በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የተከሰተው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ በመፈታቱ መርካታቸውን ሊቀመንበሯ ገለጹ

  • PDF

አዲስ አባባ፤ ጥር 6/2005 (ዋኢማ) - በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የተከሰተው ውስጣዊ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ በመፈታቱ መርካታቸውን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ-ዙማ አስታወቁ።

ሊቀመንበሯ በአገሪቱ መንግሥትና በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ጥረት ያደረገው ሴሌካ በተሰኘው ፖለቲካዊ-ወታደራዊ ቡድን መካከል ሰሞኑን በሊበርቪል፣ጋቦን የተደረሰው ስምምነት እንዳስደሰታቸው ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ገልጿል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት ወገኖች በመቻቻልና በመልካም መንፈስ ተባብረው በመሥራት ቃላቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡትም አሳስበዋል።

የማዕከላዊ አፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መሪዎች በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ላደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተለይም የቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ፣የወቅቱ የማህበረሰቡ አገሮች ሊቀመንበር የጋቦኑ ፕሬዚዳንት ዓሊ ቦንጎ ኦንዲምባና የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሶ ንጌሶንም ቀውሱን ለመፍታት ላበረከቱት ድርሻ አወድሰዋቸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላደረገው የሎጂስቲክ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣የአገሪቱ ሁሉም ወገኖች የተደረሰውን ፖለቲካዊ ስምምነት በመተግበርና ተኩስ በማቆም ስምምነቱ እንዲያከብሩ ሊቀመንበሯ ጠይቀዋል። የአፍሪካ ኅብረትም ለስምምነቱ አተገባበርና በቀጣይ ለሚከናወነ ተግባራት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።