የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ቆይታው የታላቁ ህዳሴን ግድብ እንዲያስተዋውቅ ጥሪ ቀረበ

  • PDF

አዲስ አባባ፤ ጥር 6/2005 (ዋኢማ) - ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚጀመረው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾችና ልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካ ቆይታችው ታላቁን የህዳሴን ግድብ እንዲያስተዋውቁ ጥሪ ቀረበላቸው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችና ለልዑካን ቡድኑ የታላቁ ህዳሴን ግድብ እንዴት በደቡብ አፍሪካ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥቷል።

የጽህፈት ቤቱ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባለሙያ አቶ ዮናስ ሰርፀ ድንግል በግንዛቤው መድረክ ላይ እንደተናገሩት ተጨዋቾቹ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው እዛ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የውጭ አገር ዜጎች በተለያየ መድረክ ሲያገኟቸው ታላቁን የህዳሴ ግድብ በማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በደቡብ አፍሪካም ከተለያዩ የውጪ ሚዲያዎች ጋር ስለሚገናኙ የአገሪቱን በጎ ገፅታ በማስተወወቅ አገራቸውን ለተቀሪው ዓለም በይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥራላቸውም አስረድተዋል። የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ቡድኑ ታላቁን የህዳሴ ግድብም ሆነ የአገሪቱን መልካም ገፅታ በደቡብ አፍሪካ ቆይታው ለማስተዋወቅ የሚቻለውን ያህል ስራ ይሰራል ብለዋል።

የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ በበኩሉ በሰጠው አስተያያት ተጨዋቾቹ ከሜዳ ውጪ በሚያደርጉት ልብሶችና አልባሳት ታላቁን የህዳሴ ግድብን በማስተዋወቅ የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ ብሏል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በግንዛቤው ማስጨበጫ ላይ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀከት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ታላቁን የህዳሴ ግድብና አገሪቷን በማስተዋወቅ ዙሪያ ለተጨዋቾቹ ገለፃ አድርገዋል።