ዋሊያዎቹ ከዛምቢያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያገኙት ውጤት የሚያኮራና ለበለጠ ውጤት የሚያነሳሳ ነው - የስፖርት አፍቃሪያን

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2005(ዋኢማ) - በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከዛምቢያ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ10 ተጨዋቾች ያገኘው ውጤት የሚያኮራና ለበለጠ ውጤት የሚያነሳሳ መሆኑን ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት አፍቃሪያን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከዛምቢያ ጋር አድርጎ በስኬት አጠናቀቀ።

በከተማዋ በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በመስቀል አደባባይ፣ በሚሊኒክ ሐውልትና በመሳሰሉት ቦታዎች በትልቅ ስክሪን ጨዋታውን ሲመለከቱ የነበሩ አንዳንድ ተመልካቾች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ተጨዋቾቹ ያሳዩት ጥረትና ተጋድሎ ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ በመሆኑ ተደስተዋል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ሉንጉ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ለ60 ደቂቃ ያህል በ10 ተጫዋች የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያሳየው ብቃት አስገራሚና የአገሪቱን የእግር ኳስ ደረጃ የት ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባሳየው የጨዋታ እንቅስቃሴ እንደኮሩ ጠቁመው፤ ተጨዋቾቹ በአግባቡ አገራዊና ወገናዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ቀጣይ ጨዋታዎችንም በድል እንደሚወጡትም በሙሉ እምነት የገለፁ ሲሆን፤ ቡድኑ በመጀመሪያው ግማሽ ማጠናቀቂያ ላይ በምቤሱማ በተቆጠረበት ጎል 1 ለ 0 ሲመራ ቆይቶ በአዳነ ግርማ ከእረፍት መልስ ባስቆጠረው አስደናቂ ጎል አቻ በመሆን 1 ለ 1 ተለያይቷል፡፡ የሁለቱን ቡድኖች የጨዋታ ሂደት አስመልክቶ የዓለም አቀፉ የእግርኳስ ፌዴሬሽን እንደገለጸው ዋሊያዎቹን በማድነቅ፣ የእለቱ ኮከብ ተጨዋች ሳላዲን ሰይድ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በዛምቢያ አሰልጣኝና በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ጭምር አድናቆትን የተቸረው የዋሊያዎቹ ቀጣይ ጨዋታ በመጪው አርብ ከቡርኪናፋሶ ቡድን ጋር እንደሚያካሂድ ይታወቃል።