ሊቀመንበሯ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በአገራቸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የወሰዱትን አቋም አደነቁ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2005(ዋኢማ)-  የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ቦዚዜ በአገራቸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የወሰዱትን አቋም አደነቁ።

ሊቀመንበሯ ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ-ዙማ ፕሬዚዳንቱ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የቤኒኑ ፕሬዚዳንት ቶማስ ያዪ ቦኒ ትናንት ባደረጉት ጉብኝት ከአማጺው ቡድን ጋር ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር መዘጋጀታቸውን ማረጋገጣቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ቦዚዜ አገራቸው ያጋጠማትን ችግር በውይይት ለመፍታት የደረሱበት ውሳኔ ወታደራዊ ግጭትንና ተከትሎ የሚመጡትን ችግሮች ለመፍታት ስለሚያስችል መልካም አማራጭ መሆኑንም አስረድተዋል።

አገሪቱን በወታደራዊ ኃይል ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀሰው ወገንም ወደ ድርድር በመመለስ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥበትን መንገድ መሻት እንደሚገባውም ሊቀመንበሯ አሳስበዋል። የአፍሪካ ኅብረት በኃይል ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴን በተለይም በተደራጀ ወታደራዊ ኃይል የፖለቲካ ዓላማዎችን ማራመድን አጥብቆ እንደሚኮንን የገለጹት ዶክተር ድላሚኒ-ዙማ፣በዚህ ዓይነት የሚደረግ እንቅስቃሴ ለአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት አስጊ ከመሆኑም በላይ፤የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውንና የማህበረ-ኢኮኖሚውን ልማት እንደሚያደናቅፍም አስገንዝበዋል።

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው አማጺ ኃይል ከድርጊቱ ካልታቀበ በአፍሪካ የዴሞክራሲ፣የምርጫና መልካም አስተዳደር ቻርተርና አግባብ ባላቸው ድንጋጌዎች መሠረት አገሪቱ ከኅብረቱ ማናቸውም ተግባራት እንደምትታገድም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ቦኒ በአገሪቱ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ችግር መፍትሄ ለማፈላለግና በአፍሪካ ሰላም ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረትም ሊቀመንበሯ አድንቀዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የማዕከላዊ አፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ታኅሣሥ 12 ቀን 2005 በንጃሚና፣ቻድ ባደረገው አስቸኳይ የመሪዎች ስብሰባ ከችግሩ በአፋጣኝ ለመውጣት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና በተጓዳኝ የሚደረጉ ተግባራትን እንደሚደግፉ ማረጋገጣቸውን ኮሚሽኑን ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።