ለጋምቤላ ክልል ሁለንተናዊ እድገት የፌዴራል ስርዓቱ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው

  • PDF

ጋምቤላ፤ ታህሳስ 25/2005(ዋኢማ) - በጋምቤላ ክልል ለተመዘገበው ሁለንተናዊ እድገት የፌዴራል ስርዓቱ ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተ የክልሉ ፕሬዚዳንት አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ አቶ ኡመድ ኡቦንግ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በክልሉ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ለተመዘገበው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገቶች የፌዴራል ስርዓቱ የጎላ ሚና ተጫውቷል።

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ባመቻቸው የመንግሥት መዋቅር መሠረት በጋምቤላ ክልል  ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች እንዲያድጉ ማድረጉን ጠቁመው፤ ክልሉ ከሌሎች ክልሎች እኩል በልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት አስርት አመታት በፊት የክልሉ የጤና ሽፋን 19 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኡመድ በአሁኑ ወቅት 65 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

በትምህርት ዘርፉ የላቀ ውጤት እንደተመዘገበ የጠቆሙት የክልሉ ፕሬዚዳንት በአሁኑ ወቅት ሽፋኑ 94 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

በክልሉ ያለውን የጤና ሽፋን ሲገልፁም 27 የጤና ተቋማት በክልሉ በመገንባታቸው የእናቶችና የህጻናት ሞት መቀነሱን ተናግረዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንም ከአስር አመት በፊት 5 በመቶ እንደነበር ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት 86 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

በክልሉ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ማለትም መንገድ፣ ቴሌኮምና የመብራት አገልግሎት መዘርጋታቸውን ገልፀው፤ ይህም የክልሉን እድገት ከማፋጠኑም በላይ ከሌሎች ክልሎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት አሳድጎታል ብለዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩምና ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመመቻቸቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለኢንቨስትመንት መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ 389 ባለሀብቶች በክልሉ በግብርና ስራ መሰማራታቸውን ከተሰማሩት ውስጥም ዘጠኝ የሚሆኑት የውጪ ባለሀብቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ ያሉ አርብቶ አደርና አርሶ አደር ማህበረሰብን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራምን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመታት 29 ሺ 243 የሚሆኑ ቤተሰቦችን በ43 መንደሮች ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመው፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመትም 10 ሺ 688 ቤተሰቦችን በመንደር ለማስፈር መታቀዱን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።

በሰፈራው አካባቢም 19 የትምህርት፣ 22 የጤና እና 144 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት መገንባቱን ገልፀው፤ የመንደር ማሰባሰቡ የግብርና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የክልሉን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ እንደሚያደርገው ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።