በፀጥታው ምክር ቤት ናይጄሪያ ተለዋጭ መቀመጫ እንድታገኝ ኢትዮጵያ ድጋፍ ታደርጋለች

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2005 (ዋኢማ) -  በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ናይጄሪያ ተለዋጭ መቀመጫ እንድታገኝ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦሉቤንጋ አሺሩን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት ናይጄሪያ በአፍሪካ ውስጥ የምትጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በፀጥታው ምክር ቤት አባል ተለዋጭ መቀመጫ እንድታገኝ ኢትዮጵያ ድጋፍ ታደርጋለች።

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦሉቤንጋ አሺሩ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ሁለቱ አገራት ባላቸው የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት በአፍሪካ ኀብረት መጠናከርና በአህጉሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል። አሁን ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ናይጄሪያ ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ሰላም እንዲሰፍንና ሁለቱ አገራት የፈረሟቸው ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ የምትጫወተውን ሚና አምባሳደር አሺሩ አድንቀዋል። በኢትዮጵያና በናይጄሪያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የአገራቱ የጋራ ኮሚሽን በቅርቡ በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ባለስልጣናቱ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።

ሁለቱ አገራት ከዚህ በፊት የአፍሪካ ኀብረትን ለማጠናከር ይጫወቱት የነበረውን ሚና አሁንም አጠናክረው ለመቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የአፍሪካ ኀብረትንና ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነትን /ኔፓድ/ ለማጠናከር እንዲሁም በአህጉሩ የሚፈጠሩ ችግሮችና ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት በሚቻልበት ላይ ሁለቱ ባለስልጣናት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦሉቤንጋ አሺሩ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን የተላከ ልዩ መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቅርበዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ተለዋጭ መቀመጫ የሚሰጠው ለምዕራብ አፍሪካ ሲሆን ቶጎ በቅርቡ መቀመጫውን ትለቃለች።