ኢትዮጵውያን የሂዩስተን ማራቶንና የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን በበላይነት አሸነፉ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2005 (ዋኢማ) - ኢትዮጵውያን አትሌቶች ትናንት በአሜሪካዋ ሂዩስተን ከተማ የተደረጉ የማራቶንና የግማሽ ማራቶን አራት ውድድሮችን በበላይነት አሸነፉ።

በሥፍራው በተካሄደው ውድድር በሴቶች ማራቶን መሪማ መሐመድ የቦታውን ሁለተኛ ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ ስታሸንፍ፣በወንዶች የተደረገውን ውድድር ደግሞ በዙ ወርቁ በቀዳሚነት ገብቷል።

የሃያ ዓመቷ ወጣት መሪማ ውድድሩን በሁለት ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ አጠናቃለች።ብዙነሽ ዳባ በአንድ ደቂቃ ያህል ዘግይታ ሁለተኛ ወጥታለች።

መስከረም አሰፋና መሠረት ለገሠ ተከታዮቹን ሁለት ደረጃዎች በማግኘት ውድድራቸውን መፈጸማቸውን የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያስረዳል።

በወንዶች የተከናወነውን ውድድር ደግሞ በዙ በሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ አጠናቋል። የሃያ ሁለት ዓመቱን በዙን ተከትለው ተፈሪ ባልቻና ሰለሞን ሞላ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃዎችን አግኝተዋል። ብርሃኑ ገደፋና ደረጀ አበራ ደግሞ ተከታዮቹን ደረጃዎች በማግኘት ውድድሩን ፈጽመዋል።

በዚሁ ከተማ በግማሽ ማራቶን የተካሄዱትን ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን በበላይነት አጠናቀዋል። በወንዶች ፈይሳ ሌሊሳ በ61ደቂቃ 54 ሰከንድ በመግባት አንደኛ ሲወጣ፣ድሪባ መርጊያ በስድስት ሰከንድ ተቀድሞ ሁለተኛ ሆኗል።

ውድድሩን ዊልሰን ሎያናይ በ62ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ሦስተኛ ወጥቷል። አሜሪካውያን አትሌቶች አራተኛና አምስተኛ በመሆን ገብተዋል። ማሚቱ ደስቃ በ69ነጥብ53 ሰከንድ ውድድሩን በማጠናቀቅ የሴቶች ውድድርን ማሸነፍ ችላለች።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያሉትን ደረጃዎች ኬንያውያን የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ዘምዘም አህመድ በ73 ደቂቃ ከ25ሰከንድ በመግባት አምስተኛ ሆናለች። በውድድሮቹ ኢትዮጵያውያን የበላይነታቸውንና እርስ በርስ ተፎካካሪነታቸውን ባሳዩባቸው ሁኔታዎች መካሄዳቸውንም ማህበሩን ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።