላከል ላይ የተመረኮዘና በተለይ በገጠር አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ያደረገ ሆኖ በከተሞችም  እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ በከተሞች ደረጃ  የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማካሄዱ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት  በመከላከሉ ሥራ ላይ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ መቀየር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

በአገሪቱ የጤና ፕሮግራምን ተግራዊ ለማድረግ  ከሕብረተሰቡ ተውጣጥተው ለሦስት ወራት ያህል ሰልጥና እየተሰጣቸው  የተለያዩ ዓይነት ቀላል የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የማህበረሰብ ጤና ሠራተኞች እንዲደራጁ በማድረግ ረጅም ርቀት መሄድ የተቻለበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም  አገልግሎት ሰጪዎቹ ወይም ሠራተኞቹ ተቀጣሪ ሳይሆኑ በጎ ፈቃደኞች በመሆናቸው የራሳቸው የሆነ ሌላ ሥራ ሲኖር የሕክምና አገልግሎቱን ትተው ወይም አቋርጠው ወደ ግል ሥራቸው የሚሄዱበት ሁኔታ ስለነበር ይህንን ሙሉ በሙሉ ለማቃለል ሌላ አማራጭ  በማስፈለጉ የጤና ኤክስቴንሽን ስራ መጀመሩ መረጃዎች ያሰያሉ፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን አገልግሎት አስቀርታ በምትኩ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በማስፋፋት በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ መሆን ችላለች፡፡ ይህ  ተግባሯ ደግሞ አገሪቱ ከዓለም የመጀመሪያና ብቸኛ ስኬታማ አገር እንዲትሆን አስችሏታል።

የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በዓለም ደረጃ  ታዋቂ እየሆነ፣ እንደምሳሌም እየታየና ለመላው ለአፍሪካ አገራት ምሳሌ ለመሆንም በቅታለች። በተምሳሌትነት መወሰድ ጀምራለች። ሌሎች የአፍሪካ አገራት የአገራችን ጥሩ ተሞክሮ እየወሰዱ በመተግባር ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአገር ደረጃ ከ34 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በማሰልጠንና በእያንዳዱ የገጠር ቀበሌ የጤና ኬላ በመገንባት ህብረተሰቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ የተገኘው ውጤት ቀላል አይደለም። መከላከል ላይ ይበልጥ በማተኮር  የጤና ኬላዎችን፣ ጤና ጣቢያዎችን፣ ክሊኒኮችንና ሆስፒታሎችን በማስፋፋት በአገራችን በዘርፉ ቀላል የማይበል ስራ ተሰርቷል።

ፖሊሲው በተነደፈ ማግስት በርካቶች የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል። አገሪቱ የሚያስፈልጋት መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ሳይሆን  ከፍተኛ የህክምና ተቋማት ማስፋፋት ብቻ እንደሆነም ሲለፍፉ ተደምጠው ነበር። አድርገውም በማቅረብ በሌሎች ፖሊሲዎቻችን ያደረጉትን የማጥላላት ሙከራ በዚህም ሞክረው እንደነበር ይታወቃል።

መንግስት አቅም በፈቀደ መልክ ይህንን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብና ይህንኑ እያከናወነ በዋናነት ግን መከላከሉን በመሰረታዊነት መወሰድ እንዳለበት በማስገንዘብና ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያትም በአገሪቱ ካሉት  የበሽታ ዓይነቶች  መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተላላፊ በሽታዎች በመሆናቸው  ነው። ይህ ከፍተኛ የበሽታ ስርጭት በመከላከል  ብቻ መግታት የሚቻል በመሆኑ የተቀናጀ ጥረት ተደርጓል።  

