በአፍሪካ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በደቡብ አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር ተደረገ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2005 (ዋኢማ) - በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በደቡብ አፍሪካ 22 ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ባለፈው ሐሙስ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማካሄዳቸውን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ በምታስተናግደው አገር ''እግር ኳስ ለሰላም'' በሚል መርህ ግጥሚያውን ያደረጉት ከአሌክሳንድራ ከተማ የተውጣጡ ወጣቶች ናቸው።

ቀደም መግለልና መድልኦ ይደርስባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጡት ወጣቶች ኮሚሽኑ ''ሰላም ይስፈን''በሚል መርህ የሚያካሂደው ዘመቻ አካል በሆነው በ29ነኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይም ይካፈላሉ።

ኮሚሽኑ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 ጀምሮ እያከናወነ ባለው ዘመቻ እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን አዎንታዊ ሚና በመጠቀም የሰላም መልዕክት እያስተላለፈበት መሆኑን ገልጿል።

በዚህም የቡድን ሥራን፣ክህሎት ማዳበርን፣ግጭቶችን ማስወገድን፣በኅብረተሰቡ ውስጥ እርቅንና የጋራ ትብብርን ማራመድንና አፍሪካ ግጭቶች የተወገዱባት አህጉር የማድረግ አንድ የጋራ ግብ መሰነቁንም መግለጫው ያመለክታል።

ኮሚሽኑ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮናዎችን በአህጉሪቱ ሰላም ለማስፈን እንደሚጠቀምበት አመልክቶ፣የደቡብ አፍሪካው ሁለት እግሮች የሌሉት አትሌት ኦስካር ፒስቲሪዬስ የኮሚሽኑ የሰላም አምባሳደር በመሆን በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት የሰላም ችቦ ይለኩሳል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ሂሻም ኤል አምራኒ፣የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር ሙስጠፋ ካሎኮ፣የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት(ኔፓድ)ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢብራሂም ማያኪም በክብር እንግድነት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይካፈላሉ።

እንደ ኢዜአ ዘገባ  የዚህ ዓመቱ የአፍሪካ ዋንጫ ከአፍሪካ ኅብረት ምሰረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ ጋር መገጣጠሙንና በአጋጣሚው ለግማሽ ምዕተ ዓመቱ ውስጥ የተገኙ ስኬቶችን፣ችግሮችና ሰላማዊ፣የበለጸገችና የጋራችን የሆነች አፍሪካን የምትገነባበትን መንገድ ለመተለም እንደሚያስችል ኮሚሽኑ መገለጹን ኢዜአ አስታውቋል።