አፍሪካ ለስነ ምድር ሳይንስ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ እንደሚገባ ተገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2005 (ዋኢማ) - አፍሪካ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የምትፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ለስነ ምድር ሳይንስ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የአህጉሪቱ ስነ ምድር ከያዛቸው የተፈጥሮ ሐብቶች እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው 15 በመቶው ብቻ ነው፡፡ አፍሪካ ይኖራታል ተብሎ ከሚጠበቀው ማእድን ሐብት 85 በመቶው የሚሆነው ደግሞ እስካሁን ጥናት አልተካሄደበትም፡፡

ለዚህ ደግሞ የገንዘብ እጥረት፣ የቴክኖሎጂ አለመኖር፣ ማዕድናትን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች አለመስፋፋት እንዲሁም በስነ ምድር ሳይንስ ያለው የተማረ የሰው ኃይል ቁጥር ዝቅተኛ መሆን በምክንያነት ተቀምጠዋል፤ አዲስ አበባ ውስጥ በተጀመረው 14ኛው የአፍሪካ የስነ ምድር ማህበር ጉባኤ ፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አበራ ሞገሴ እንደሚሉት አፍሪካ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚ መስኮች የምትፈልገውን ለውጥ ለማምጣት እነዚህን ችግሮች መቅረፍ እና የስነ ምድር ሳይንስ ዘርፍ አህጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሐብት በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ ይገባል፡፡

በግብርናው መስክ ምርታነትን ለመጨመር፣ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማስፋፋትም ዘርፉ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ሀገራት በስነ ምድር ሳይንስ የሰለጠነ የሰው ኃይል ቁጥር ማሳደግ ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚም ሌላ በስነ ምድር ሳይንስ ላይ የሚደረጉ ጥናቶችን ወደ ተግባር መለወጥ፣ ሳይንሱን ማሳደግ የሚችሉ ፖሊሲዎችን መንደፍ እና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን የርስ በርስ ቅርርብ የሚፈጥሩበት ይህን መሰል ስብሳባዎችን ማጠናከርም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ ምላሽ ለመስጠትና የስነ ምድር ሳይንስን ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው ብለዋል ፕሮፌሰር አበራ ሞገሴ፡፡

የጉባዔ ዋና አዘጋጅ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ሳይንስና ማዕድን ኢንጅነሪንግ ማህበር ሊቀመንበር ዶክተር ግርማ ወልደትንሳኤ ኢትዮጵያ የበርካታ የተፈጥሮ ሐብትና ማዕድን ያላት ሀገር በመሆኗ ስብሰባውን ለማዘጋጀት እንድትመረጥ አስችሏታል ብለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የስነ ምድር ሳይንስ ባለሙያዎችን ለማፍራት ልዩ ትኩረት መስጠቷም ሌላው ለአዘጋጅነት ያስመረጣት ምክንያት ነው፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ ለአንድ ሳምንት የሚቆየውና በአዲስ አበባ የተጀመረው ይህ ስብሰባ ለአፍሪካ እድገት ፈተናዎች፣ የስነ ምድር ሳይንስ መፍትሄዎች ድርሻና ጥቅም የሚል መሪ ቃል አለው፡፡ ከ60 የተለያዩ ሀገራት የመጡ የስነ ምድር ባለሙያዎችም ከ400 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