የመከላከል ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ  የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በየአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ሕብረተሰቡ የግልና የአካባቢ ንጽህናውን እንዲጠብቅ፣ እናቶች የወሊድ መከላከያና መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ በማስተማርና ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ወደ በላይ የሕክምና አካል ሪፈር በማድረግ ረገድ የሚያበረክቱት አገልግሎት ለጤናው ዘርፍ ስኬት የጎላ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በአገሪቱ የተለያዩ የገጠርና የከተማ አካባቢዎች በማገልገል ላይ ያሉት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞቹ 16 በሚሆኑ የጤና ፓኬጆች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና እየተሰጣቸው ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላ እንደየ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን እንድያያገኙ እየተደረገ ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።እንዲያገለግሉ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  ባለሙያዎቹ አብዛኛው የሥራ ጊዜያቸውን  ወደ ሳኒቴሽን በማድላት ሕብረተሰቡ መፀዳጃ ቤት እንዲቆፍር፣  የቤትና የውሀ ንጽህና እንዲጠብቅና አካባቢውን እንዲያጸዳ  ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ  ህብረተሱቡን ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል አስችሏል።  የገጠሩን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ በእያንዳንዱ ገጠር ቀበሌ የኬላ ጣቢያ በማቋቋም  ሕብረተሰቡ በአካባቢው የህክምና አገልግሎት የሚያገኝበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና የጤና ተቋማት መስፋፋት፤ የጤና አገልግሎት ከከተማው አልፎ የገጠር ቀበሌዎችን ማዳረስ፤ ወባንና  ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከልና ስርጭቱን በመግታት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ቀላል የማይባል ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ አገሪቱ ነድፋ እየተገበረችው ያለው የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት መሆኑ እሙን ነው።
መንግስት የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የግል ባለሃብቶች በጤናው ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፉ አመች ሁኔታዎችን በመፍጠር በርካታ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣኒያዎችና ክሊኒኮች በግል ባለሃብቶች መስፋፋት ችለዋል። እነዚህ የህክምና ተቋማት ቀላል የማይባል እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በአገሪቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት  ምንም ዓይነት የግል የህክምና ተቋም እንዳልነበረ ሲታወቅ  ሁኔታው ከሃያ ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።
የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን  የህክምና ሙያተኞችን ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲስፋፉ ተደርጓል። በዘርፉ መንግስትም ሆነ የግል ባለሃቶች የጤና ሳይንስ ማሰልጠኛ ተቋማትን በሰፊው በማስፋፋት ለዘርፉ ስኬት ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አምራች ዜጋ ባልተፈጠረበት ሁኔታ የአገር ልማትና እድገት የማይታሰብ መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት ጤናማ አምራች ዜጋን ለማፍራት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ በመተግበር የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ጤንነት ለማስጠበቅ የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የጤና ፕሮግራሙ ሰፊውን የከተማና የገጠር ሕዝብን ማዕከል በማድረግ የተቃኘ በመሆኑ በዋናነት በሽታ መከላከል ላይ ማዕከል በማድረግና የአገሪቱ የፋይናንስ አቅም በፈቀደ መንገድ ቅድሚያ ሰጥቶ  የህክምና ተቋማትን በማስፋፋት ሕብረተሰቡ ቀድሞ ራሱ የሚያደርጋቸውን ጥንቃቄዎች እንዲያደርግ በማድረግ ከዚህ በላይ ለሆነ በሽታ ደገሞ  በመስፋፋት ላይ ባሉት የህክምና ተቋማት የህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት።

የጤና ተቋማትን በመገንባትና ተደራሽነቱን በማስፋት በከተማም ሆነ በገጠር ሕብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የተደረገው የተቀናጀ ጥረት ፍሬ አፍርቶ አሁን  የተባበሩት መንግስትታት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች የጤናው ዘርፍ በአስተማማኝ መልክ ለማሳካት በሚያስችል ደረጃ ላይ ትገኛለች አገራችን ኢትዮጵያ።

ፖሊሲውና ስትራቴጂው ህዝቡ ራሱን ከበሽታ መከላከል እንዲችል የግልና የአካባቢውን ንጽህና የቤቱን ጽዳት እንዲጠብቅና የግልና የጋራ ንጽህናውን እንዲጠብቅ፤ ከተላላፊ በሽታዎች ራሱን እንዲከላከል፣  ሽንት ቤት አጠቃቀምና ሌሎችም መሰረታዊያንን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች  በእያንዳንዱ የገጠር ቀበሌ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ን በመመደብ ውጤታማ ስራ መስራት ተችሏል። 

በአገሪቱ በዘርፉ የነበረው መጠነ ሰፊ ችግር በአስተማማኝ መልክ  መፍታት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።   በዚህ መሰረት በየቀበሌው ለአምስት ሺሕ ሰው አንድ የጤና ኬላና ሁለት የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን በመመደብ አገልግሎት በመስጠት በተለይም የገጠሩን ኗሪ የጤና ችግር በአስተማማኝ መልክ የጤናውን ዘርፍ ችግር ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እያሳይ ይገኛል። ተችሏል።   በዚህም ኢትዮጵያ የተቀናጀ የጤና ፖሊሲ ጥበቃ ስራን በመንደፍና በመተግበር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን የጤና ችግር በመሰረታዊነት በመፍታት   የምዕተ ዓመቱን የጤና ዘርፍ የልማት ግቦችን ሙሉ በሙሉ የሚያሳካ ለማሳካት ጽኑ መሰረት ገንብታ በተስተካከለ ሁለንተናዊ አቋም ላይ ትገኛለች። ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች።